‹‹ሁሌም ከአትሌቶች ጀርባ አለሁ›› -አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው በዓለም ታሪክም ከታዩ ምርጥ አትሌቶች አንዱ የረጅም ርቀት ንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ ነው።። ከመም እስከ ጎዳና ላይ ውድድሮች አስደናቂ ብቃቱን ያስመሰከረው ይህ ድንቅ አትሌት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ ውድድሮች እየታየ አይገኝም።። ቀነኒሳ በተጠናቀቀው ዓመት ከተካሄደው የቡዳፔስቱ ዓለም ቻምፒዮና መልስ ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች ጋር በመገኘት የሞራል ድጋፍ ሲያደርግ ነበር።።

ውድድሩን ተከትሎም በሰጠው አስተያየት “ጥሩ ውጤት ነው የተገኘው” በዚህም ደስ ብሎኛል።። በተለይ በማራቶንና በ10ሺ ሜትር ሴቶች የተገኘው ውጤት እጅግ አስደሳች ነው።። እንዳየነው በእልህ አስጨራሽ ፉክክር ይህ ውጤት መገኘቱ አመርቂ ሊባል የሚችል ነው።። ሆኖም በአንዳንድ ተጠባቂ ርቀቶች ውጤት ባለመገኘቱ ተሰምቶኛል።። በልምድ፣ የአቅምና በቴክኒክ ማነስ ይህ ሊሆን እንደቻለ እገነዘባለሁ፤ አንዳንዶቹ ግን አቅም እያላቸው ውጤት የታጣባቸው ርቀቶች አሉ።። በእነዚህም ላይ ለወደፊቱ አትሌቶችን በሥነልቦና በማጠናከር ወደ ውድድር እንዲገቡ እንዲሁም የተፎካካሪ አትሌቶችን ደካማ ጎን በማውጣት ምክር ቢሰጥ ይሻሻላል ብዬ አስባለሁ›› ብሏል።።

ቀነኒሳ በመም ውድድሮች ላይ በርካታ አስደናቂ ገድሎችን ፈፅሟል፣ እሱ የበላይነቱን ለረጅም ጊዜ በተቆጣጠረበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች አሁን ያለው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት እየቀነሰ በመምጣቱ ይቆጫል።። ምክንያቱን ሲገልጽም ‹‹ውጤት የጠፋው ጠንካራ አትሌቶች ስለሌሉ አይደለም።። በእርግጥ በአንዴ አትሌቶችን ማግኘት አይቻልም ነገር ግን ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ ነው።። የታዳጊ ፕሮጀክቶች እና ወጣቶች ላይ ከተሠራ ውጤቱ ይመለሳል የሚል እምነት አለኝ›› ይላል።።

