ሞሮኮ በ2024 ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በምታስተናግደው 14ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪያውን ዙር የማጣሪያ ውድድር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻሉም::
ሉሲዎቹ በማጣሪያ ጨዋታው ቡሩንዲን የገጠሙ ሲሆን፤ የደርሶ መልሱን ጨዋታ በቡሩንዲ ፍቃደኝነት አዲስ አበባ ላይ ነበር ያደረጉት:: ይህም ለሉሲዎቹ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ በደርሶ መልስ ጨዋታ ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋሉ ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር::
የመጀመሪያውን ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም ባለፈው አርብ ያደረጉት ሉሲዎቹ በረድዔት አስረሳኸኝ ግብ መምራት ቢችሉም አንድ ለአንድ ነበር የተለያዩት:: ያም ሆኖ በሁለተኛው ጨዋታ ያሸንፋሉ ተብሎ ብዙ ተስፋ ተደርጎ ነበር::
ሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ትናንት በተመሳሳይ አበበ ቢቂላ ስቴድየም ሲካሄድ ረድዔት አስረሳኸኝ በ19ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ ሉሲዎቹ በድምር ውጤት ሁለት ለአንድ መምራት ችለው ነበር:: 48ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቡሩንዲዎች የአቻነት ግብ በማስቆጠር በማጣሪያ ፉክክሩ መቆየት ችለዋል:: ሉሲዎቹ በጨዋታው ተጨማሪ ጎል አስቆጥረው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በኳስ ቁጥጥር ልቀው የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም:: በዚህም ውጤት ጨዋታው በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቶ ቡሩንዲ 5ለ3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማጣሪያ ማለፏን አረጋግጣለች::
በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የሉሲዎቹ ስብስብ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን ይዞ ከረጅም ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ቢዘጋጅም በሜዳውና በደጋፊው ፊት የነበረውን እድል መጠቀም አልቻለም:: በዚህም የመጨረሻውን ዙር ማጣሪያ ከወዲሁ ለመሰናበት ተገዷል::
ቡሩንዲ ቀጣዩን ዙር መቀላቀሉን ተከትሎ በመጨረሻው ማጣሪያ ከዩጋንዳና አልጄሪያ አሸናፊ ጋር የምትገናኝ ይሆናል:: አልጄሪያ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ 2ለ1 አሸንፋለች፣ ይህም በመልሱ ጨዋታ በሜዳዋ አሸንፋ ቡሩንዲን የመግጠም የተሻለ እድል እንዲኖራት አድርጓል::
እኤአ ከ1991 ጀምሮ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አዘጋጅነት የሚካሄደው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ሀገራት በደርሶ መልስ ጨዋታ እንደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሚያደርጉት ፍልሚያ ነበር። እኤአ ከ1998 ጀምሮ ግን ልክ እንደወንዶቹ የአፍሪካ ዋንጫ ራሱን የቻለ ትልቅ የአህጉሪቱ ውድድር በመሆን በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል።
ሉሲዎቹ በዚህ ትልቅ መድረክ እኤአ ከ2002 ናይጄሪያ ያዘጋጀችው አፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን አድርገዋል። በዚያ ውድድር ከምድብ ጨዋታዎች የዘለለ ውጤት ግን አላስመዘገቡም። እኤአ በ2004 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ ተሳትፈው አራተኛ ሆነው ያጠናቀቁበት ውድድር በታሪካቸው አሁንም ድረስ ትልቁ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። ከዚህ የተሻለ ውጤት በቀጣይ 2006 ላይ ናይጄሪያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ያስመዘግባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ከማጣሪያ ጨዋታዎች አስቀድሞ በውድድሩ ሳይሳተፉ ቀርተዋል። በ2008ቱ የኢኳቶሪያል ጊኒና በ2010 የደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ደግሞ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻሉም። በቀጣይ እኤአ 2012 ኢኳቶሪያል ጊኒ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ መቅረብ ቢችሉም ከምድብ ጨዋታዎች ማለፍ ሳይችሉ በጊዜ ከውድድሩ ተሰናብተዋል። ከዚያም በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሳይመለሱ አስራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የዛሬው የአሰልጣኝ ፍሬው የወጣቶች ስብስብ ይህን ታሪክ ለመቀየር ከመጀመሪያው ማጣሪያ ከወዲሁ መሰናበቱን ተከትሎ ሉሲዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ተጨማሪ ሁለት ዓመታትን ሊጠብቅ ተገዷል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2026