ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የሰጠችውን ትኩረት ተከትሎ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እንዲሰማራ በየጊዜው ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ሀገሪቱ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ያላትን እምቅ አቅም በማሳየት፣ ዘርፉን የሚያሳድጉ ሕጎችን በማውጣትና በመሳሰሉት ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል፡፡
በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎች ዘርፉን እንደሚፈለገው አላራምድ ባሉ ቁጥርም ማነቆዎቹን ለመፍታት ሠርቷል፡፡ ማነቆዎቹን ለመፍታት ካደረጋቸው ጥረቶች መካከል የዘርፉን የመሬት አቅርቦት እና የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት የሄደበት ርቀት ይጠቀሳል፡፡ ለእዚህም የገነባቸው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ የፓርኮቹ መገንባት በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እስከ አሁንም 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
ይህም ባለሀብቶቹ የመሬት፣ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ዘርፍ ችግር ሳይገጥማቸው ማምረቻዎቻቸውን አምጥተው በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሼዶች በመትከል በቀጥታ ወደ ማምረትና መላክ የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ ፈጥሯል፤ ይህ ምቹ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ኢንዱስትሪዎች ባለሀብቶችን ጭምር ለመሳብ አስችሏል፡፡
ባለሀብቶቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል፤ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡም ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ናቸው፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው መስራት ጀምረዋል፡፡
የኢንቨስትመንቱ እንቅስቃሴው በክልሎችም በስፋት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በክልሎች የተለያዩ ከተሞች በኢንቨስትመንቱ መስክ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ባለሀብቶች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በመሳሰሉት ዘርፎች ተሰማርተው እያለሙ ተኪ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በስፋት እያመረቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ የባለሀብቶቹ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ይህ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጎልቶ ከሚታይባቸው ክልሎች አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ነው፡፡ ክልሉ እንደ ክልል ከተቋቋመ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም፣ በዘርፉ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
ክልሉ ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ሀብቶች እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የክልሉን ሀብቶች ለመለየት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ክልሉ ለዓመታዊ ሰብሎች፣ ለቡናና ቅመማ ቅመም እና ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚውል ሰፊና ለም መሬት አለው፡፡ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎችም የኢንቨስትመንት መዳረሻና አማራጭ መሆን ይችላል፡፡
ክልሉ ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ ማዕድናት ባለፀጋ እንደሆነም የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች በስፋት የሚገኙ ሲሆን፣ ማእድኑ እየለማ ያለበት ሁኔታም አለ።
በክልሉ 15 አነስተኛ ደረጃ አምራቾች እና ሦስት በከፍተኛ ደረጃ አምራቾች በአጠቃላይ 18 አምራቾች ፈቃድ ወስደው ድንጋይ ከሰል ወደ ማምረት ሥራ ገብተዋል ፡፡ ከክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 748 ሺ24 ቶን ያህል የድንጋይ ከሰል ለማምረት ታቅዶ፤ 209ሺ398 ቶን ለማምረት ተችሏል፡፡ ከገቢም አንጻር 30 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማስገባት ታቅዶ፤ 29 ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን የክልሉ ማእድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የብረት ማዕድንም ሌላው በክልሉ የሚገኝ ሀብት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ማዕድን ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ በክልሉ ገና በጥናት ያልተለዩ ብዙ ሀብቶች አሉ፡፡ ኦፓልና ሌሎች ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
በርካታ ባለሀብቶች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ክልሉ በክልልነት ከተዋቀረ አጭር እድሜ ቢኖረውም፣ ኢንቨስትመንቱ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ ሰፊ ጥናትና ውይይት ተደርጓል፡፡ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ለማበረታታት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና የካቢኔ አባላትን ጭምር ያሳተፈ የንቅናቄና የፕሮሞሽን ሥራ በስፋት ተሠርቷል፡፡
ክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተሰሩት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎች በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ በተለያየ የሥራ ደረጃ ላይ የሚገኙና ለ112ሺ983 ዜጎች የሥራ እድል (7983 ቋሚ እና 105ሺ ጊዜያዊ) የፈጠሩ 380 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2015 በጀት ዓመት አበረታች የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ማስመዝገቡንና በ2016 በጀት ዓመትም ይህን አፈፃፀሙን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ2015 የበጀት ዓመት በክልሉ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 141 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ፕሮጀክቶች መካከል በግብርና 48፣ በማምረቻ 50 እና በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ ስድስቱ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለሁለት ሺ 892 ዜጎች ቋሚ እና ለ79ሺ335 ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር እንዲሁም ለግብርና ሥራዎች የሚውል 32ሺ170 ሄክታር መሬት መለየት ተችሏል፡፡ ሦስት ሺ 600 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለ648 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትል ተደርጓል፡፡ ማኅበረሰቡ ከኢንቨስትመንት ሥራዎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል እንዲሁም ባለሀብቶችም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚያከናውኗቸው ተግባራትም ኅብረተሰቡ የልዩ ልዩ ድጋፎችና አገልግሎቶች ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ በ2015 በጀት ዓመት ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በ2016 በጀት ዓመትም አጠናክሮ ለማስቀጠል እቅድ ማዘጋጀቱንና ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ ይገልጻሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ በበጀት ዓመቱ በግብርና 84፣ በአገልግሎት 64 እንዲሁም በኢንዱስትሪ 58፣ በአጠቃላይ ለ206፣ ፕሮጀክቶች ፈቃድ በመስጠት ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዷል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ11 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንደሚያስመዘግቡና ከ109ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች (ሦስት ሺ 181 ቋሚ እና 105ሺ 951) የሥራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፡
