ጫላ ባይሳ ይባላል። በ1982 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አቡና ግንደበረት ወረዳ ገርቢ ጎሌ ቀበሌ ልዩ ቦታው ገርቢ በተባለ አካባቢ ተወለደ። እናቱ ወይዘሮ ቀበኖ መርጋም ሆኑ አባቱ አቶ ባይሳ ዱፋ ሕልማቸው ልጃቸው ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ነበር።
በዛው አካባቢ ከአንደኛ ክፍል እስከ አስረኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትሎ፤ በ1999 ዓ.ም አጠናቋል። በ2000 ዓ.ም የአስራ አንደኛ ክፍል ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ፤ በ2001 ዓ.ም ወደ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተሸጋግሮ መማር ሲጀምር የጉጂ ዞን ጤና ፅህፈት ቤት ያወጣውን የሥራ ማስታወቂያ ተመለከተ።
ከ2002 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም በነርስ ሞያ ትምህርቱን ተከታትሎ ሲጨርስ፤ ቦረና ዞን ሂዱሎላ ወረዳ ጤና ጣቢያ ተመድቦ በሞያው የአካባቢውን ሕዝብ ማገልገል ጀመረ። በዛው በጤና ጣቢያው ለሁለት ዓመት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ፤ በ2006 ዓ.ም በገዛ ፍቃዱ ሥራውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ ገባ። አዲስ አበባ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በዲግሪ ደረጃ ለመመረቅ ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም ቢማርም ሳያጠናቅቅ አቋረጠ።
ጫላ ራሱ በሰጠው የምስክርነት ቃል ላይ የሕይወት ታሪኩን ሲዘረዝር፤ በወቅቱ በቄሮ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ ሲጀምር ትምህርቱን አቋርጧል። በኋላ በ2011 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብቶ ያቋረጠውን ትምህርት አጠናቋል።
ደህንነት ነኝ በሚል ስም ማታለል
በ2011 ዓ.ም ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ጫላ አዲስ ሃሳብ አመነጨ። የደህንነት ሰው እንደሆነ እና ብዙ ሰዎችን እንደውም በትልልቅ የኃላፊነት ደረጃ ያሉ ሥመ ጥር ሰዎችን እየጠቀሰ፤ አንዳንዴ ደህንነት እንደሆነ ሌላ ጊዜ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤት ዳኛ መሆኑን ሌላ ጊዜ ደግሞ አቃቤ ሕግ መሆኑን እየገለፀ ማታለል ጀመረ።
በ2011 ዓ.ም የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው ዘፍመሽ ግራንድ ሞል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጫላ አቶ ብርሃኑ ዳኛቸውን ያገኛቸዋል። ባይተዋወቁም ለአንዳንድ ነገር እንተዋወቅ እና እንደዋወል በማለት ስልክ ቁጥር ይቀያየራሉ። ጫላ ወጥመዱ ስር ካስገባቸው በኋላ ሁለት ቀን አሳልፎ ይደውልላቸዋል። በአካል ቢገናኙ ሊጠቃቀሙ እንደሚችሉ አሳምኖ ይቀጥራቸዋል። ሲገናኙ የደህንነት አባል መሆኑን ቢሮውም የዋናው ደህንነት ቢሮ መሆኑን በመጥቀስ አሳሳች መታወቂያ ያሳያቸዋል።
ጫላ አቶ ብርሃኑ እምነት እንዲያድርባቸው ማድረግ ቻለ። በሥራው ምክንያት ለገጣፎ 500 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሠጠው አስመስሎ ተናገረ። እርሳቸው ካገዙት 250 ካሬ ሜትሩን እንደሚሰጣቸው ገለፀ። ነገር ግን ካርታ እንዳልተሠጠው እና ለካርታ ማሠሪያ 3ሺህ 400 ብር ብቻ ጠየቃቸው። አቶ ብርሃኑ በኤ ቲ ኤም ገንዘቡን አውጥተው ሰጡት። ከሳምንት በኋላ እንገናኝ በማለት በድጋሚ ደወለላቸው።
ጫላ በድጋሚ ለአቶ ብርሃኑ፤ ታማኝ መሆኑን በሚያስመስል መልኩ የኦሮሚያ መሬት አስተዳደር ኃላፊ ዶክተር ሚልኪሳ አዳማ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ 250 ካሬውን ሕጋዊ አድርጎ ለማስፈፀም በአቶ መስፍን ጌታቸው ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 24 ሺህ ብር እንዲያስገቡ ይነግራቸዋል።
