የሴቶች ማራቶን ክብረወሰን ከየት እስከ የት?

 ባለፉት ሁለት የዓለም ቻምፒዮናዎች በሴቶች ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት የርቀቱ የሴቶች የዓለም ክብረወሰ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅዋ ገብቷል። በኢትዮጵያ ሴቶች የአትሌቲክስ ታሪክ በዚህ ርቀት ክብረወሰን ሲሰበር ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ይህንን ያሳካችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ ከመላው ዓለም ዛሬም ድረስ አድናቆት እየተቸራት ይገኛል። በተለይም አዲሱ የትዕግስት ክብረወሰን በሴቶች ማራቶን አትሌቶች በታሪክ ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች የማጠናቀቅ ተስፋ ማሳየቱ ዋነኛው ምክንያት ነው። ከዚህ ጋር ታያይዞም የዛሬው የአዲስ ዘመን ስፖርት ማህደር ትኩረቱን በሴቶች የማራቶን ክብረወሰን ሂደት ላይ ያደርጋል።

ከስፖርታዊ ውድድሮች ፈታኙ፣ ከሩጫ ስፖርቶች ደግሞ ረጅም በሆነው ማራቶን አዳዲስ ክብረወሰኖችን ለማስመዝገብ የሚያስፈልገውን ልፋትና የብቃት ጥግ መገንዘብ ቀላል ነው። ታዲያ ከፍተኛ ጽናትና ቁርጠኝነትን በሚጠይቀው በዚህ ውድድር በዓመታት ውስጥ የሚመዘገበው የሰዓት ልዩነት አስደናቂ የሚባልም ነው። ለአብነት ያህል በ19ኛው ክፍለዘመን ወንዶች ማራቶንን ለ3 ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች በሚቀሩት ሰዓት ይሸፈን ነበር። ከመቶ ዓመት በኋላ ግን ይህ ሰዓት ተሻሽሎ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የቀረው 1 ደቂቃ ብቻ ነው። ከዚህም በመነሳት በርቀቱ አዲስ ሰዓት ማስመዝገብ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል።

ይህ ሁኔታ በሴቶች በኩል ሲታይ ግን ሌላ መልክ አለው። ማራቶንን እንዲሮጡ ከመፍቀድ አንስቶ ክብረወሰን እስከማሻሻል ባለው ረጅም ሂደት ሲመዘን ከወንዶቹ አንጻር በእርግጥም ዘርፈብዙ ለውጦች ታይተዋል። ምክንያቱም ወንዶች በኦሊምፒክ ማራቶንን መሮጥ ከጀመሩበት ወደ 100 ዓመታት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ነው ሴቶች ርቀቱን የተቀላቀሉት። አንዳንድ መዛግብት የሴቶች ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንዶች እኩል የመሮጥ ታሪክ የተመዘገበው በቦስተን ማራቶን መሆኑን ያትታሉ። በወቅቱ ለወንዶች ብቻ በተፈቀደው ውድድር ወንድ በመምሰል እንዲሁም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግብግብ በመግጠም ጭምርም ነበር የመጀመሪያዋ ሴት ርቀቱን የሸፈነችው። ይህ ከሆነ ከአምስት ዓመታት በኋላም ሴቶች ከወንዶች እኩል መወዳደር እንደሚችሉ ታምኖበት በኦሊምፒክ እንዲወዳደሩ መደረጉንም መዛግብት ያስነብባሉ።

እውቁ የአትሌቲክስ መጽሔት ራነርስ ወርልድ በበኩሉ በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅናን ያገኘው የመጀመሪያው ውድድርና የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት የተመዘገቡት እአአ በ1926 መሆኑን ያስነብባል። እንግሊዛዊቷ ቫዮሌት ፔርሲ የተሰኘችው አትሌት በወቅቱ ርቀቱን ለመሸፈን የፈጀባትም ጊዜ 3:40:22 ነበረ። ይህ አሁን አትሌቶች ከሚገቡበት ጊዜ አንጻር ሲታይ እጅግ ከፍተኛ ለውጥ ያለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ይሁንና በስፖርቱ ታሪክ የትኛዋ ሴት በየትኛው ውድድር ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሮጠች የሚለውን በትክክል በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ አይቻልም። ምክንያቱ ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት ይደረግ በነበረው የጥንታዊው ኦሊምፒክም ጥቂት ሴቶች የወንዶቹ ውድድር ከተካሄደ በኋላ ይሞካክሩ እንደነበር የተለያዩ ጽሑፎች ስለሚያስነብቡ ነው።

በዘመናዊው ዓለምም ቢሆን በመላው ዓለም ጎልቶ ከሚታወቀው የቦስተን ማራቶኑ ታሪክ አስቀድሞ እንደእነ ፔርሲ ያሉ ሴቶች በተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል። ይሁንና በዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት እውቅና ባለማግኘታቸው ምክንያት ታሪካቸው ከመዳፈኑ ባለፈ ርቀቱን የሸፈኑበት ሰዓትም በትክክል ባለመታወቁ ልዩነቱን ለመረዳት አዳጋች ይሆናል። ኦሊምፒክን እንደ መነሻ ካደረግን ግን እአአ በ1984 በተካሄደው የሎስአንጀለስ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የሴቶች ውድደር በአሜሪካዊቷ አትሌት ጆን ቤኖይት የተመዘገበው ሰዓት 2:24:52 የሆነ ነበር። ነገር ግን ኦሊምፒኩ ከመካሄዱ አንድ ዓመት አስቀድሞ በተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አሸናፊ የነበረችው ኖርዌያዊት አትሌት ግሬቴ ዊትዝ 2:28:09 የሆነ ሰዓት ነበር። ይህ ከሆነ ለ4 አስርት ዓመታት የተጠጋ ጊዜ ቢቆጠርም ግን የሴቶች የማራቶን ሩጫ ከውስን ደቂቃዎች በላይ ለውጥ ሊመጣበት እንዳልቻለ መገንዘብ ይቻላል።

ከ2ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች የሮጡት እአአ 1979 ሲሆን፤ በ2ሰዓት ከ19 ደቂቃ ርቀቱን ለመሸፈን ደግሞ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል። እአአ ከ1970ዎቹ ወዲህ ባሉት ዓመታት አዳዲስ ክብረወሰን የተመዘገበባቸውን ጊዜያት ስንመለከትም እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል። ይኸውም ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በወንዶች በኩል ከሚደረገው ጥረት እና ከፍተኛ ፉክክር አንጻር በሴቶች በኩል ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች ለመግባት የሚደረገው ጥረት እምብዛም ሊባል የሚችል ነው። ይሁንና ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ቀድሞ ከነበረው ሰዓት ወደ 3 ደቂቃ ፈጥና 2:11:53 በሆነ ሰዓት መግባቷ ተስፋ ሰጪ ሆኗል። አትሌቷ ካላት ጽናትና ብቃት አንጻርም ይህ ሰዓት በራሷ ይሻሻላል በሚልም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ይጠበቃል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You