በክልሉ በርካታ ባለሀብቶች የተሰማሩት በግብርና ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ በርካታ ባለሀብቶች ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ ማድረግ ከ2016 በጀት ዓመት እቅዶች መካከል አንዱ መሆኑን ምክትል የቢሮ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በክልሉ ከግብርናው ዘርፍ ባሻገር ባለሀብቶች በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችል የመሬት ዝግጅት መደረጉንም ነው ያስታወቁት፡፡
እንደ አቶ ከበደ ገለፃ፣ ከ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በክልሉ እስካሁን ያለው ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት መቀንሱን ተከትሎ ወደ ኢንቨስትመንት ተግባራት በስፋት ለመሰማራት ከሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ጎን ለጎን፣ የመሬት ኦዲቲንግ ተግባር በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት በተከናወነ የመሬት ኦዲቲንግ ሥራ ስድስት ሺ 628 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስገባት ተችሏል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች ካልተወሰዱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በታለመላቸው የጊዜ ገደብ ላይጠናቀቁ ይችላሉ፡፡ ለዓመታዊ ሰብል ምርት ልማት የሚውል መሬት ፆም ማደር እንደሌለበት ታምኖ፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት 64 ፕሮጀክቶችን ኦዲት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህ የኦዲቲንግ ሥራ መሬት ተረክበው የማያለሙ ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ወይም መሬቱን ለሌሎች አልሚዎች ለማስተላለፍ ያግዛል፡፡›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡
የኢንቨስትመንት አዋጁ (1180/2010) ለባለሀብቶች የተሰጡ መሬቶች ሊነጠቁ የሚችሉባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በግልፅ አስቀምጧል፡፡ የባለሀብቶች የሥራ እንቅስቃሴዎች በእነዚህ መስፈርቶች መሰረት ተገምግመው ቅድመ ሁኔታዎቹ ካልተሟሉ መሬት እንዲነጠቁ ይደረጋል›› ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እየተሰጠም ይገኛል፡፡ ለአምስት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ፕሮጀክቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ 28 የግብርና ዘርፍ ፕሮጀክቶች ደግሞ አስፈላጊው ማጣራትና ግምገማ ተደርጎባቸዋል፡፡
ለኢንቨስትመንት የሚሆን አቅም ያለውን መሬት በማጥናት ረገድ በበጀት ዓመቱ 12ሺ650 ሄክታር መሬት ለማጥናት መታቀዱን ጠቅሰው፣ የግብርና ሚኒስቴር ከክልሉ በቀረበለት የድጋፍ ጥያቄና የፕሮጀክት እቅድ መሰረት ለጥናቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ተቋማት ለባለሀብቶች መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማስፈን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች በጥልቀት እንዲታዩ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሬት በፍጥነት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡
በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ ነባሮቹን የማጠናከር እና የተጀመሩትን የመጨረስ እንጂ አዳዲስ በተለይ መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንደሌሉም አቶ ከበደ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፣ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል ሊፈጥር የሚችለው ዋናው ችግር የበጀት እጥረት ነው፡፡ የክልሉ ዞኖች የሚመደብላቸው በጀት ቀደም ሲል በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር በነበሩበት ጊዜ የነበራቸው በጀት ነው፡፡ ሀገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታም ተጨማሪ በጀት ለማግኘት የሚያስችል አይደለም፡፡
‹‹በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ‹አንድ ባለ ሀብት ወደ አንድ አካባቢ ሲመጣ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ምንድን ነው?› የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚሻ ዐቢይ ጉዳይ ነው›› የሚሉት አቶ ከበደ፣ ይኸው ጉዳይ የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግባር አካል እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት መስክ ሲሰማሩ የሥራ እድል መፍጠር አለባቸው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡›› ሲሉ ገልጸው፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋፅኦ የማያበረክቱ ከሆነ፣ የኅብረተሰቡ ኑሮ ሊለወጥና ሊሻሻል አይችልም ፤ ይህ ደግሞ የኢንቨስትመንት ተግባራት ዘላቂ ፋይዳ እንዳይኖራቸው ያደርጋል ይላሉ፡፡
ስለሆነም ባለሀብቶች ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት እንዲሰጡ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀው፣ በዚህ መሰረት በበጀት ዓመቱ ሰባት ሺ 949 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት የሚሰማሩት ሰርተው ለመጠቀም (ትርፍ ለማግኘት) አልመው እንደሆነ ባይካድም፣ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ለኅብረተሰቡ ዓይነተ-ብዙ ድጋፎችን ያደርጋሉ ያሉት አቶ ከበደ፣ በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋሉ፤የአረጋውያንን ቤት ያድሳሉ ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት ከ88 ኪሎ ሜትር በላይ መዳረሻ መንገዶች በባለሀብቶችና በኅብረተሰቡ ትብብር ተገንብተዋል፡፡ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ደግሞ 96 ኪሎ ሜትር መንገድ ይገነባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ባለሀብቱ ከኅብረተሰቡ ጎን፣ ኅብረተሰቡም ከባለሀብቱ ጎን ካልቆመ ጥሩ ያልሆኑ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ቀደም ሲል ከተፈጠሩ ክስተቶች ተምረናል፡፡ ባለሀብቶች ለኅብረተሰቡ ድጋፍ ሲያደርጉ ኅብረተሰቡ የባለሀብቶችን ንብረት ይጠብቃል፣ ይንከባከባል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ የኅብረተሰቡን ድጋፍ ያላገኙ ባለሀብቶች ደግሞ ብዙ ጉዳትና ኪሳራ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ ክልሉ ከባለሀብቶች ጋር ተቀራርቦ በትብብር እየሠራ ይገኛል ሲሉ የኅብረተሰቡና የባለሀብቶች ትብብር ስላለው ትልቅ ትርጉም አስረድተዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም