በውድድር ዓመቱ በሶስት ርቀቶች የዓለም ክብረወሰኖችን ሰብራለች፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ እንዲሁም በዳይመንድ ሊጉ አሸናፊ በመሆን እጅግ ስኬታማ ዓመትን አሳልፋለች፡፡ ጠንካራዋ ኬንያዊት አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን ዓመቱን ባለመሸነፍ ለማጠናቀቅም እቅድ ነበራት፤ ይሁን እንጂ ሃገሯን ወክላ በተሳተፈችበት የመጨረሻው ውድድር መረታቷ የግድ ሆኗል፡፡ አትሌቷን በመርታት የወቅቱ ተቀናቃኟ መሆኗን ያስመሰከረችው የመጪው ዘመን ኮከብ አትሌት ኢትዮጵያዊቷ ድርቤ ወልተጂ ናት፡፡
ወጣቷ አትሌት አዲስ በሆነችበት ርቀት በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም ዳይመንድ ሊግ መድረኮች ኬንያዊቷን ተከትላት ከመግባት ባለፈ አሳማኝ በሆነ ብቃት ክብረወሰን በመስበርም ጭምር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ውድድሮች ቻምፒዮና በአንድ ማይል ፉክክር አሸናፊ ሆናለች፡፡ ወጣቷ ኢትዮጵያዊት ይህን ታሪካዊ ውጤት አስመዝግባ ወደ ሃገሯ ስትመለስም ‹‹ውድድሩ ካሰብኩት በላይ ነበር፤ ለሃገሬም ሆነ ለራሴ ይህንን ውጤት በማምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ፌይዝ ኪፕዬጎን በጣም ጠንካራ አትሌት በመሆኗ እሷን ማሸነፍ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሁለት ጊዜ አብሬያት ሮጬ ሁለተኛ ደረጃን ይዤ ነበር ያጠናቀኩት፤ በዚህ ውድድር ላይም ስላሸነፍኳት ደስተኛ ነኝ፡፡ በቀጣይም ከዚህ የተሻለ በመስራት ለራሴና ለሃገሬ የሚያስደስትና ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት አደርጋለሁ›› ብላለች፡፡
የመም አትሌት የሆነችው ድርቤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎዳና ውድድሮች ተሳትፋ ይህንን ውጤት ማምጣቷ አስደናቂ መሆኑን የሚናገረው ደግሞ አሰልጣኟ ኢሳ ሁሴን ነው፡፡ በዚህ ውድድር ላይ የተሳተፈችው ከዓለም ቻምፒዮናና ዳይመንድ ሊግ መልስ በተደረገ የጥቂት ቀናት ዝግጅት ነው፡፡ ይህ የአትሌቷ አቋም የሚያሳየውም የ1ሺ500 ሜትርን ክብረወሰን ጭምር ከኬንያዊቷ አትሌት መረከብ እንደምትችል ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜ እና ስራ ይፈልጋል፤ በተከታታይ በተካሄዱ ውድድሮች ድርቤ የኪፕዬጎን ተፎካካሪ በመሆን ስነልቦናዋን መገንባት ችላለች፡፡ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግም ለፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ከመወከል ባለፈ አዲስ ክብረወሰንን ለማስመዝገብ አቅደው እየሰሩ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ አማተር ሯጮችን እንዲሁም የየሃገራቸውን ብሄራዊ ቡድን የወከሉ አትሌቶችን በማሳተፍ በላቲቪያ ሪጋ የተካሄደው የጎዳና ላይ የዓለም ቻምፒዮና በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ውድድር ተካፋይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 2የወርቅ፣ 4 የብር እና 1የነሃስ በጥቅሉ 7 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከዓለምም ከአፍሪካም የሁለተኛነት ደረጃን ይዘዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያን የወከሉት አትሌቶች ትናንት ማለዳ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የወርቅ ሜዳሊያ ላጠለቁ 40ሺ ብር፣ ለብር ሜዳሊያ ባለቤቶች 30ሺ ብር፣ ለነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች 15ሺ ብር እንዲሁም ዲፕሎማ ላመጡ አትሌቶች 10ሺ ብር በማበረታቻ መልክ አበርክቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ሜዳሊያ በማስመዝገብ፣ የዓለም ክብረወሰንን በመስበር እንዲሁም በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና በ1ሺ500ሜትር እና 5000ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችውን ኬንያዊት አትሌት መርታት የተቻለበት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጻለች፡፡ ውድድሩ ከቡዳፔስት ማግስት የተካሄደ በመሆኑ እንጂ ምናልባትም የተሻለ ዝግጅት ተደርጎበት ቢሆን ከዚህ የተለየ ውጤት ሊገኝበት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የተገኘው ውጤት አስደሳች ሊባል የሚችል ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከሚካሄዱ ውድድሮች ይህ ቻምፒዮና የመጨረሻው ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያ እንደ አጠቃላይ በአትሌቲክስ መልካም በሚባል ውጤት ዓመቱን እንደደመደመችም አክላለች፡፡
ከረጅም ጉዳት መልስ ወደ ውድድር የተመለሰው አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት በ5ኪሎ ሜትር የወንዶች ውድድር የሃገሩን ልጅ አስከትሎ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን የግሉ ሊያደርግ ችሏል፡፡ በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና ውጤት አለመምጣቱ የሚያስቆጨው አትሌቱ ህዝቡን ለመካስ ባደረገው ጥረት ውጤታማ ሊሆን እንደቻለ ይገልጻል። ከ3ዓመት ጉዳት በኋላ ወደ ውድድር ተመልሶ ውጤት ማስመዝገብ እንዲሁም የመጀመሪያው ቻምፒዮና እንደመሆኑ አስደሳች ነው፡፡ ውድድሩ ወደሚካሄድበት ሪጋ የነበረው ጉዞ እንዲሁም በውድድር ወቅት የነበረው ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ፈታኝ ቢሆንም ውጤት የመጣው ይህንን በመቋቋም ነው፡፡ ከጉዳት መልስ ውጤታማ ለመሆን በስነልቦናም ሆነ በአካል ብቃት ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ውጤት ለቀጣዩ ኦሊምፒክ ሞራል ቢሆንም፤ አስቀድሞ ዝግጅት በማድረግ ውጤታማ ለመሆን አትሌቶች እየተቸገሩበት ያለው የማዘውተሪያ ችግር ሊቀረፍ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016