ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ቡሩንዲን ይገጥማሉ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ቡሩንዲን በመግጠም ይጀምራሉ። ሁለት ዙሮች ባሉት በዚህ ማጣሪያ በደርሶ መልስ ጨዋታው ብልጫ ያለው በሁለተኛው ጨዋታ ተለይቶ የውድድር ተሳታፊነቱን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል። ሞሮኮ በምታስተናግደው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ለመሆንም ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከቀናት በኋላ የሚጀምሩ ይሆናል። በማጣሪያው ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ካሉ ሀገራት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ይገኝበታል። ከብሩንዲ አቻው ጋር የተደለደለው ቡድኑ ከቀናት በፊት ተሰባስቦ ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን፤ የደርሶ መልስ ጨዋታውንም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከነገ በስቲያ የሚያከናውን መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በማጣሪያው 40 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ ሁለት ዙር በሚኖረው የማጣሪያ ውድድር የሚያልፉ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫው ይካፈላሉ። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መሪነት ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱና ትልቁ ሲሆን፤ 12 ቡድኖችን በማሳተፍ ይካሄዳል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ የደርሶ መልስ ጨዋታ ብልጫውን የሚያገኘው ቡድን ወደ ሞሮኮ ለመጓዝ አንድ እግሩን ሲያነሳ፤ በቀጣዩ ዙር ጨዋታዎች ደግሞ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥ ይሆናል። የውድድሩ አዘጋጅ ሀገር ሞሮኮ ስትሆን፤ እአአ በ2022 አስተናጋጅ እንደነበረች የሚታወስ ነው። ሀገሪቷ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ ዓመት ውድድሩን እንድታዘጋጅም ተመርጣለች። ጨዋታዎቹም ራባት ላይ በሚገኘው የሞሃመድ ስድስተኛ ሁለገብ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል።

ቡድኑ ለመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቹ የሚሆነውን ዝግጅት ለማድረግ በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን፤ 26ቱ ተጫዋቾች ከጳጉሜ 2/2015 ዓ.ም ጀምሮ ሪፖርት በማድረግ ወደ ዝግጅት ገብተዋል። ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አጠናክሮ የቀጠለው ቡድኑ ዳማ ከተባለ የወንዶች ቡድን ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የልምምድ ጨዋታ አድርጓል። ጨዋታው 7ለ7 ሲጠናቀቅ፤ ሎዛ አበራ እና ንግስት በቀለ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል። ንቦኝ የን፣ አርያት ኦዶንግ እና ማህሌት ምትኩ ደግሞ ቀሪዎቹን የሉሲዎቹን ግቦች ከመረብ አገናኝተዋል። ከልምምድ ጨዋታው አስቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል እና አጥቂ የሆነችው ሎዛ አበራ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠማት ቢሆንም አገግማ ቡድኑን በመቀላቀል ግቦችን ማስቆጠርም ችላለች።

የመጀመሪያው ጨዋታው መስከረም 9/2016 ዓ.ም ሲከናወን ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ መስከረም 15/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚከናወንም ተረጋግጧል። ይኸውም ኢትዮጵያ በሜዳዋ ከሚደረገው ግጥሚያ ከቀናት በኋላ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ እዚሁ እንዲቀጥል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት ያደረገችና ለካፍ ያሳወቀች በመሆኑ ነው። በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎም ሆነ ውጤታማነት እምብዛም የሚነገር ታሪክ የሌለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ 124ኛ ላይ ተቀምጧል። በማጣሪያው የሚገጥመው የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በአንጻሩ በደረጃ ሰንጠረዡ 176ኛ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በራሱ ሜዳ በሚያደርገው ጨዋታ ተጋጣሚውን ቡድን በመርታት ወደ ሁለተኛው ዙር ለማለፍ ምቹ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ይህንኑ ያገናዘበ ዝግጅቱንም ባሉት ቀናት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በልምምዱ ወቅትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሃቢባ ሲራጅ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በአካዳሚ በመገኘት ክትትል ያደረጉ መሆኑንም ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አስነብቧል።

 ብርሃን ፈይሳ

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You