‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች›› የልጆች መጽሐፍ

ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? አዲሱን የትምህርት ዓመት እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? በጥናት እና በንባብ እያሳለፋችሁት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆችዬ ብዙ ጊዜ ስለ ንባብ ጥቅም አውርተናችኋል አይደል? ዛሬ ደግሞ እናንተ ልጆች ብታነቡት ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ነገር እንደምታውቁበት መረጃ ስለያዘው መጽሐፍ የተወሰኑ መረጃዎችን እንሰጣችኋለን እሺ።

ልጆችዬ «ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የሕፃናት መጽሐፍ መስከረም 12 ቀን/2016ዓ.ም ተመርቆ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በአራት ምዕራፍ የተከፋፈል ሲሆን፤ አንደኛው ምዕራፍ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ምትታወቅባቸው ነገሮች፣ ምዕራፍ ሁለት አዲስ አበባ እና በውስጧ የሚገኙ ሐውልቶችን እንዲሁም ሙዚየሞችን አካቷል። ምዕራፍ ሦስት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚዘረዝር ሲሆን፤ የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ ባህላዊ የሆኑ የማይዳሰሱ መስህቦችን በዝርዝር አካቷል። ደራሲው አይነ ስውር ልጆች እንዲያነቡት በማሰብም በብሬል አዘጋጅቷል።

የመጽሐፉ ጸሐፊ መምህርና የሕግ ባለሙያ ሞገስ ጌትነት እንዳሉት፤ ልጆች አካባቢያቸውንና የሀገራቸውን ባህል እንዲያውቁ እና ብዙ ጊዜ የሕፃናት መጻሕፍት ሲጻፉ ተረቶች ላይ ያዘነበሉ በመሆናቸው ታሪካቸውንና ባህላቸውን የሚያስገነዝቡ መጻሕፍትም አስፈላጊ በመሆናቸው መጽሐፉ ተጽፏል።

ወላጆች ልጆቻቸው በሚያነቡበት ወቅት፤ በቅርበት ቢሆኑ ስለሚያነቡት ነገር በመወያየት ግንዛቤያቸው እንዲጨምር ያግዛቸዋል። በተጨማሪም አቅማቸው የሚፈቀድ ከሆነ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን በአቅራቢያቸው የሚገኙትንም የመስህብ ስፍራዎች እንዲጎበኙ እንደሚያግዛቸው ደራሲው አስታውቀዋል።

ወላጆችም ልጆቻቸውን ከቀለም ትምህርት ባለፈ ሁለንተናዊ ዕውቀት እንዲያዳብሩ መጻሕፍትን ለልጆቻቸው ማስነበብ እንዳለባቸው በማስገንዘብ፤ ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩም እንደዚህ ዓይነት መጻሕፍትን በመግዛት ለልጆቻቸው ማስነበብ እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጽሐፉ ምርቃት ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ደራሲ የዝና ወርቁ ታደሰ ደግሞ፤ ታሪኩን የሚያውቅና በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት፤ ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ የሕፃናት መጽሐፍትን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። እናም ልጆች፤ የሕፃናት መጽሐፍትን ለማዘጋጀት ከቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ ልዩ ጥንቃቄና ዕውቀትን በሚጠይቅበት ሁኔታ እና በሥዕላዊ መረጃ አስደግፎ ደራሲው መጽሐፉን ማቅረቡን ጠቁመዋል።

‹‹ሀገር የራሷ መልክ እና ቅርጽ ያላት ሆና የምትቀጥለው በልጆች ነው። ትውልድ ያልፋል፤ ትውልድ ይተካል። በልጆች አእምሮ ተቀርጾ የሚተላለፉ መለያ ማንነታችን እና እሴቶቻችን ናቸው።›› ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ ማንነቱን ያወቀ እና የለየ ትውልድ ለማስቀጠል በጣም ብዙ ስልቶችን መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል። ‹‹በቤተሰብ ውስጥ የሚከወን ሥነ ቃል፣ ተረት እና ለልጆች ታሪክን መንገር የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ አብዛኛው ወላጅ (አሳዳጊ) ለልጁ ‹‹ተረት ተረት›› የመነገር ችሎታ የለውም። ከችሎታ ባለፈም ጊዜም የለውም። ስለዚህም ይህንን ኃላፊነት መወጣት የሚቻለው የሕፃናት መጽሐፍትን በማዘጋጀት ነው። በራሳቸው የሚተማመኑ ሀገራቸው እና ወገናቸውን የሚወዱ በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጋ ለማፍራት የሕፃናት እና የታዳጊዎችን መጽሐፍት ማሳተም መተኪያ የሌለው ዐቢይ ሥራ ነው›› ሲሉ ለልጆች የሚታተሙት መጽሐፍት ትኩረት አናሳ እንደሆነ እና ትውልድን በሥነ – ጽሑፍ መቅረጽ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ልጆችዬ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የልጆች መጽሐፍ የተጻፈው ጥቅምት 16 ቀን/ 1916 ዓ.ም ሲሆን፤ መቶ ዓመት ሊያስቆጥር ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት። ‹‹የፍቅር መላዕክት ለኢትዮጵያ ልጆች›› በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ በበቀለ ሀብተ ሚካአል ሲታተም፤ አንድነት ኃይል እንደሆነ፣ ስለጊዜ ጥቅም፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በማስተዋል እና በጥበብ መፍታት እንደሚገባ የሚያመላክት እንደሆነ ሥራ አስኪያጇ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን መጽሐፍ የሚያነቡ እና ለልጆች መጽሐፍ የሚገዙ ወላጆች ቁጥር አናሳ ነው። ስለዚህም ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና እውቀቱን በመጠቀም የትውልድ ኃላፊነቱን ለተወጣው ደራሲ ምስጋናቸውን በማቅረብ፤ ሥነ ጽሑፍ የሰዎችን አእምሮ በማዝናናት እና በማስተማር መልካም አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ለማገዝ ድርሻ እንዳለው የዝና ወርቁ አስረድተዋል።

ደራሲ እና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤ ደራሲው ‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች›› የተሰኘው መጽሐፍ፤ ልጆችን በሚመጥን መልኩ መዘጋጀቱን በመግለጽ፤ እንደዚህ ለልጆች ስለ ሀገራቸው የሚጻፉ መጽሐፍት ልጆች ስለሀገራቸው ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ ያደርጋሉ ሲሉ ገልጸዋል። አሁን ላይም ልጆች ላይ መሥራት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንደምንገኝም ጠቁመዋል።

ልጆችዬ በመጽሐፉ ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ኮሜድያን አስረስ በቀል (ቼሪ) ይጠቀሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት ደራሲው ልጆች ኢትዮጵያን በሚጣፍጥ፣ አጭር እና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያውቁት አዘጋጅቶታል። ይህን ዓይነት ሥራ በማቅረቡ የሚያስመሰግነው እንደሆነ በመግለጽ፤ የልጆች ንባብ እንዲስፋፋ ትምህርት ቤቶች የልጆች መጽሐፍትን በመግዛት የንባብ ባህል እንዲዳብር መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You