በሙዚቃው ‹‹ኦሴ ባሳ›› የሚጠራው አቀንቃኝ

እናቱና አባቱ ተስማምተው በሀገር ወግ መጠሪያ እንዲሆነው ያወጡለት ሥም ጸጋዬ ይሰኛል። ሙሉ መጠሪያው ጸጋዬ ሥሜ። ድምጻዊ የግጥምና ዜማ ደራሲነት ደግሞ የተሰጠው መክሊቶቹና መተዳደሪያው ናቸው። በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቅርቡ በአዲስ አደረጃጀት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል በተደራጀው ክልል ውስጥ ሶዶ ወረዳ ኑረና ጎርጊዜ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የትውልድ ቦታው ነው።

የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ መኖሪያውን ከተወለደበት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ በመቀየር በቄስ ትምህርት ቤት የፊደል ጉዞውን ሀ ብሎ ጀመረ። ገሊላ ትምህርት ቤት፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል እውቀት የቀሰመባቸው ትምህርት ቤቶቹ ናቸው። በመቀጠል ባመራበት አዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል። በጄነራል ዊንጌት ለአራት አመታት የጂኤም ትምህርቱን ተከታትሎ ዲፕሎማ አግኝቷል።

ግን በዚህ ሁሉ የትምህርት ቤት ቆይታው ጸጋዬና የክበባት ተሳትፎ ጭራሽ አይተዋወቁም። የእሱ ዋና አላማ ትምህርት ተምሮ በተማረው ትምህርት ሀገሩን ማገልገል ነበር። በሰፈርም በትምህርት ቤት አካባቢም ትርፍ ሰዓት ሲያገኝ እግር ኳስ መጫወት ያስደስተዋል። ሰፈር ውስጥ በሚደረጉ ሠርግና መሰል ዝግጅቶች ልቡ እስኪጠፋ ይጨፍራል። ዘፈን ለመዝፈን አስቦም አልሞም አያውቅም። በቃ ድግስ ካለ እሱ በጭፈራ የዚያ ድግስ አድማቂ ነው። ለመተዳደሪያ ደግሞ የተማረበት የሥራ መስክ ላይ ይሰማራል፤ እቅዱም ህልሙም ፍላጎቱም ይህ ነበር።

ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ የአዲስ አበባ ነዋሪ ቢሆንም በየክረምቱ ወደ ትውልድ አካባቢው መሄድ የዓመት ከዓመት ልማዱ ነው። በጋ በአዲስ አበባ ትምህርቱን ሲከታተል ይቆያል ክረምት ላይ በመደበኛነት ሀገር ቤት ይገባል። እዚያ እንደልቡ ይጫወታል ከጨዋታ በዘለለም የክስታንኛ ቋንቋውን አዳበረ። አዲስ አበባ ሲመለስም በተደጋጋሚ ቋንቋውን የሚችሉ ሰዎችን እየፈለገ ስለሚያወራ መለያ ሥሙ ‘ጸጋዬ ክስታኔው’ ሆነ።

በ1982 ዓ.ም ከዊንጌት መመረቁን ተከትሎ ከቤተሰብ ጫና በመውጣት የራሱን ገቢ ለማመንጨት ጓጉቷል። በሀገሪቷ የለውጥ ወቅት አየሩን ተቆጣጥሮታል፤ እሱ ግን እራሱን ሊችል ስለሆነ ሃሳቡ በሙሉ እራስ መቻል ላይ ነበር። ከተማረበት ትምህርት ቤት ሥም ዝርዝራቸው ተወስዶ በአምቦ የጦር መሣሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ እንደሚጀምሩ ተነግሯቸው ልቡ ጮቤ ረግጧል። ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ የቤተሰብ ደጀን ሆኖ የታናናሾቹ መከታ ሊሆን ተዘጋጅቷል። እሱን ያዩ ታናናሾቹ በሱ ፈለግ እንደሚከተሉ በማሰብ ተደስቷል።

ግን ይህ ሁሉ ጮቤ መርገጥ ሳይሰምር ቀረ። የዚህ ምክንያቱም ሹፌር የነበሩት ወላጅ አባቱ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ምን ሲደረግ መሣሪያ ፋብሪካ ትቀጠራለህ አይሆንም አሉ። የዚህ ምክንያታቸው የመሣሪያ ፋብሪካዎች በግጭት ወቅት ጥቃት ይደርስባቸዋል ብለው በመስጋት የበኩር ልጃቸውን እንዳያጡ መፍራታቸው ነው። የኔን ደመወዝ አካፍልሀለሁ እንጂ እያየሁ ለሞት አልክህም በማለት ልጃቸውን በአዲስ አበባ ለማቆየት ወሰኑ።

ክስታኔኛ በደንብ መቻሉ ጠቅሞት የክስታኔ ልማት ማኅበር በክስታንኛ ቋንቋ በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት መሥራት ጀመረ። ታዲያ ያኔ የማኅበሩ አባል የነበሩትና በዘርፉ የዳበረ ልምድ ያላቸው ተክሉ ታቦር በጋዜጠኝነት ለመሰማራት እንዲያስችለው ለአንድ ሳምንት የጋዜጠኝነት ሥልጠና ሰጥተውታል። ጸጋዬ ክስታንኛ በደንብ ይችላል፤ በክስታንኛ ግጥም ይጽፋል፤ ዘፈኖችን ያንጎራጉራል። ግን ‹‹አንድም ቀን ዘፋኝ እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር›› ይላል።

በ1988 ዓ.ም የዋለው የፋሲካ ዋዜማ ግን ከሌሎች የበዓል ሰሞኖች ሁሉ ይለያል። ከጓደኞቹ ጋር ሰብሰብ ብለው ለመዝናናት በማሰብ አብነት አካባቢ የሚገኝ የምሽት ክበብ ይገባሉ። ዕለቱ የበዓል ዋዜማ ነውና ቤቱ በሰው ተሞልቷል። ጸጋዬና ጓደኞቹ እንደሌሎቹ ተዝናኞች ከምግቡም ከመጠጡም እየወሰዱ ዘና ብለዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በቤቱ የሙዚቃ ባንድ መኖሩ ተመችቷቸዋል።

በሙዚቃውም በመጠጡም እየተዝናኑ ነው። በዚህ መሃል የጉራጊኛ ዘፈን ሊዘፍን አንድ ልጅ ወደመድረክ ይወጣል። ልጁ ቋንቋውን በደንብ ባለማወቁ በትክክል እየዘፈነው አይደለም። በዚህ የተናደደው ጸጋዬ ልጁ ከመድረክ ሲወርድ ጠብቆ የዘፈነው ቋንቋ ትክክል አለመሆኑን ይነግረዋል። ከፈለገ ትክክለኛውን ግጥም ሊጽፍለት እንደሚችል ቃል ይገባለታል። በመሃል ለምን እኔ አስተካክዬ አልዘፍነውም በሚል ወኔ መድረክ ላይ ይወጣል።

ከታዳሚነት ወደ ዘፋኝነት ተሸጋግሮ እራሱን መድረክ ላይ ተበላሸ ያለውን ዘፈን ሲያስተካክል ያገኘዋል። አንድም ቀን ሳይለማመድ ለልምምድ ለባለሙያ ሳይዘፍን በመሣሪያ ተጫዋቾች ታጅቦ ለታዳሚዎች ሙዚቃን አቀረበ። ምንም እንኳን ‹ፒች ኪይ› የሚባሉ የሙዚቃ ጽንሰ ሀሳቦች ለሱ ሩቅ ቢሆኑም የአርጋው በዳሶን ዘፈን በሙዚቃ መሣሪያ ታጅቦ ዘፈነ።

ቤቱን የሞላው ታዳሚ ጸጋዬን በሽልማት አጥለቀለቀው። ከሽልማቱ በዘለለም ሁሉም ታዳሚ ብላልኝ ጠጣልኝ ባዩ ሆነ። ዘፈኑንም በታዳሚ ምርጫ በድጋሚ ዘፈነ። ያላሰበውን ሽልማት ተቀብሎ ኪሱን ሞልቶ ወደ ቤቱ ሊጓዝ ሲነሳ፤ የቡና ቤቱ ባለቤትም የቤታቸው ታዳሚ ሲደሰት ተመልክተዋልና እባክህ ነገ ና እንዳትቀር ሁሉን ወጪህን እኔ እችልሀለሁ ሲሉ አግባቡት።

በማግስቱ «የኔ ጌታ መአረይ ባክህ እንዳትቀር» ሲሉ የተማጸኑትን የቤቱ ባለቤትን ልመናና ሽልማቱን አስታውሶ በዕለተ ፋሲካ ማምሻውን ሄደ። በማግስቱም የታዳሚው አቀባበል ለየት ያለ ቢሆንበት በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ «ይሄ ነገር እንጀራዬ ይሆን እንዴ?» ሲል አሰበ። ሆኖም የዘፈን ጥናት ልምድ የለውምና ይደገም ቀርቶ ይሰለስ ቢባልም የሚያውቀውም ሆነ የሚዘፍነው ብቸኛ ዘፈን የአርጋው በዳሶ አለምብሬን ብቻ ነበር።

