«ዮቶር» መጽሐፍ ዛሬ ያወያያል
ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ንባብ እና ውይይት ዝግጅት ክፍል ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ዛሬ እሁድ ግንቦት 11 ቀን 2011ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ «ዮቶር» በተሰኘውና በዓለማየሁ ደመቀ በተዘጋጀው መጽሐፍ ላይ ውይይት ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ ውይይት፤ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት መምህርና ገጣሚ ዋሲሁን እጅጌ ናቸው። ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ዛሬ በሚያካሂደው በዚህ የመጽሐፍ ውይይት ላይ መታደም የሚፈልግ ሁሉ እንዲታደም ግብዣና ጥሪውን አስተላልፏል።
ብራና ግጥም በጃዝ ነገ ይከናወናል
ብራና ግጥም በጃዝ ወርሃዊ መርሐ ግብር በዚህ ወር «እኛው ነን!» በሚል ርዕስ ነገ ግንቦት 12 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን ከ11፡30 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይከናወናል።
በዚህ ክዋኔ ወግና ዲስኩር እንዲሁም የግጥም ሥራዎች ይቀርባሉ። ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ፣ ደራሲና የሕግ ባለሙያ ዳግማዊ አሰፋ እንዲሁም ተዋናይና የፊልም አዘጋጅ ሰለሞን ሙሄ የሚገኙ ሲሆን፤ ገጣምያን በላይ በቀለ ወያ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ምልዕቲ ኪሮስ እና ኢዮኤል አያሌው ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ፍሬ አምባ የሕጻናት ዝማሬ ቡድን እና ሻሎም ኢትዮጵያ የሙዚቃ ባንድም መድረኩን ያደምቁታል። በዚህ መርሐ ግብር መታደም ለሚፈልጉ ሁሉ መግቢያው አንድ መቶ ብር መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
«…መፍትሔው ኢትዮጵያዊነት ነው!» የኪነጥበብ ዝግጅት ይካሄዳል
በምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን የተዘጋጀ «…መፍትሔው ኢትዮጲያዊነት ነው!!!» የተሰኘ የኪነ ጥበብ ዝግጅት ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን ከ11፡00 ሠዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል።
በዚህ ክዋኔ ላይ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ ነብይ ዮናታን አክሊሉ እንዲሁም ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ዲስኩር ያቀርባሉ። ደራሲት ሕይወት ተፈራ (Tower In The sky)፣ ተዋንያን ዓለማየሁ ታደሰ እና ሽመልስ አበራ ደግሞ ወግ ያስደምጣሉ። ግጥሞች በገጣምያን ነብይ መኮንን እና ኤፍሬም ስዮም የሚሰማ ሲሆን የባህል ውዝዋዜም ምሽቱን ያደምቀዋል ተብሏል። በዚህ ክዋኔ ላይ ለመታደም መግቢያው 100 ብር መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011