
አዲስ አበባ፡- በጉራጌ ዞን በደመቀ መልኩ የሚከበረውን የመስቀል በዓል የጉራጌ ማንነትና መገለጫዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እንደሚሠራ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ቢሮ አስታወቀ።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት አመርጋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የመስቀል በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ የጉራጌ ዞን ነው። ይህም በዓል በዞኑ ከሃይማኖታዊ ገፅታው ባለፈ ባህላዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።
የመስቀል በዓል እንደ ዞን በየዓመቱ በተመረጡ ቦታዎች የሚከበር መሆኑን አንስተው፤ ዘንድሮ በመንግሥት ደረጃ ከመስከረም 12 ጀምሮ ለ6ኛ ጊዜ በምሁር አክሊል ወረዳ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ቱሪስቶች በተገኙበት እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከበርም አስታውቀዋል።
የዘንድሮ የመስቀል በዓል በደመቀ ሁኔታ ከማክበር ባለፈ እንደ ጉራጌ ዞን በጉራጌ የበዓሉ አከባበር በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይም የጉራጌ ክትፎ አዘገጃጀትን ሙሉ ሂደቱን ማሳየት፣ የጉራጌ የመንደሮች አቀያየስ እና የባህላዊ ጎጆ ቤቶች አሠራርና መሰል የጥበብ ሥራዎች ለማሳየት በአውደ ርእይ ይካሄዳል ብለዋል። በተለይም ባህሉን የማያውቁና ሌላ አካባቢ ላይ ላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ቱሪስቶች እና ለአስጎብኚ ማኅበራት የጉራጌን ባህልና የመስቀል አከባባር የማሳየትና የማስተዋወቅ ሥራን በትኩረት እንደሚሰሩ ወይዘሮ መሠረት አስታውቀዋል።
በጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል ከመስከረም 12 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት የሚከበር መሆኑን ገልጸው፤ በእነዚህ ቀናትም የጎመን ክትፎ ፣የሴቶች መስቀል፣ ደመራ፣ የእርድ ሥነ ሥርዓት፣ አዳብና፣ መሰል የአከባበር ሥነ ሥርዓቶች እንደሚካሄዱ ጠቅሰዋል።
በዓሉን ለመታደም የብሔረሰቡ ተወላጆችም ሆነ ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ቢሮው የጉራጌ ዞን ያለውን ሰፊ የመልክዓ ምድር እና ባህላዊ እሴቶች ለቱሪዝም መስህብነት በመጠቀም ከቱሪዝሙ ዘርፍ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት እየሠራ ነው ብለዋል። በዚህም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ የሚገኙትን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች ይዘታቸው እንደተጠበቀ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ወይዘሮ መሠረት አስታውቀዋል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2016 ዓ.ም