መውሊድ ፤ የሰላምና የሁላችንም በዓል፤ የሁላችንም ድምቀትየአብሮነት በዓል!

 መውሊድ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር ዘመነ ሂጅራ ራቢአል አወል የተሰኘው ሦስተኛው ወር በገባ በ12ኛ ቀን በየዓመቱ ይከበራል። የቃሉ ምንጭ አረብኛ ሲሆን ትርጉሙም የመወለጃ ቦታ ወይም እለት ማለት ነው።

የመውሊድ በዓል ነብዩ መሐመድ የተወለዱበትን ቀን ለመዘከር በሙስሊሞች ዘንድ የሚከበር በዓል ነው:: የመውሊድ በዓል የነቢዩ መሐመድ መልካም ተግባራትን የህይወት መርህ በመከተል ይከበራል። በመውሊድ በዓል ሰላም፣ ፍትሕ፣ በጎነትና አንድነት የመሳሰሉ ነብያዊ ባህርያት ጎልተው የሚወጡበትና ሰዎችም የነብዩ መሐመድን ፈለግ በመከተል የሚረዳዱበትና የሚደጋገፉበት ቀን ነው::

ነብዩ መሐመድ በምድር ላይ ሳሉ ሰላም ፍቅርና አንድነትን በማስተማር አርዓያ የነበሩ ነብይ ነበሩ። የነብዩ መሐመድ መልካም ፀባያትም በመላው ዓለም እንዲሰርጽና ሰዎችም ፈለጋቸውን ተከትለው መልካም ተግባራትን እንዲያከናውኑ የመውሊድ በዓል በመላው ዓለም በድምቀት ይከበራል::

የመውሊድ በዓል በኢትዮጵያ መከበር ከጀመር በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በጋራ በመሆን በዓሉን ሲያከብሩ ኖረዋል:: በበዓሉ ዕለት ሙስሊሞች ክርስቲያን ጎረቤቶቻቸውን በመጥራት እና ማዕድ በመቋረስ በዓሉን በድምቀት ያሳልፋሉ:: ስለሀገራቸው ሰላምና አንድነት ይጸልያሉ፤ አብሮነታቸውንም ያጠናክራሉ::

መውሊድ የአብሮነት በዓል ነው። በመውሊድ በዓል ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ ያሳልፋል፤ አብሮነት ይደምቃል:: ከዚህ በሻገር ግን ከጥንት በኢትዮጵያ ያለው የመውሊድ አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት:: ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ነች:: መውሊድን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ በክርስትና በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው:: ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን፤ ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው::

ነብዩ መሐመድ በእስልምና ሃይማኖት በነበራቸው አስተምህሮት የሰው ልጆች ያለ ዘርና ሃይማኖት ልዩነት የምድር ፍጡራን ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሲያስተምሩ የቆዩ በመሆኑ ዛሬ በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት እየተናጠች ለምትገኘው ሀገራችን የነብዩ አስተምህሮት ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል:: ሕዝበ ሙስሊሙም ልዩነትን፤ መገፋፋትና መወቃቀስን በማስወገድ ለሀገሩ አንድነትና ሰላም የሚሰራበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚገኝ መረዳት አለበት::

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው:: የእስልምና እምነት ድሆችን ማብላትና ማጠጣት እንዲሁም በዓላትን እኩል በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ጥሎባቸዋል:: ከእነዚህ ትዕዛዞች አንዱ ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትና መደገፍ አንዱና ዋነኛው ነው::

የእምነቱ ተከታዮች በዓላትን ራሳቸው ብቻ ተደስተው እንዲያሳልፉ አይፈቀድላቸውም:: ይልቁንም በዓላት ድምቀት የሚኖራቸውና በፈጣሪም ዘንድ ተቀባይነትን የሚያጎናጽፉት ከተቸገሩ ወገኖች ጋር አብሮ ማሳለፍ ሲቻል ነው:: ስለዚህም ሙስሊሞች የመውሊድ በዓልን ሲከብሩ ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ ከማጋራት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሊሆን ይገባል::

በአጠቃላይ መውሊድ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ከዚህ በሻገር እንደሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው:: በተለይም በአሁኑ ወቅት በጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተሰደዱ በርካታ ወገኖች አሉ:: ከዚሁ ባሻገር በድርቅ የተጎዱና በተለይ በተለያየ መንገድ ጉዳት ደርሶባቸው ያላገገሙ ወገኖች በችግር ውስጥ ስለሚገኙ እነዚህን ወገኖች መደገፍና ተባብሮ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው መመለስ አንዱ በመውሊድ ወቅት የሚከወን ተግባር ሊሆን ይገባል::

በአጠቃላይ ሕዝበ ሙስሊሙ 1498ኛውን የመውሊድ በዓል ሲያከብር የነብዩ መሐመድን መልካም ስብዕናና አስተምህሮቶችን በመውሰድ የሀገሪቷን ሰላምና የሕዝቦቿን አንድነት ለማጠናከር መስራት ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You