የመጀመሪያው የዓለም የጎዳና ላይ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነገ ይካሄዳል

የዓለም አትሌቲክስ ከቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮና ማግስት ፊቱን ወደ ዓለም የጎዳና ላይ ውድድር መልሷል። በላቲቪያ ሪጋ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ ውድድሮች ቻምፒዮ ነገ ይካሄዳል። ለአንድ ቀን በሚቆየው ውድድር ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ አትሌቶች የሚፎካከሩ ይሆናል። ከእነዚህ አትሌቶች መካከልም ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሔራዊ ቡድን በርካታ ሜዳሊያዎችን ይሰበስባል ተብሎ ተገምቷል።

በውድድሩ ከ57 ሀገራት የተወጣጡ 347 አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን በ 1 ማይል፣ በ 5 ኪሎ ሜትር እና ግማሽ ማራቶን ፉክክሮች ይደረጋሉ። ከዓለም ቻምፒዮና እና ከዳይመንድ ሊግ መልስም በጎዳና ውድድሮች ስኬታማ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካን ጨምሮ ከሌሎች ዓለማት የተወጣጡ አትሌቶች ወደስፍራው አቅንተዋል። ኢትዮጵያ የሚወክለው ቡድንም ሽኝት ተደርጎለታል።

13 አትሌቶችን ካካተተው የኢትዮጵያ ቡድን መካከል 7ቱ ሴቶች እንዲሁም 6ቱ ወንድ አትሌቶች መሆናቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በአንድ ማይል ውድድር ታደሰ ለሚ በወንዶች የሚወዳደር ሲሆን፤ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ በሴቶች ኢትዮጵያን በዚሁ ርቀት የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው። በ5 ኪሎ ሜትር ወንዶች በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም በዳይመንድ ሊግ ተሳታፊ የነበሩት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሐጎስ ገብረህይወት ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተሳታፊዎች ናቸው። በሴቶች በኩልም እጅጋየሁ ታዬ እና መዲና ኢሳ በዚህ ርቀት የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው። በዚህ ቻምፒዮና ረጅሙና ከዚህ ቀደም ከውድድር ተሰርዞ የቆየው ርቀት ግማሽ ማራቶን ሲሆን፤ አትሌት ጀማል ይመር፣ ንብረት መላክ እና ጸጋዬ ኪዳኑ በወንዶች በኩል የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው። በሴቶች በኩል ደግሞ ጽጌ ገብረሰላማ፣ ያለምጌጥ ያረጋል እንዲሁም ፍታው ዘርዬ ሃገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች ይሆናሉ።

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የመም እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የጎዳና ላይ ልምምድ ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይተል። ይህንንም ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት አትሌት ጀማል ይመር እና አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና በግልም ሆነ በቡድን ጥሩ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል። አሰልጣኝ ጌታመሳይ ሞላ በበኩላቸው ሁሉም አትሌት በግሉ እረፍት ሳይኖረው ልምምድ ላይ ነው። በመሆኑም ቡድኑን የሚወክሉት አትሌቶች ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ጥሩ የሚባልና ባላቸው ልምድ ታግዘው ጥሩ ውጤት ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባላቸው ሰዓት መመረጣቸውንና ጥሩ ተፎካካሪዎች በመሆን ሜዳሊያ እንደሚያመጡ የጠቆሙት ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ቡድን መሪ አቶ ብስራት ለጥይበሉ ናቸው። የቡድን መሪው ዶክተር ተስፋዬ አስገዶም በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ የቡድን መሪ አድርጎ ኃላፊነት ስለሰጣቸው በማመስገን ‹‹በሰላም ሄደን ሜዳሊያ ይዘን እንድንመለስ ሁሉም ከጎናችን እንዲሆን እጠይቃለሁ›› ብለዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉም ከቀናት በፊት በ5ሺ እና በማራቶን የዓለም የሴቶች ክብረወሰንን የሰበሩትን አትሌቶች ጨምሮ ብሔራዊ ቡድኑን አበረታታለች። አክላም የላቲቪያ አገር ተወካይ የኦስትሪያ ኤምባሲ ከቡድኑ መካከል ለአራት አባላቱ ቪዛ መከልከሉን አንስታለች። ነገር ግን እስከመጨረሻው ፌዴሬሽኑ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግም አስረግጣለች። በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትም ቡድኑን አበረታተዋል። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ኩራት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ‹‹ሁሌም ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋን በልባችሁ አትማችሁ ምንም ዓይነት የማይመች ሁኔታ ቢገጥማችሁም በጽናት ታግላችሁ እንደምታሸንፉ ጽኑ እምነት አለኝ›› ሲሉ ለቡድኑ ንግግር አድርገዋል። ስለተፈጠረው የቪዛ መከልከል ችግርም እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተቻለውን እንደሚያድጉም ገልጸዋል።

በቻምፒዮናው ላይ ተካፋይ ከሆኑ ቡድኖች መካከል ስኬታማ ይሆናሉ በሚል ከሚጠበቁት አትሌቶች ኢትዮጵያውያኑ ቀዳሚ መሆናቸውን ትኩረታቸውን በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ያደረጉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በተለይም በቅርቡ በተጠናቀቀው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም በኦሪጎኑ ዳይመንድ ሊግ የተሳተፉና ዓመቱን በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶች በጎዳና ውድድሩ ሌላኛውን ስኬት እንደሚያጣጥሙም ይጠበቃል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You