አቶ ብርሃኑ የተነገራቸውን ቃል ተስፋ አድርገው ገንዘቡን ገቢ አደረጉ። ነገር ግን ከዛ በኋላ በፍፁም ጫላን ማግኘት አልቻሉም። ገንዘቡን ገቢ ያደረጉበትን የባንክ ሒሳብ ቁጥር፤ የገንዘቡን መጠን፤ አታላዩ ግለሰብ ማን እንደሆነ፤ በምን መልኩ እንዳታለላቸው ዘርዝረው ለፖሊስ ጣቢያ አመለከቱ።
ጫላ ማታለሉን አላቆመም፤ በድጋሚ በመጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 በአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ጉዳይ ለማስፈፀም ይመላለሱ የነበሩ አቶ ዮሴፍ ማሞ የተሰኙ ሰውን ተዋወቀ።
ጫላ ልክ አቶ ብርሃኑ ላይ የፈፀመውን ተመሳሳይ ድርጊት አቶ ዮሴፍ ላይም ፈፀመ። የአቶ ዮሴፍን ለየት የሚያደርገው ለማታለል የሞከረው መሬት አሰጣለሁ ወይም እሰጣለሁ በሚል መልኩ ሳይሆን፤ የደህንነት አባል በመሆኔ ጉዳይህን አስፈፅምልሃለሁ የሚል ነበር። ግለሰቡን በተለያየ ጊዜ ገንዘብ በመጠየቅ ጫላ ከአቶ ዮሴፍ ላይ በአጠቃላይ 94ሺህ ብር የተቀበለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ጫላ በድጋሚ ቀኑና ወሩ ባልታወቀ እና በውል ባልተገለፀ ጊዜ በ2013 ዓ.ም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ኦሎምፒያ ፒኤል ሲ ትሬዲንግ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአቶ አሸናፊ ሃብቴ ልብስ እና ጫማ መሸጫ ሱቅ ተገኘ። የሱቁ ባለቤት ከሰራተኛው ጋር ሲያወራ ጫላ ጣልቃ በመግባት የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሆኑን ከመንግስት ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳለው ገልፆ፤ ማንኛውም ችግር ቢያጋጥማቸው እርሱ የሚፈታላቸው መሆኑን አስረዳ።
ችግር ፈቺ ነኝ ባዩ ጫላ በማንኛውም ጊዜ እረዳችኋለሁ በማለት በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ሙሉ ልብሶችን፣ የተለያዩ ጫማዎችን፣ ቀበቶ እና ከረቫትን ጨምሮ በአጠቃላይ ዋጋቸው 48 ሺህ ብር ሊያወጡ የሚችሉ አልባሳትን በነፃ ከሱቅ እያታለለ ወሰደ።
በጥር 2013 ዓ.ም በተጨማሪ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ኤቢሲ ትሬዲንግ አካባቢ ባለው ቶኩማ ምግብ ቤት ተገኝቶ በተመሳሳይ መልኩ አቶ ወንድሙ ደበላ ከሚባሉ ሰው ጋር ይተዋወቃል። እንደተለመደው ትውውቁን በማጠናከር የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሆነ አስመስሎ በመቅረብ፤ ለአቶ ወንድሙ ‹‹ዳያስፖራ እንደሆንክ ጠቅሼ መሬት በህጋዊ መንገድ አሰጥሃለሁ፤ አንተ ደግሞ ለመሬቱ ካሳ የሚሆን ገንዘብ ትከፍላለህ። ›› በማለት አቶ ወንድሙ ደበላ እንዲያምኑት አደረገ።
አቶ ወንድሙ መሬቱን አገኛለሁ ብለው በመጓጓት መጀመሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአቶ ጫላ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 60 ሺህ ብር አስገባ። በመቀጠል ለትራንስፖርት እና ለአንዳንድ ጉዳይ ለማስፈፀም በሚል 10 ሺህ ብር ሰጠ። በኋላም ተጨማሪ 20 ሺህ ብር እንዲሰጥ በመጠየቁ የተባለውን ገንዘብ አቀበለ። በመጨረሻ ግን የተገባለት ቃል ውሃ በላው። ጭራሽ አቶ ጫላም ተሠወረ። አቶ ወንድሙ የቶኩማ ምግብ ቤት ባለቤትን ጠየቀ። የሆቴል ቤቱ ባለቤት ጫላ የሆቴሉ ደንበኛ ከመሆን እና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ነኝ ሲል ከመስማት ውጪ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናገሩ።
ጫላ እጠነቁላለሁ በማለት ረሃብ እና በሽታ እንዳይመጣባችሁ ይህንን አድርጉ፤ ያንን ፈፅሙ እያለ ሲያታልል ነበር የሚል ተደራራቢ የማታለል ወንጀል ፈፅሟል የተባለ ሲሆን፤ ግለሰቡ አታላይ ነው መባሉን ተከትሎ ፖሊስ አሳዶ በመያዝ ምርመራ ጀመረ።
የፖሊስ ምርመራ
የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ለማደራጀት ምርመራ የጀመረው ፖሊስ ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ማስረጃ ጠየቀ። ጫላ ባይሳ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተንቀሳቀሰ የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ እንደሆነ በመንገር በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መሬት አሰጣችኋላሁ፤ ለጉዳይ ማስፈፀሚያ የሚውል ገንዘብ ስጡኝ በማለት የተቀበላቸው እና መሬቱን ባለመስጠቱ ወደ ሕግ ለመሔድ ሲንቀሳቀሱ የሸኔ ቡድንን በገንዘብ እና በቁሳቁስ ይደግፋሉ ብዬ አሳስራችኋላሁ ማለቱን ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሠረት ምርመራውን እያጣራ እንደሚገኝ እና የተጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ይረዳ ዘንድ ግለሰቡ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አባል መሆን አለመሆኑን በተመለከተ አጣርቶ መልሱ በአስቸኳይ እንዲሰጠው የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ማስረጃ ጠየቀ።
የደህንነት አገልግሎቱም ግለሰቡ የያዘው እና አቅርቦ የነበረው መታወቂያ ሐሰተኛ መሆኑን ጫላ አባል አለመሆኑን ጠቅሶ ለቀረበለት ጥያቄ ምለሽ ሰጠ። ፖሊስ ሶስት የሠው ምስክሮችን ቃል በማስረጃው ላይ ዘርዝሮ እና ተከሳሽ ጫላ፤ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አባል አለመሆኑን በተመለከተ የተሰጠውን ምላሽ አካቶ እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገባ የሒሳብ ደረሰኝን ጨምሮ ለአቃቤ ሕግ አቀረበ።
የጫላ የእምነት ክህደት ቃል
በተደጋጋሚ ክስ የሚቀርብበት መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተጠርጥረሃል በሚል በ2010 ዓ.ም አስሮት ወደ ማረሚያ ቤት ከወሰደው በኋላ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በነፃ እንዳሰናበተው በምስክርነት ቃሉ ላይ ጠቅሷል።
ከወይዘሮ ደራርቱ ጫልቺሳ ጋር ትዳር መስርቶ ከአሜሪካን ከቤተሰቦቹ ገንዘብ እየተላከለት እንደሚኖር አመልክቶ፤ ከከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት እንዳለህ በማስመሰል ሰዎችን አታለሃል በሚል ክስ ቢመሠረትበትም የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ10ሺህ ብር ዋስ እንደተለቀቀም በእምነት ክህደት ቃሉ ላይ ሠፍሯል።
ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ስድስት ኪሎ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አካባቢም የማታለል ወንጀል ፈፅመሃል መባሉ፤ ፍፁም ውሸት እንደሆነ እና በአራዳም ሆነ በየካ እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች በአቶ ዳኛቸው ብርሃኑ፣ በአቶ ወንድሙ ደበላ እና በአቶ ዮሴፍ ማሞ ላይ የማታለል ወንጀል አለመፈፀሙን እና ሰዎቹን በምንም መልኩ እንደማያውቃቸው ገልፆ ቃሉን ሠጥቷል።
ውሳኔ
ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ ጫላ ባይሳ ላይ ክስ መስርቷል። የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 295007 ሲያከራክር ከቆየ በኋላ፡ በሕዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ጫላ ባይሳ ላይ አራት ዓመት ፅኑ እስራት እና 2 ሺህ ብር ቀጥቶታል።
በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ በመጠየቁ፤ ከግንቦት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተከሳሽ ጫላ ባይሳ በእስር ላይ የቆየ ቢሆንም፤ በተከሰሰበት ወንጀል የፌዴራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ 1ኛ ምድብ ይግባኙን ተከትሎ በሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰባት ዓመት ፅኑ እስራት ይፈፀምበት ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2016