የቲአትር ባለሙያ ናት። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ውስጥም ሠርታለች። በአሁኑ ጊዜም በአሜሪካን ሀገር ነው የምትኖረው። ኑሮም ሆነ የሥራ ጫና ሳያግዳት በማህበራዊ ድህረ – ገጽ ላይ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራ በማከናወን ላይ ትገኛለች። ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር እያከናወነች ባለው የበጎ አድራጎት ሥራዎቿ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ችላለች።በዚህ መልካም ሥራ ላይ የምትገኘውን ሕይወት ታደሰን ስለሕይወት ልምዷ እንድታካፍለን፣ስለበጎ ሥራዎችዋም እንድታጫውተን በመጋበዝ ቆይታ አድርገናል።
ሕይወት ትምህርቷን የተከታተለችው ተወልዳ ባደገችበት ጎንደር ከተማ ውስጥ ነው።ሕይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችበት ፃድቁ ዮሃንስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ ያስጠሩ ታላላቅ ሰዎችን ያፈራ መሆኑንና የፊልም ባለሙያውን ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማን ለአብነት ትጠቅሳለች።
ሕይወት ስለትምህርትቤት ቆይታዋም እንደነገረችን፤ ከልጅነቷ ጀምሮ የማንበብ ልምድ ስለነበራት ትምህርት ቤት ውስጥ በተለያዩ ክበቦች ውስጥ በንቃት ትሳተፍ ነበር።
ሕይወት ትምህርቷም ሆነ ኑሮዋ በተወለደችበት ጎንደር ከተማ አልዘለቀም። አያቷ እማሆይ የሺ ተሰማ በማረፋቸው ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመምጣት ተገደደች።አዲስ አበባ ከተማ በአክስቷ ቤት ሆና የመሰናዶ ትምህርቷን ቀጠለች።
ሕይወት የልጅነት ፍላጎቷ እና ተሰጥኦዋ አብሯት አድጎ ፤ ከተማን ተሻግሮ ወደ ቲአትር ሙያ እንድታዘነብል አድርጓታል። የመሰናዶ ትምህርቷን ስትጨርስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቲአትር እና ሥነ-ጥበባት ትምህርት ክፍል ተቀላቀለች ። የዩኒቨርሲቲ ተመርቃ እንደወጣችም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የመሥራት እድሉን አግኝታለች። ‹‹ራሴን እንደ ቲአትር ባለሙያ እንጂ እንደጋዜጠኛ አልቆጥረውም ይህ ማዕረግ ይገባኛል ብዬም አላስብም። ነገር ግን ቲአትር እና ሚዲያው በሀገራችን የተቀራረበ ነገር በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ላይ የመሥራት እድሉ ነበረኝ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። እኔም በዚህ ሙያ ላይ ጋዜጠኝነትን ተምረውና ብዙ ዋጋ ከፍለው የሚሠሩበት የማደንቃቸው ጋዜጠኞች አሉ›› ስትልም ትገልጻለች።
‹‹በምድር ላይ ስኖር በልቼ ፣ ጥሩ ለብሼ ፣ አልያም ጥሩ መኪና ይዤ ብቻ ለመኖር ተፈጥሪያለሁ ብዬ አላስብም ነገር ግን የቅርቤ ከምላቸው ሰዎች ባለፈ ለማላውቃቸው እነሱም ለማያውቁኝ ለተቸገሩ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ለነርሱ መድረስ እፈልጋለሁ። ሰዎችን በማገዝ መማር እየፈለጉ ካልቻሉት ጋር ፣ መኖር እየፈለጉ ከከበዳቸው ጋር ችግራቸውን እየተጋራሁ መኖር የምንጊዜም ፍላጎቴ ነው።›› የምትለው ሕይወት ሙያዋን ለበጎ ምግባር በማዋልም ተጠቅማበታለች።
ሕይወት የግልዋን የማህበራዊ ገፅ በጎ ሥራዎችን ለመሥራትና መልካም መልዕክቶችን ሃሳቦችን ለማስተላለፍ ትጠቀምበታለች። ማህበራዊ ሚዲያን አብዝታ መጠቀም እና ጊዜዋን ለበጎ ዓላማ መስጠት የጀመረችውም ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረሽሽኝ በዓለም ላይ ስጋት መሆኑ ይፋ በተደረገበት ወቅት ብዙዎች በቤታቸው መቆየት ተገደው በነበረበት ወቅት ነው።
አሜሪካ ኮቪድ አብዝቶ ከመታቸው ሀገራት አንዷ ነበረች በዚሀ ጊዜም ሕይወት ሥራዋን አቁማ በቤት ውስጥ መቀመት ነበረባት። ወቅቱ ምንም እንኳን ለኢኮኖሚ መዳከም ምክንያት የሆነ እና የብዙዎችን ሕይወት ችግር ውስጥ የከተተ ቢሆንም እጅግ በጣም ብዙ አዳዲስ ሃሳቦች የተፈጠሩበት እና ሰዎች ራሳቸውን እንዲፈትሹበት እድል የሰጠ እንደነበር አይዘነጋም። ሕይወትም በቤቷ ስትቆይ በቤት ውስጥ ከሚኖርባት ሃላፊነት ባሻገር ሰፊ ሰዓቷን የማህበራዊ ገፅ ላይ ማሳለፍ ጀመረች። በማህበራዊ ገፅ ላይም ሌሎች ቤተሰቦችን አፈራች።
ወደ በጎ አድራጎት ሥራዎች እንድትገባ መነሻ የሆናት ግን በኢትዮጵያ የሚገኘው የመቄዶኒያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ማዕከሉን ለመጎብኘት የሚሄዱ እንግዶች ቁጥር እጅግ በጣም በመቀነሱ በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና ራሳቸውን መንከባከብ ለማይችሉ አዋቂዎች የዳይፐር እጥረት እንደገጠመው በመስሟቷ ነው። እርስዋም በምትኖርበት ሀገር በቀላሉ ማግኘት ስለምትችል የቅርቧ የሆኑትን ሰዎች በማስተባበር ያሰባሰበችውን ዳይፐር በቨርጂኒያ ከተማ ለሚገኘው የመቄዶኒያ ተወካይ በመስጠት ማድረስ ቻለች።
በዚህ መነሻም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በንቃት በመሳተፍ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መሥራቷን አጠናክራ ቀጠለች። በማህበራዊ ገፅ ላይም የተለያዩ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ታሪክ ትክክለኛነታቸውን በማረጋገጥ ሌሎች ተከታዮቿም ሆኑ ሃሳቧን የሚደግፉ ሰዎች እንዲሳተፉበት ታደርጋለች። ሕይወት በምታጋራቸው ታሪኮች በተለያየ ምክንያት ኑሯቸው የከበዳቸው ከባድ የሕይወት ውጣውረድን ያሳለፉ ፤ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ምክንያት ታክመው ለመዳን ከፍተኛ የህክምና ወጪ ተጠይቀው የሌሎችን ርዳታ የሚፈልጉ ህፃናት እና አዋቂዎች ጭምር ናቸው።
በዚህ መልኩ የምታከናውነው የበጎ ሥራዋ የሰዎችን እምነት ከማግኘት ባሻገር የምትኖርበት አሜሪካ ሀገር እያንዳንዱ ሰዓት ገንዘብ የሆነበት ሀገር በመሆኑ ከሥራ ከግል ሕይወት የተቀነሰ ሰዓት ለዚህ ዓላማ መስዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ነገር ግን በሕይወት አገላለፅ ከሰው ሕይወት ጋር አልያም ለህፃናት ከማድረስ ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ትላለች።
ሕይወት በምታደርጋቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎችና ቅስቀሳዎች ላይ በአብዛኛው በገንዘብ እጥረት ምክንያት መታከም ያልቻሉ የልብ ህመሙማን ህፃናትን በተመለከተ በማህበራዊ ድረገጿ ላይ በተደጋጋሚ ታጋራለች ። ‹‹ከልብ ህሙማን ህፃናት ጋር መሥራት የጀመረችበትን አጋጣሚም እንደገለጸችው የልብ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር የሆነችው አርቲስት መሠረት መብራቴ ‹‹የገና ስጦታችሁን ለልብ ህሙማን ›› የሚል ማስታወቂያ ባየችበት ጊዜ ነው።
‹‹ጊዜው በኮቪድ ምክንያት ቤት ውስጥ የተቀመጥንበት ሰዓት ነበር እናም አንድ የልብ ህመም ያለበት እና ህክምና የሚያስፈልገው ሕፃን ልጅ በጊዜው ለመታከም የሚያስፈልገው ወደ 100 ሺህ ብር ነበር ፤ ይሄ ደግሞ እኔ በምኖርበት ሀገር ገንዘብ (በዶላር) ሲሰላ ያን ያህል የሚከብድ አልነበረም ፤ ስለዚህ በዚህ በዓል ቢያንስ አንድ ህፃን ማሳከም ብንችል ብዬ አሰብኩኝ ይሄንንም ሃሳቡን ለወዳጆቼ አካፈልኳቸው እነሱም ተስማሙ እናም በመጀመሪያ ርዳታችን 3 ልጅ መታከም የሚችልበትን ወደ 270 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ ቻልን›› ስትልም ታስታውሳለች።
ሕይወት እንደገለጸችልን፤ አብዛኛውን ጊዜ በማህበራዊ ገፅ የምታጋራቸው እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚገኙት በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እሷ ደግሞ የምትኖረው ከሀገር ርቃ ነው። ነገር ግን በሷ ቁርጠኝነት ፣ ደግ ልብና ጊዜው በደረሰበት ቴክኖሎጂው አማካኝነት የቅርብ ያህል ከብዙዎች ጋር ቤተሰብ በመሆን በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን የምታከናውን ትጉ ሴት ናት። የምትሠራቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተሳክተው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን አግኝተው ፤ መታከም የሚገባቸው ሰዎች መታከሚያ ገንዘብ አግኝተው ሲታከሙ እንደገና ለምስጋና ወደርሷ ይመጣሉ። ከነዚህ ውስጥ እጅግ በጣም የማትረሳት ህፃን ነበረች ።
ህጻኗንም እንዲህ ታስታውሳለች ‹‹የዛሬ ሶስት ዓመት አንድ አባት ደወለለልኝና የስድስት ወር ህፃን ልጁ የልብ ህመም ገጥሟት ለህክምና ወደ ህንድ መሄድ ነበረባት ነገር ግን ለመታከሚያ የሚሆናት ገንዘብ ከሰዎች ተሰብስቦ እንደጎደለ ነገረኝ። እኔም የህፃኗን መታመም እርግጠኛ ከሆንኩ በኋላ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሳይወጣ የማውቃቸውን ጓደኞቼን ፣ ወዳጆቼን ጠየኳቸው ገንዘቡንም በቶሎ ማግኘት ችዬ ወደ ህንድ ሄዳ ህክምናዋን አድርጋ መመለስ ቻለች ። እኔም ፈጣሪዬን አመስግኜ ወደ ሌሎች ጉዳዮቼ እና እገዛ ወደሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፊቴን አዞርኩኝ ፤ ከዚያም ከዓመታት በኋላ አባቷ ይህቺ በልብ ህመም ተይዛ የነበረችው ህፃን ልጅ ተሽሏት አድጋ እየቦረቀች ልደቷን ስታከብር የሚያሳይ ምስል ከመልዕክት ጋር ላከልኝ። ይሄ ለኔ በጣም ትልቅና የማረሳው ታሪክ ነው።››
ሕይወት ለተቸገሩ ሰዎች ለመድረስ የልደት ቀንዋንም ለዚህ መልካም ነገር ማዋል ከጀመረች ሰንበትበት ብላለች። መነሻው የነበረው ግን እንዳጫወተችን የመጀመሪያ ልጇን የአንደኛ ዓመት ልደት ከተለመደው የልደት አከባበር ወጣ በማለት በባለቤቷ ሃሳብ አመንጪነት በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የሚገኝ ክበበ ፀሃይ የወደቁ ህፃናትን አንስቶ የሚያሳድግ ማዕከል ከሚኖሩ ህፃናት ጋር ለማክበር ወሰኑ ለማዕከሉም ከእንግዶቻቸው የሚሰጣቸው ስጦታ የልጆች የተረት መፅሃፍ እንዲሆኑ በማድረግ ሃሳቡን በማህበራዊ ገፅ ላይ በማጋራት ከተለያዩ ግለሰቦች እና የመፅሃፍ መደብር ያላቸው ሰዎች ሃሳባቸውን ደግፈውት ብዙ መፅሃፎችን መሰብሰብ ቻሉ።
የሰበሰቡትን መፅሃፍ ወደ ማዕከሉ ይዘው በመሄድ የልጃቸውን ልደት አክብረው የመፅሃፍ ስጦታውንም ለማዕከሉ አበረከቱ።
ሕይወት ከአራት ዓመት በፊት ከልብ ህሙማን ህፃናት ጋር ተቀራርባ በምትሰራበት ፤ ዓላማውን ለብዙዎች እያስረዳች ድጋፍ በምታሰባስብበት ሰዓት የልደቷ ጊዜ ደረሰ እናም የልደት ቀኗ ከመድረሱ በፊት ሰዎች የሚሰጧትን የመልካም ልደት ስጦታ በገንዘብ ተቀይሮ የልብ ህሙማን ህፃናት ህክምና ይውል ዘንድ በማህበራዊ ገጽ ላይ አጋራችው። ሃሳቡን ባጋራችበት የመጀመሪያ ልደቷ ላይም በጎ ሃሳቧን በተጋሩ መልካም ሰዎች አማካኝነት አንድ ሚሊዮን ብር ማግኘት ቻለች ይህም ለ10 ህፃናት ህክምና ዋለ።
ይህ ለርሷ ጥሩ ምልክት እና ብርታት ነበር ። ሁለተኛው ዓመት ላይ ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ሰብስባ 12 ህፃናት ሲታከሙ ከዛ በተጨማሪም ተስፋ ለህፃናት የካንሰር ህመሙማን ማዕከል ውስጥ በአካል ባትገኝም በቦታው ለሚገኙ ህፃናትና እና የህፃናቱ ቤተሰቦች የምሳ ግብዣና ለህፃናቱ የሚስፈልጋቸውን ስጦታዎች በማበርከት ደስታቸውን በመፍጠር ተከብሮ አለፈ ።
ሕይወትና የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል ቤተሰባዊነታቸው እየጠነከረ ሄዷል። በማዕከሉ ህክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቁ ህፃናት ቁጥር ከሰባት ሺህ በላይ ሲሆን፣ማዕከሉ ያለው አቅም እና የሚያስተናግዳቸው ታካሚዎች ቁጥር የሚመጣጠን አልነበረም ። እናም ልባሟ ሕይወት በዚህ የልደት ቀኗ ላይም ከገንዘብ ባሻገር በልብ ህመም ተይዘው ለህክምና ወረፋ የሚጠብቁ ህፃናትን ለማገዝ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል ያለበትን የህክምና መርጃ መሣሪያ እጥረት በመረዳት ሌላ የተሻለ ሃሳብ አመጣች ፤ በዚህም ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ሚባለው እንዲሁ አይደለምና ከሌሎች ልበ-ቀናዎች ጋር በመተባበር ኪዩር ከተባለ ዓለምአቀፍ ድርጅት 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አገኘች።
ሕይወት ባለትዳር እና የሶስት ልጆች እናት ነች። ሕይወት ባለቤቷን የተዋወቀችው ገና የ 11ኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነበር ። ‹‹ከተዋወቅን ጊዜ ጀምሮ አብረን እንኖር ነበር ብዙ ውጣ ውረዶችን ከፍታ እና ዝቅታዎችን አሳልፈናል ትናንት ያሳለፍነው ሕይወት ዛሬያችንን ሰርቶታል አሁን ባለንበት ደግሞ ፈጣሪ በልጅ ባርኮናል ይህም የሆነው ከፈጣሪ ነው አጋርነት ፤ በትዳር መጣመር ማለት አንዱ ያንዱን ሸክም መሸከም ኀዘንንም ሆነ ደስታን በጋራ ማሳለፍ ነው›› ስትልም ስለትዳሯ አጫውታናለች።
ሕይወት ወደፊት ብዙ ህልሞች እና ልታደርጋቸው የምትፈልጋቸው ሃሳቦች አሏት ፤ ከኢትዮጵያ የልብ-ህሙማን ማዕከል ጋር በተገናኘ የምታደርገውን የበጎ ሥራ ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥለው እንጂ የምትተወው እንዳልሁነም ትገልፃለች ትፈልጋለች። ከዚህም ባሻገር ከህፃናት ትምህርት ቤቶች ጋር ፣ አረጋውያንን ከማገዝ ጋር በተያያዘ ወደፊት ሰፊ ሥራዎችን የመስራት ሃሳብም ጭምር አላት ።
