የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት ችግሮችን መሻገር ይገባል

አዲስ አበባ፡– የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከር ችግሮችን መሻገር እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በአፍንጮ በር አካባቢ ባለሀብቶችን በማስተባበር ያስገነባቸውን ቤቶች ሰሞኑን ለአቅመ ደካሞች ወገኖች አስረክቧል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክ ያላት ሀገር ብቻ ሳትሆን በሰብአዊ፣ በባህላዊና በተፈጥሮአዊ ሀብቶች የታደለች ሀገር ናት፡፡ ይህንን ትልቅ አቅም በመጠቀም ድህነትንና ኋላቀርነት መዋጋት ይቻላል፡፡

አቶ ገብረመስቀል መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ መልካም ሥራዎችን በማጠናከርና የኅብረተሰቡ የእርስ በርስ የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከርና በማስፋፋት የሕዝቡን ችግር መቅረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጎነት የሚጀምረው ራስን ከመቻልና በጎ አስተሳሰብ ከመያዝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በጎ ሀሳብ፣ ገንዘብና ጉልበት ያለው ሰው ሁሉ በጎ በማድረግ ለብዙዎች መትረፍ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ ድህነትን በመዋጋት ወደ ብልጽግና ለመሻገር ገና ብዙ እንደሚቀር ገልጸው፤ አሁንም በትብብር መሥራትና የሀገር ባለውለታዎችን መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴሩ ለሀገር አገልግለው ጧሪ ያጡ ዜጎችን ለመደገፍ ያስገነባው ሕንፃ በ432 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን 32 ክፍሎች አሉት፡፡ እነዚህም ክፍሎች ለ10 አባወራዎች ተሰጥተዋል። ቤቶቹ ነዋሪዎች በፊት በነበራቸው የቤት ስፋት መሠረት የተገነቡ ሲሆን ለግንባታ እና የቤት ዕቃ ለማሟላትም ከ 15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

አካባቢው በወንዝ ዳርቻ ልማት እየታደሰ ያለ አካባቢ እንደመሆኑ ሌሎችም ድጋፍ የሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ሌሎች ባለሀብቶች ትብብር እያደረጉ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቤት የተሰጣቸው ወይዘሮ አስቴር ሞገስ፤ ከዚህ ቀደም በደከመ ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገልጸው፤ በጎ ልብ ባላቸው ሰዎች ትብብር የተሻለ ቤት ማግኘታቸው ደስታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም ሠርቶ ተለውጦ እኔም ለሌሎች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት ፈጥሮብኛል ብለዋል፡፡

ሌላኛው ቤት ያገኙ እማሆይ አለምነሽ ባርዳ በበኩላቸው ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ በዚሁ አካባቢ  መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን ‹‹ለረጅም ዓመታት በኖርኩበት አካባቢ እንደዚህ ያለ ቤት በማግኘቴ ዳግም የተወለድኩ መስሎ ተሰምቶኛል›› ብለዋል፡፡

በጎነት ያቀረቀረን አንገት ቀና ያደርጋልና ለበጎ አድራጊውም ደስታን በረከት ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን  መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You