በወቅቱ የጸጋዬ ድምጻዊነት ከሁለት ቀናት አልዘለለም ነበር። ያም ቢሆን አብነት አካባቢ በርካታ የጉራጌ ማኅበረሰብ ስለሚኖር ጉራጊኛ የሚዘፍን ልጅ ያለበት ቤት እያሉ ሁለት ቀን የዘፈነበት ቤት ቢያመሩም ጸጋዬ ግን ሊገኝ አልቻለም። ሲያገኙትም የት ጠፋህ የሚሉት አድናቂዎች ያፈራበት የሁለት ቀን ቆይታ አድርጓል። በየመንገዱ የሚጠይቁትን ኧረ እኔ አልሠራም ለበዓል ነው የዘፈንኩት እያለ ይመልሳል። በወቅቱ በክስታንኛ ቋንቋ የሚሠራበትን የህትመት ሚድያ ማጥበቅ ምርጫው አድርጓል። በልማት ማኅበሩም የቢሮ ሠራተኛ ሆኖ ተቀጥሮ እየሠራ ነው።

በልማት ማኅበሩ አማካኝነት የክስታኔ ባንድ ሲቋቋም ከመሥራች አባሎች መሃል አንዱ ሆነ። ባንዱ ከጸጋዬ ስሜ ባሻገር ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አብነት አጎናፍርና ሌሎችም በርካታ ሙዚቀኞችን አቅፎ ሥራ ጀመረ። ጸጋዬ የጉራጊኛ ዘፋኝ በመሆን ባንዱን ተቀላቀለ፤ ለሱም የኪነጥበብ መንገድ ተጀመረ። እንሾሽላ ሠርግ መልስ ሲባል አብዛኛውን ቀን የሥራ ቀናቸው እንደነበርና በሳምንት ረቡዕን ብቻ ያርፉ እንደነበር ያስታውሳል።

ጸጋዬ ችላ ካላት መክሊቴ ብሎ ብዙም ዋጋ ካልከፈለላት ሙዚቃ ጋር በባንዱ አማካኝነት በደንብ ተግባብቷል። መድረክና ዝግጅት ላይ ከመሥራት በዘለለም ክስታኔ ሲሉ የሰየሙትን የመጀመሪያ አልበማቸውን በባንዱ አማካኝነት ሦስት ድምጻውያን ተጣምረው ለአድማጭ እንካችሁ አሉ። አልበሙ ሙሉ የሙዚቃ መሣሪያ ገብቶበት የተቀረጸ ሲሆን የአልበሙ አብዛኛው ክፍል የተቀናበረው የባንዱ ኪቦርዲስት በነበረው ድምጻዊ አብነት አጎናፍር ነበር።

ጸጋዬ ክስታኔ ባንድ እየሠራ ነጠል ብሎ ለብቻው ሁለተኛ አልበሙን አወጣ። የሕዝቡ ተቀባይነት እየጎላ ሲመጣና በየቦታው ፈላጊው ሲበዛ ከባንድ ተቀጣሪነት ወደ ባንድ ባለቤትነት ተሸጋገረ። የራሱን ባንድ ‹እስኝታ› ባንድ ሲል መሠረተ። ያም ቢሆን የመጀመሪያውንና ባለውለታውን የማይረሳው ድምጻዊ ክስታኔ ባንድ ዛሬ ባይኖርም ከሕዝብ ጋር ያስታዋወቀኝ ባለውለታዬ በማለት ያስታውሰዋል።

በ1996 ዓ.ም ጳጉሜ አራት የወጣው የጸጋዬ ሦስተኛ አልበም የሙዚቃውንም ሆነ የሕይወቱ ማርሽ ቀያሪ አልበም ነው። የአልበሙ መጠሪያ እንሾሽላ ሲሰኝ የድምጻዊው መጠሪያ እስኪሆን የታወቀበት ኦሴ ባሳ የተሰኘው ሙዚቃ የተካተተበት ነው። ድምጻዊው ‹‹ኦሴ ባሳ ከጉራጌ ማኅበረሰብ አልፎ በመላው ኢትዮጵያውያን እንድታወቅ ያደረገኝ ዘፈን ነው›› ይላል።

