የዓለም አትሌቲክስ በዓመቱ ለማከናወን ያቀዳቸውን ዓለም አቀፍ የውድድር መርሐ ግብሮቹን አጠናቋል።በነዚህ ውድድሮች ምርጥ አቋም ያሳዩ አትሌቶችንና ሌሎች ባለሙያዎችን ወደመሸለምም እየተንደረደረ ይገኛል።የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና፣ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እና የዓለም የጎዳና ላይ ቻምፒዮና በዓመቱ የተደረጉ ዋና ዋና ውድድሮች ሲሆኑ፤ እንደ ዳይመንድ ሊግ፣ የቤት ውስጥን ጨምሮ ሌሎች የዙር ውድድሮችም መከናወናቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በእነዚህ ውድድሮች ላይ አትሌቶቿን በማሳተፍ ስኬታማ የውድድር ዓመት አሳልፋለች።ይህም እንደ አጠቃላይ ሲታይ መልካም የሚባሉ ውጤቶች የታዩበት፣ ለቀጣዩ 2024 የፓሪስ ኦሊምፒክም ደካማና ጠንካራ ጎኖች የተለዩበት ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉም ዓመቱ 90 ከመቶ ስኬታማ ሊባል የሚችል ሆኖ ማለፉን ትናገራለች።ውድድሮች መብዛታቸው ለአትሌቶችም ሆነ በስፖርቱ ስመጥር ለሆኑ ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።ባለፉት ዓመታት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች ተሰርዘዋል፣ አዘጋጅ ሀገራትም ተቀያይረዋል፣ እንዲሁም የመርሐ ግብሮች መሸጋሸግ፣ መዘበራረቅና መደራረብ ተፈጥሯል።ይህ ዓመት በአንጻራዊነት ሲታይ ግን ውድድሮች ወደነበሩበት የተመለሱበት ነበር፡፡
ከወር በፊት በቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም ቻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኦሪጎን የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ቢያቅድም በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ በተጠበቁ ውድድሮች ውጤት አልተገኘም።ያም ሆኖ በሴት አትሌቶች የተመዘገቡ ውጤቶች የውድድር ዓመቱን ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ደራርቱ ታብራራለች።ይህም ተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ለሚኖረው የፓሪሱ ኦሊምፒክም ትምህርት የሰጠና ተገቢውን ዝግጅት ያመላከተ ነበር።ከቀናት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ በተካሄደው የጎዳና ላይ ቻምፒዮናም መልካም የሚባል ውጤት በማስመዝገብ የውድድር ዓመቱ መጠናቀቁን አብራርታለች።
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሀገር ውስጥ የውድድር መርሐ ግብሮቹን በመጪው የጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም የሚጀምር ሲሆን፤ ጠቅላላ ጉባኤውንም በተመሳሳይ ያካሂዳል።በቀጣዩ የፈረንጆቹ የውድድር ዓመት የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚደረጉ ዝግጅቶችም በዚያው የሚቀጥሉ ይሆናል።በመሆኑም በተጠናቀቀው ዓመት መልካም ውጤት የተገኘ ባቸውን በማጠናከር እንዲሁም ውጤት የታጣባቸው ላይ ትኩረት በማድረግ በዋነኛነት የፓሪሱን ኦሊምፒክ ያለመ ዝግጅት እንደሚደረግም ገልፃለች።
በሌላ በኩል በዓመቱ በአራት አትሌቶች (ለሜቻ ግርማ፣ ጉዳፍ ጸጋይ፣ ትዕግስት ግርማ እንዲሁም ድርቤ ወልተጂ)የዓለም ክብረወሰኖች የተሻሻሉበትም እንደነበር ያስታወሰችው ደራርቱ፣ ለዚህ ውጤት ድርሻ የነበራቸው አካላት ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል ትላለች።ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ እንደ ቀድሞ ብሄራዊ አትሌቶች የሌሉትና እገዛም የማያደርግ እንደመሆኑ አትሌቶች በጥረታቸው ያስመዘገቡት ነው።በመሆኑም በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለያዩ ውድድሮች ላይ ባንዲራዋን ከፍ ያደረጉና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የገነቡ አትሌቶች ሊመሰገኑ ይገባል።
እንደ ደራርቱ ማብራሪያ፣ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅት እንዲሁም ሽልማት ፌዴሬሽኑ በራሱ ከሚያደርገው ባለፈ በመንግሥት በኩልም እገዛ ይደረግለታል።በተለያዩ ውድድሮች ውጤት ላመጡ አትሌቶች የመሬት ሽልማት ሲሰጥ ቢቆይም በቡዳፔስት ዓለም ቻምፒዮና ለተካፈሉት ግን አልተሰጠም።በሌላ በኩል ለውጤቱ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት አሰልጣኞች በእኩል አይን አይታዩም።በዚህም ምክንያት ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 7 የሚሆኑ አሰልጣኞች በውጪ ሀገራት ቀርተዋል።አሰልጣኝ ከሌለ አትሌት አይኖርምና በመንግሥት በኩል እኩል ሽልማትና ዕውቅና እንዲሰጥ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት መገንቢያ የመሬት ሽልማት በዓለም ቻምፒዮናው ውጤት ላስመዘገቡ እንዲሁም ክብረወሰን ለሰበሩ አትሌቶች እንዲሰጥም ጠይቃለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በ70 ዓመት ታሪኩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የለውም። አትሌቶች ለሀገራቸው ሜዳሊያ የሚያስመዘግቡትም ሆነ ክብረወሰኖችን የሚያሻሽሉት በተመቻቸ የማዘውተሪያ ስፍራ ተዘጋጅተው አይደለም። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የመለማመጃ እንዲሁም የውድድር ቦታን ያካተተ ሁለገብ የአትሌቲክስ ማዕከል እንዲገነባ ለመንግሥትም ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል።ከሩጫ ባለፈ የሜዳ ተግባራት ላይም ውጤት እንዳይገኝ አንዱ መሰናክል በቂ የመለማመጃ ቦታ አለመኖር ነው።በመሆኑም እንደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ሁሉ በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተካፋይና ውጤታማ ለመሆን እንዲቻል ጥያቄው በመንግሥት በኩል አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ጥሪዋን አቅርባለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም