በሰው ሠራሽ አስተውሎት- የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ለመማር

አሁን ባለንበት ዘመን በቴክኖሎጂ የረቀቀ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial intelligence) በመጠቀም የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ቀላል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። በዚያ ልክ ቴክኖሎጂዎችን በመለማመድ በፍጥነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመራመድ ጥረት የማድረጉ ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህም ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲጨምርና እንዲያድግ እያደረገ ነው።

ለዚህም በእጃችን ላይ ያለውን ተንቀሳቃሽ ስልክ እንኳ ብንመለከት በቴክኖሎጂ አማካኝነት በቀላሉ ብዙ ጥቅሞች እያገኘን መሆኑን መገንዘብ ያስችለናል። ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ተጠቅመን ምንም ነገር ሳይገድበን የምንፈልገውን መረጃና አገልግሎት በፍጥነት እያገኘን ነው። የጊዜና የጉልበት ብክነትን እያስቀረን፣ ካልተገባ ወጪ እየዳንን ነው፤ ባለንበት ቦታ ሆነን የምንፈልገውን መረጃም ሆነ አገልግሎት እንደልብ እንድናገኝ ቴክኖሎጂው አስችሎናል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የታክሲ አገልግሎት ፈልገን የታክሲ አገልግሎት የምናገኝበትን መተግበሪያ አውርደን ስናዝ የሚፈልገውን ታክሲ ያለበትን ቦታ፣ ወደኛ ሲመጣ ያለውን ሂደት፣ በስንት ሰዓት ውስጥ መድረስ እንደሚችል፤ ስለምንሄድበት መንገድ የትራፊክ ፍሰትና ሌሎች የተሟላና የተጠናከረ መረጃ በመስጠት እያገለገለ ይገኛል።

አሁን ደግሞ እየረቀቀ በመጣው ቴክኖሎጂ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial intelligence) የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት እየተቻለ ነው። ቴክኖሎጂዎች እየረቀቁ ላቅ ወዳላ ደረጃ ለመድረሳቸው ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በሰው ሠራሽ አስተውሎት ማሽን በማስተማር ማሽኑ ደግሞ መልሶ የሰው ልጅን እንዲያስተምር ማድረግ የተቻለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

ከዚህ ግሩም ቴክኖሎጂ ግኝቶች መካከል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2016 ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት በተውጣጡ የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያዎች እንደተፈጠረች የሚነገርላት ‹‹ሶፊያ›› የተሰኘ መጠሪያ የተሰጣት ሮቦት ትጠቀሳለች። ‹‹ሶፊያ›› ሮቦት አስደናቂ ነገሮችን ስትፈጽም ተመልክተን ተደንቀናል። አብዛኞዎቻችን ይህንን ስናይ በሰው ልጆች የሰለጠነ ማሽን እንዲህ አይነት አስገራሚና አስደናቂ ሥራዎች ሲፈጸም እንዴት ብለን በእጅጉ ተገርመናል።

አሁን ደግሞ የሰው ልጅ የሚግባባበትን ቋንቋ ለማሽን በማስተማር ማሽኑ ቋንቋውን መልሶ እንዲያስተምር እየተደረገ ያለበት ሂደት ላይ ደርሰናል። ይህ ቋንቋን የማሽን ለማድረግ የሚካሄድ ሥርዓት ናቹራል ለርኒንግ ፕሮሰስ (natural language processing) ይሰኛል። በዚህ ዘዴ ቋንቋን ለማሽን በማስተማር ከተለያዩ ቁሶች፣ መተግበሪያዎችና ሶፍትዌሮች ጋር እንዲናበብ የሚያደርጉ ማስተማሪያ የሆኑ በርካታ የ‹‹ናቹራል ለርኒንግ›› አይነቶች እንዳሉ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በቅርቡም በኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ቋንቋ ማስተማር የሚችል የማሽን ሥርዓት ተሰርቶ ማጠናቀቁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ የቋንቋዎች መማሪያ ሥርዓትን የያዘ መተግበሪያ ተግባራዊ ማድረጉን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ሥርዓት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መማሪያ ነው። ሥርዓቱም ለሁለት ነገሮች ያገለግላል፤ ቋንቋዎችን ለመማር እና ድምጽን ወደ ጽሑፍ ለመቀየር የሚያስችል ነው።

ቋንቋዎችን ለመማር የሚያስችለው ሥርዓት የአማርኛ፣ የአፋን ኦሮሞ፣ የሱማሊኛና የትግረኛ ቋንቋዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ንግግርን፣ ሰላምታን፣ ቁጥሮችን፣ ቀናትን፣ ወራትን፣ ጊዜን፣ ወቅቶችን እና እነዚህን የመሳሳሉትን ነገሮች ለመለዋወጥና ለመማር ያግዛል።

ሁለተኛው ድምጽን ወደ ጽሑፍ መቀየሪያ ሥርዓት ነው፤ ይህ ደግሞ መጀመሪያ ሰዎች እየተነጋገሩ ያሉትን መተግበሪያ ላይ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች መቅዳት የሚያስችል ሲሆን፤ ድምጹ ከተቀዳ በኋላ ትራንስክራይብ አድርግ ብለን ማሽኑን ስናዘው ድምጹን ወደ ጽሁፍ ይቀይራል። ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል የተቀረጸ ድምጽ ካለ የድምጽን ፋይል ወደዚህ መተግበሪያ በመጫን አስገብተን ወደ ምንፈልገው ጽሑፍ መለወጥ (መቀየር) የሚያስችለን ሥርዓት (ሲስተም) ነው።

ይህ ሥርዓት በዋናነት ለተለያዩ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ያስችላል። ለምሳሌ በተለይ ለሚዲያ ተቋማት ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ይሰጣል። ድምጾች ከተቀረጹ በኋላ ወዲያውን ተጭኖ ወደ ሚፈለገው አይነት ጽሑፍ ተቀይሮ መልዕክቱን ማስተላለፍ ሲፈልጉ ይጠቀሙበታል። በትላልቅ ጉባኤዎች እና ስብሰባዎች ላይ የተደረጉ ውይይቶችን ድምጽ ከተቀረጸ በኋላ እንዲሁ በሁለቱ ቋንቋዎች (በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ) ተጠቅሞ ወደ ጽሁፍ ቀይሮ ለመያዝ ያገለግለናል።

የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ቋንቋዎችን ለመማር ትኩረት አድርጎ የሰራው በአራቱ ቋንቋዎች ላይ ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ እስካሁን ባለው ሂደት እነዚህን ቋንቋዎች ማሽኑ እንዲማር ሲደረግ መቆየቱን ይናገራሉ። ማሽኑ የተማረውን መልሶ ለሰው ልጅ ችግር ፈቺ የሆነ አገልግሎቶች መስጠት መቻል አለበት በሚለው እሳቤ መሠረት አራት ቋንቋዎችን እንዲማር ተደርጓል። ይህም አንድ ሰው ከእነዚህ አራት ቋንቋዎች የማይችለውን ቋንቋ ለመማር ከፈለገ እንዲማር እድሉን ይከፍትለታል። ለምሳሌ አንድ ሶማሊኛ ቋንቋን የማይችል ሰው በሶማሊኛ ቋንቋ ሰላምታ ለመስጠት ከፈለገ በቋንቋው ሰላምታ ለመጠየቅ ምን ይባላል የሚለውን ለማወቅ ማሽኑን ሲጠይቅ ሶማሊኛ ቋንቋ የሚባለው በድምጽም በጽሑፍም ይሰጠዋል። በዚህም በአማርኛ ‹‹ሰላም›› የሚለውን ቃል በሶማሊኛም ‹‹እነበድ›› በሚል በጽምጹ እያደመጥን እንዲሁም በጽሁፍም እያየን ቋንቋውን እንድንማር ያስችላል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እንደምን ዋልክ፣ እንደምን ዋልሽ የሚሉትን እና የመሳሳሉትን ሌሎችንም አስፈላጊ የሆኑ መግባቢያዎችንም እንዲሁ በድምጽም በጽሁፍም መማር እንችላለን። ማንበብ ለማይችልም ሰው ድምጹን እየሰማ እንዲማር ይረዳዋል። ‹‹ቋንቋ ስንማር አስፈላጊ የሆኑ ማዳመጥ፣ መናገር፣ ማንበብ እና መጻፍ ያሉ ክህሎቶች ተጠቅመን እንድንማር ያስችለናል። በሰው ልጆች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባባት ሊያግዙ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸውን ቋንቋዎች ቃላትን በማሽን ታግዘን እንድንማር የሚረዳ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ መተግበሪያው በፕሌስቶር (play store) ላይ ከተጫነ ሦስት ወራት በላይ አስቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ 3ሺ ያህል ሰዎች መተግበሪያውን አውርደው በመጫን እየተጠቀሙበት ነው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ለማድረግ በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ መስራት አለበት።

ይህን መተግበሪያ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች የአንድሮይድ (Androied) ተጠቃሚዎች ሆነው ዘመናዊ ስልክ ካላቸው ከፕሌስቶር (play store) ላይ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መማር (learn Ethiopian lan­guage) የሚለውን መተግበሪያ በመፈለግ በስልካቸው ላይ በሚጫኑበት ጊዜ ሁለቱን አገልግሎቶች ያገኛሉ። አንደኛው ቋንቋው የሚያስተምራቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የተናገሩት ወይም በፋይል ያለን ድምጽ ወደ ጽሁፍ የሚቀየርላቸውን አገልግሎት በአንድ ላይ ማግኘት ያስችላቸዋል።

ይህን መተግበሪያ የሚጠቀሙ ቪፔኢን (VPN) አጥፍተው መጠቀም ይኖርባቸዋል። እስካሁን ባለው ሂደት በማንኛውም ሁኔታ ላይ በአንድሮይድ (An­droied) ላይ ይሰራል። በቅርቡ ደግሞ የአፕል (Ap­ple) ምርት የሆኑ ዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎችን እየተጠናቀቁ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም በዌብ ሳይት (wave based) እንዲሰራ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎች እየተጠናቀቁ በመሆኑ በቅርቡ ይለቀቃሉ። በኮምፒዩተርም ሆነ በአይፎን (I Phone) ስልኮች መጠቀም የሚያስችለን ሥራ እየተጠናቀቀ ነው በማለት አቶ ተስፋዬ ያመላከቱት።

እስካሁን ድረስ ኢንስቲትዮቱ በተቻለው መጠን መተግበሪያውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራበት እንዳልሆነ ይናገራሉ። በቀጣይ መተግበሪያውን በማስተዋወቅ ረገድ የሀገራችን ሚዲያዎችም ሆነ ሌሎች አገልግሎቱን የሚጠቀሙ የተሻለ አገልግሎት እያገኙበት ያሉ ሰዎች በስፋት እንዲጠቀሙበት ለማድረግም ሆነ ሌሎችም እንዲጠቀሙበት ለማስቻል የማስተዋወቁ ሥራ በትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

‹‹እንደ ኢንስቲትዩትም ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ትልቅ ሥራ ነው የተሰራው። የሀገራችንን ቋንቋዎች እንደዚህ ለማሽን አስተምሮ መልሶ ማሽን ለሰው ልጅ ትርጉም እንዲሰጥ ማድረግ ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራ ነው። ባለፉት ጊዜያት ይህ ሥራ እንኳን ሊሞከር ሊታሰብ የማይችል ነበር›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ አሁን ላይ ግን በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እውን ሆኗል ይላሉ። ተቋሙ መተግበሪያውን ማስተዋወቅ ላይ ውስንነቶች እንዳሉም ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ከሚዲያ ተቋማት፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከምርምር ተቋማት ጋር በጋራ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ መተግበሪያ በደንብ የተሰራ ዓለም አቀፍ ምልከታዎችን ያካተተ፣ ሳይንሳዊ ትንታኔዎች ታክሎበት የተሰራ ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የዚህን መተግበሪያ ጥቅሙን ሰው በደንብ መረዳትና መጠቀም መቻል እንዳለበት ይጠቁማሉ። በቀጣይ አጠቃቀም ላይ ያሉ ክፍተቶች ካሉ እየታዩ የሚሻሻሉበት ሁኔታ እንደሚኖር ያመላክታሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የአርተፊሻል አንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ትኩረት አድርጎባቸው ከሚሰራባቸው ነገሮች አንዱ ለማሽን የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ማስተማር/machine learn Ethiopian language /natural lan­guage processing/ በሚለው ክፍል ውስጥ በሀገረኛ ቋንቋዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። በቅርቡ የተለያዩ የምርት አገልግሎቶች የሰው ሠራሽ አስተውሎት አቅም ያላቸውን ያዳበሩ ሲስተሞችን ለተጠቃሚው ሕዝብ ተደራሽ ለማድረስ ተቋሙ ዝግጁቱን አጠናቅቋል።

በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው የሚለው አቶ ተስፋዬ፤ ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ወደ ተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግና በተጨማሪም ለሚሰራቸው ሌሎች የምርምር ሥራዎች ማንኛውም ዘርፍ ላይ የሚገኙ ዳታዎችን (መረጃዎች) በመስጠት ባለድርሻ አካላት ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። አሁን ላይ እነዚህን ምርቶች ለማውጣት ዓመታት እየወሰደ ያለው ሥራ መሰራቱን አስታውሰው፣ ከዚያ ባጠረ ጊዜ ውስጥ በፍጥነት መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች ሠርቶ ለማቅረብ ባለድርሻ አካላት መረጃን በማጋራት በኩል ትብብር ቢያደርጉ ሲሉም ጠይቀዋል። ይህም በሀገራችን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ይረዳል በማለት ተናግረዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጅ የሚግባባቸውን ቋንቋዎች ለማሽን በማስተማር የቋንቋውን አድማስ ለማስፋትና ጠቀሜታው እንዲያድግ በተደረገው ጥረት በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። በሀገራችን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥራዎች በጅምር ላይ ያሉ ቢሆንም፣ የተሰሩ ሥራዎች ሊደነቁና ሊበረታቱ ይገባቸዋል። በቴክኖሎጂዎቹ ለመጠቀም ጥረት ማድረግም ያስፈልጋል።

ከቴክኖሎጂ ውጭ መሆን በማይቻልበት ጊዜ ላይ ባለንበት በዚህ ዲጅታል ዘመን ከዘመኑ ጋር መራመድ የግድ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም ሌሎች የሰሯቸውን ቴክኖሎጂዎች ከመጠቀም ባሻገር የራሳችን የምንላቸውን የሀገራችንን አውድና ነባራዊ ሁኔታ መሠረት አድርገው የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ነገ የሚፈጠሩ አዲዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚኖረው መገንዘብ ይገባል።

 ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን መስከረም 22/2016

Recommended For You