ባለፉት የዓለም ቻምፒዮና እና ኦሊምፒኮች በተለይ በኃይሌ ገብረስላሴ፣ በቀነኒሳ በቀለ እና ስለሺ ስህን የቡድን ቅንጅት የተገኙት ሜዳሊያዎች ከኢትዮጵያውያን ትውስታ ሊሰረዙ የማይችሉ ናቸው።። በአንጻሩ አሁን ላይ ያሉት አትሌቶች እንደቀድሞው አለመሆናቸው ይስተዋላል።። በዚህ ላይም ጠንካራው አትሌት ‹‹በቡድን ለመሥራት ጥረት ያደርጋሉ፤ ሆኖም ይህም ራሱን የቻለ ችሎታ ያስፈልገዋል።። ለምሳሌ ያህል በኡጋንዳውና በእኛ አትሌቶች መካከል ያለው የብቃት ደረጃ የሚለያይ ነው፤ ስለዚህም ጠንካራ ሥራ ይፈልጋል።። ጊዜው በሄደ ቁጥር ሁኔታዎችም መለወጣቸው አይቀርም። በሁለቱም ርቀቶች ከ15 ዓመት በፊት ክብረወሰኑ የእኛ ነበር።። በሂደትም ነገሮች ዘመናዊ መልክ እየያዙ፣ ጠንካራ አትሌቶች እየተፈጠሩ ክብረወሰኑም ሊሻሻል ችሏል።። ነገር ግን ይህንን ክብር ወደ ሀገሩ ሊያስመልስ የሚችል ብቃት ላይ የሚገኝ አትሌት ማፍራት የግድ ነው።። በመሆኑም ተፎካካሪው አትሌት ጠንክሮ በመሥራት አሸናፊ እንደሆነ በመረዳት የእኛ አትሌቶችም በቁጭት ሊሠሩ ይገባል።። አሁን ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የስፖርት ትጥቆች በተለይ የመሮጫ ጫማዎች ፍጥነትን በመጨመር ሰከንዶችን ሊያፈጥኑ የሚችሉ መሆናቸው የአትሌቱን ብቃት ሊያሻሽሉ ይችላሉ።። በዚህ በመታገዝ እንዲሁም በጠንካራ ሥራ ውጤታማ መሆን ይቻላል፤ የተወሰደብን ክብረወሰንም አንድ ቀን እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለሁ›› ሲል ያብራራል።።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአትሌቶች ዝግጅት ጎን ለጎን እነ ቀነኒሳን የመሰሉ የዓለም የምንጊዜም ምርጥ አትሌቶች አጋርነት ሁሌም አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው።። መጪው ኦሊምፒክ እንደመሆኑም በቻምፒዮናው የታየው ሁኔታ እንዳይደገም ከአንጋፋ አትሌቶች ምን ይጠበቃል? ‹‹እኔ ለአትሌቶች ልምዴንና ምክሬን እንዳካፍል በፌዴሬሽኑም ተጋብዣለሁ።። ነገር ግን በግሌም ቅርበት ካለኝ አትሌቶች ጋር ምክር ከመስጠት ባለፈ ባገኘሁት አጋጣሚ በልምምድ ቦታም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮ ስንገናኝ ልምዴን ሳካፍል ነው የቆየሁት።። ሁሌም ከአትሌቶች ጀርባ ነበርኩ በቀጣይም መሰል አስተዋጽኦዬን የምቀጥል ይሆናል›› ብሏል።።

በሌላ በኩል ‹‹አትሌቶች ልምምድ ሊያደርጉበት የሚችሉበትን መም በመገንባት ወጣቶች እንዲበራከቱ እገዛ እያደረኩ ነው።። በሱሉልታ አካባቢ መም በመገንባቴ በርካታ አትሌቶች እየተጠቀሙበት ነው።። ይህንን ያደረኩት ወጣት አትሌቶችን ከማገዝ ጎን ለጎን የሚወደኝን ሕዝብ ለማስደሰትም ነው።። የተለያዩ የንግድ አማራጮች ላይ በመሳተፍ ገቢ ማግኘት ብችልም ትኩረቴን ስፖርቱ ላይ በማድረግ ለሀገር ውጤት የሚመዘገብበትን መንገድ ለመፍጠር በማሰብ ነው።። በእርግጥም በርካታ አትሌቶች እየሠሩበት ነው፤ ውጤታማም ሆነዋል››።።

በማራቶን የዓለም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ የማራቶን ክብሩን ወደ ኢትዮጵያ ያስመልሳል የሚለው የበርካቶች ዕምነትና ምኞት ነው።። ይህ መቼ ሊሳካ ይችላል የሚለውንም ‹‹በእርግጥ ይህ ሰዓት እንደቀላል የሚታይ አይደለም፤ ፈጣን ሰዓቶች በየጊዜው እየተመዘገቡ መሆኑ ይታወቃል።። ነገር ግን እኔም ውድድር አላቆምኩም፤ እስካሁንም ክብረወሰኑን ለመስበር የቀሩኝን 2ሰከንዶች ለማሻሻል የያዘኝ የእግሬ ሕመም ነው።። አሁንም ቢሆን ግን ጥረቴን እቀጥላለሁ፤ እኔ ባልችልም የሀገሬን ልጆች በመደገፍ ክብረወሰኑ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ›› ሲል አብራርቷል።

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

ብርሃን ፈይሳ

Recommended For You