አዳጊዎቹ ክለቦች የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዲሱን የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፈው እሁድ በሁለት ጨዋታዎች መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጅማሬውን ባደረገው የአንደኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ ከተማን ከአዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገናኝቶ ያለምንም ግብ ሲጠናቀቅ፤ በቡና ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና 1 ለምንም በሆነ ውጤት ሲዳማ ቡናን ማሸነፉ ይታወቃል፡፡ የሊጉ አንደኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን፤ ወደ ሊጉ ያደጉት ሁለት ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከወራት እረፍት በኋላ መስከረም 20/2016 ዓ.ም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ ተጀምሯል፡፡ በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎች ቀዝቀዝ ብሎ ብዙ ግቦችን ሳያስተናግድ የተጀመረው ሊጉ ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች አዲስ አዳጊዎቹን ክለቦች የሚያፋልም በመሆኑ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ጨዋታቸው የሚያገጥሟቸው ቡድኖችም ባለፈው ዓመት በሊጉ ግርጌ ያጠናቀቁ መሆናቸው ተመጣጣኝ ፉክክር ይኖራል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ዛሬ 9 ሰዓት ላይ ፕሪሚየር ሊጉን ከ15 ዓመታት በኋላ ዳግም መቀላቀል የቻለው ሻሸመኔ ከተማ ከሊጉ ጠንካራ ክለብ ወላይታ ድቻ ጋር ይፋልማል፡፡ ሁለቱ ክለቦች የውድድር ዓመቱን በውጤት ታጅበው በመጀመርም የሊጉን ረጅም ጉዞ ከወዲሁ ለማሳመር የሚፋለሙ ይሆናል። በተለይ ለአዳጊዎቹ ክለቦች ከጨዋታው ውጤት ይዞ መውጣት በራስ መተማመናቸውንም ስለሚያጎለብት ለቀጣይ ጨዋታ ስንቅ ይሆናቸዋል። ቀድሞ ነጥብ መሰብሰብ ክለቦች በሊጉ የመቆየት እድላቸውን ስለሚያሰፋ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ጨዋታውን ማሸነፍ ለወላይታ ድቻ አስፈላጊ ቢሆንም ለሻሸመኔ ግን ከአስፈላጊም በላይ ነው፡፡

ሻሸመኔ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት ከደገመ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የሚችልበት እድል አለው፡፡ ይህ ግን ወላይታ ድቻ በሊጉ ካለው ልምድና ጥንካሬ አንጻር ለሻሸመኔ ከተማ ቀላል ላይሆን ይችላል። የጦና ንቦቹ በ2015 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር 12ኛ ደረጃን ይዘው ቢያጠናቅቁም በቀላሉ ከማይረቱ ክለቦች ይመደባሉ። አካላዊ ንኪኪዎችን በማብዛት የሚጫወቱ ስለሆነም ለተጋጣሚ ክለቦች በፈታኝነታቸው ይታወቃሉ። ሻሸመኔ በበኩሉ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ ጊዜን በማሳለፍ ሊጉን በአስደናቂ ሁኔታ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም ከከፍተኛ ሊጉ ያሳደገውን አሰልጣኝ ውል ያራዘመ ሲሆን በዝውውሩም በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ራሱን ለማጠናከርም ችሏል፡፡ ይህም ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ከአንድ ሙሉ ቡድን የሚበልጥ በመሆኑ ለቡድን ውህደት ጊዜ ስለሚያስፈልገው ጨዋታውን አስቸጋሪ ሊያደርግበት ይችላል፡፡ ሻሸመኔዎች በቀጣይ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ሲያስተናግዱ የጦና ንቦች በበኩላቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታሉ፡፡

በከፍተኛ ሊጉ አስደናቂ ጊዜን በማሳለፍ ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀል የቻለው ሌላኛው ክለብ ሀምበሪቾ ዱራሜ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ድሬዳዋ ከተማን በመግጠም ይጀምራል፡፡ ሀምበሪቾ በክረምቱ የዝውወር መስኮት ብዙም ተሳትፎ ያላደረገ ሲሆን ወደ ቅድመ ውድድር ዓመት ዝግጅትም የገባው ዘግየት ብሎ ነው። ክለቡ ራሱን በዝውውር በአግባቡ ባለማጠናከሩና በቂ የዝግጅት ጊዜን ባለማሳለፉ በሊጉ የሚኖረው ቆይታ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ተጋጣሚው ድሬዳዋ በበኩሉ የተሻለ ዝግጅትና የዝውውር ጊዜን በማሳለፉ ለሀምበሪቾ ከባድ ተጋጣሚ መሆኑ አይቀርም። የቡድኑን ወሳኝ አጥቂ ቢኒያም ጌታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢሸኝም ካለው የቡድን ጥልቀትና ልምድ አኳያ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት እንዲሰጠው ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ድሬዳዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሊጉ ለመቆየት የሚጫወት ክለብ እየሆነ መምጣቱ ለሀምበሪቾ የራስ መተማመኑን መጨመሩ አይቀርም፡፡ በዚህም በሁለቱ ክለቦች በኩል በጨዋታው ላይ ተመጣጣኝ ፉክክር እንደሚኖር ይገመታል፡፡

ድሬዳዋ በ2015 ዓ.ም በፕሪሚየር ሊግ 30 ጨዋታዎችን ከውኖ 11 ድል አድርጎ በ7 አቻ በመውጣት በ12 ደግሞ መሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም 40 ነጥቦችን በመሰብሰብ 10ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር በሊጉ መቆየት የቻለው፡፡ ሀምበሪቾ በበኩሉ በከፍተኛ ሊጉ ከፍተኛ ተጋድሎን በማድረግ ነው ፕሪሚየር ሊጉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለው፡፡ ክለቡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያሳደገውን አሰልጣኝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የሚያቆየውን ውል ያስፈረመ ሲሆን ያም በክለቡ ውስጥ መረጋጋት የሚፈጥር በመሆኑ በሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ ያስችለዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ውጤት ይዞ መውጣት የሚችል ከሆነም በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ከወዲሁ እንዲሰንቅ ያስችለዋል፡፡ ድሬዳዋ በሁለተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ሊጉን በድል ከጀመረው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ይጫወታል፤ ሀምበሪቾ ዱራሜ ደግሞ ከቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጋጠማል፡፡ ሁለቱም ክለቦች ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ከባድ ጨዋታ መነቃቃትንና በራስ መተማመናቸውን እንዲያዳብሩ የሚረዳቸውም ይሆናል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You