«መጠሪያዬ በኦሴባሳ መተካቱን አድናቆት ስለሆነ እቀበለዋለሁ እንጂ ቃሉ ለሰው ልጅ አይሆንም።» በማለት ኦሴባሳ ትርጉሙ ነውር ነው ማለት እንደሆነ ያስረዳል። በወቅቱ ብዙ ነውር የሆኑ ነገሮችን በማስተዋሉ ነውር ነው ለማለት በድፍረት የጻፈውና የተጫወተው ዘፈኑ ነው። በዘፈኑ የሚያየውና የሚሰማው ነገር በሙሉ አስቀያሚ ነገር መሆኑን ይጠቅሳል።

ድምጻዊው በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ሴት ልጅ ሳታገባ ካረገዘች፣ ስርቆት ካጋጠመ፣ ባጠቃላይ መሆን ያልነበረበት ነገር ሲሆን ከታየ ትልልቅ ሰዎች ‹‹ይሄ ኦሴባሳ ነው›› እንደሚሉና የማውገዣ ቃል መሆኑን ያነሳል። በዘፈኑ ጆሮዬ መጥፎ ነገር አትስማ ሲል መክሮበታል። ኦሴባሳ መውጣቱን ተከትሎ ጸጋዬ በርካታ የሥራ አማራጭ የተሻለ ገቢ እንዲሁም የሕዝብ ፍቅርና እውቅና ያገኘበት ሥራው ነው። ሥራውን የሕይወቴ ለውጥ ይለዋል። ሥራው 20 ዓመት ቢጠጋውም አሁንም መድረክ ላይ በወጣ ቁጥር ሁሉ ኦሴባሳን ሳይዘፍን መውረድ የማይታሰብ መሆኑን ይናገራል። ታዳሚው ቀድሞ ኦሴባሳ ይላል። ጸጋዬን ያየ ታዳሚ ኦሴባሳን እንደሚሰማ እርግጠኛ ይሆናል።

ዬሻለ የተሰኘው አራተኛ አልበሙን በ2000 ዓ.ም ለአድማጭ አድርሷል። በ2005 ዓ.ም የወጣው ‹ጥምቡስ አሳብ› አምስተኛ አልበሙ ሲሆን፤ የመጨረሻው አልበሙ ‹ሱታና› ይሰኛል። ድምጻዊው በሀገር ውስጥ በበርካታ ከተሞች ተዘዋውሮ ሥራዎቹን አቅርቧል። በባህር ማዶም በጀርመን ፍራንክፈርትና ሙኒክ ላይ ሥራዎቹን አቀንቅኗል። ባህሬን፣ ኳታር፣ ዱባይ ኤርትራ ታዳሚዎቹን አዝናንቷል።

እንደ ሙዚቃ ሕይወቱ ሁሉ የሰመረ ትዳር አለው። የትዳር አጋሩን የተዋወቃት ሙዚቃ ጥሪው መሆኗን ሳያውቅ በዊንጌት ትምህርቱን ሲከታተል ነው። ያኔ እሷም በትምህርት ቤቱ የአካውንቲንግ ተማሪ ነበረች። የያኔ የፍቅር ጓደኛው የአሁን የትዳር አጋሩ አስቴር ታደሰ። በተማሪነት ዘመናቸው የተጀመረው ፍቅር ወደ ጋብቻ ሳያመራ ድፍን አስር ዓመት በፍቅር ጓደኝነት ቆይተዋል። ሁሉን አደላድለው የጀመሩት ትዳር በፍሬ ተባርኮ የአንድ ሴት ልጅ ወላጆች ሆነዋል።

በቡታጅራ መስመር በምትገኘው ቡዒ ከተማ የገነባው ኦሴባሳ ሆቴል ተመርቆ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ተሻግሯል። በቀጣይነት ለኑሮ መደጎሚያ ከሱ የሙዚቃ ሥራና ከባለቤቱ መደበኛ ሥራ ተጨማሪ ደጓሚ እንደሚሆናቸው ተስፋ አድርጓል። ድሮ ክትፎ ዋነኛ የምግብ ምርጫው ነበር። ዕድሜ ጨመር እያለ መሄዱን ተከትሎ የምግብ ምርጫው በጎመን ክትፎና በአይብ ተተክቷል። ሁሉንም ሥራዎቼን እወዳለሁ የሚለው ድምጻዊው አጥብቆ ለጠየቀው ግን ‹‹ኸዲስ ባለአገር ነውን›› የተለየ እንደሚወደው ምስጢር ያወጣል።ኸዲስ ባለአገርነው (እኔ ባላገር) ኦሴባሳ የሚገኝበት ሦስተኛ አልበሙ ላይ የተካተተ ሥራው ሲሆን አስተዳደጉን የሚገልጽበትና አሁንም ባላገር ነኝ የሚልበት ተወዳጅ ዘፈኑ ነው።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን  መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You