ሕይወት በምትሠራቸው በጎ ሥራዎች ከተለያዩ አካላት ሽልማቶች ተበርክቶላታል። ከተበረከቱላት ሽልማቶች ውስጥ በሞንቶጎሞሪ ከተማ ‹‹ቤስት ሰርቪስ አዋርድ›› ማለትም የምርጥ አገልግሎት ሽልማት ዘርፍ አለ። በዚህ ዘርፍ እጅግ በጣም ትልልቅ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የተሳተፉ ሰዎች የሚታጩበት እና የሚሸለሙበት መድረክ ነው። በዚህ መድረክ ላይም ሕይወት እጩ ሆና ቀርባለች ይህም ለሷ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ትናገራለች ።
ሌላኛው ሽልማት መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገው የጣፋጭ ሕይወት ሽልማት ማህበራዊ ድህረ-ገፅን ለበጎ ዓላማ መጠቀም በሚል የኢንስታግራም ማህበራዊ ገፅን በመጠቀም ላበረከተችው አስተዋፅኦ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላታል። ሌላኛው ሽልማት ከሠራቻቸው የበጎ ሥራዎች ከተበረከቱላት ምስጋናዎች ፣ ሽልማቶች እና እውቅናዎች ውስጥ ግን እሷ አብልጣ የምትወደው እና የምታስታውሰው በኢትዮጵያ የልብ ህመም ማዕከል የተሰጣት ሰርተፍኬት እና በማዕከሉ ውስጥ በሷና በሌሎች እገዛ ታክሞ የዳነ አንድ ህፃን ልጅ ለልደቷ የሰጣትን ስጦታ አትረሳውም ‹‹ከህፃናቱም ሆነ ከማዕከሉ የሚሰጡኝን ስጦታዎች ቤቴ አስቀምጬ ልጆቼ አድገው ሲጠይቁኝ የምናገረው ታሪክ ለሌሎች በጎ ስለመሆን የማስተምርበት ታክመው የዳኑ ህጻናት መሆናቸውን ስነግራቸው ልጆቼ ልባቸው ተነክቶ ስለመስጠት የሚማሩበት ስለሚሆን በጣም ደስተኛ ነኝ›› ስትል ትገልፃለች ።
ከሽልማቶቹ ባሻገርም በተለያየ ጊዜ ላደረገቻቸው መልካም ሥራዎች ከመቄዶኒያ የአረጋውያን ማዕከል ፣ ተስፋ አዲስ የካንሰር ህሙማን ህፃናት ማዕከል ፣ ሰሊሆም የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል ፣ ከኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል የምስጋና የምስር ወረቀት ተበርክቶላታል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሕይወት ሳትል የማታልፈው አንድ ነገር አለ ‹‹እነዚህ ሁሉ ሽልማቶች የኔ ብቻ አይደሉም የባለቤቴና የልጆቼ ናቸው። ምክንያቱም እነዚህን ሥራዎች ስሠራ ከነሱ ሰዓት እየቀነስኩ ነው የማደርገው ፣ በሀገር ውስጥም በውጭም የሚገኙ በገንዘብ ፣ በሃሳብ ደግፈውኛል ወዳጆቼ ጓደኞቼ ከጎኔ ነበሩ›› በማለት ታመሰግናለች።
ሕይወት እስከዛሬ ድረስ በግልም ከሌሎች ጋር በመሆንም በምትሠራቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች ባሰበችው ልክ ታስኬድ ዘንድ የረዷትን ባለቤቷን ፣ ልጆቿን ፣ ቤተሰቦቿን ፣ ወዳጆቿን ፣ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና በአሜሪካ የሚገኝ ተወካይ ሌሎች ተባባሪ ድርጅቶች ታመሰግናለች። የተለያዩ ርዳታ የሚፈልጉ የብዙ ሰዎችን ርብርብ የሚጠይቁ የበጎ ሥራዎችን በማህበራዊ ገፅ ላይ ለማጋራት ይዛ በምትወጣበት ጊዜ በተለያየ የዓለም ክፍል ሆነው ነገር ግን በፍላጎትና በአመኔታ ያገዟትን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ጭምር ታመሰግናለች ።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016