‹‹ኢትዮጵያውያን በየሕይወታቸው ምዕራፍ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ታሪክ መጻፍ ይገባቸዋል›› – ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የጥንታዊ መዛግብት ተመራማሪና ፀሃፊ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን በእያንዳንዱ የሕይወታቸው ምዕራፍና በ365 እያንዳንዱ ቀናት ሽክርክሪት ለሀገር፣ ለወገንና ለዓለም የሚጠቅም ታሪክ ሊጽፉ እንደሚገባ የጥንታዊ መዛግብት ተመራማሪ እና ጸሃፊ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ገለጹ።

ዶ/ር ሮዳስ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዘመን ኡደት፣ ሽክርክሪት ጉዞ ነው። በዘመን አንቆምም እንሄዳለን። ሁሉም ተንቀሳቃሽ ነው። ጸሃይ፣ ጨረቃም ይንቀሳቀሳል። በስራና በሕይወት ለውጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። አዲስ ዓመት አዲስ ማንነት ይዘን የምንጓዝበት ነው ያሉት ዶ/ር ሮዳስ፤ ከኡደት ጋር አብረን መሄድ አለብን። አምላክ በየዓመቱ 365 ገጽ ያለበት ምንም ያልተጻፈበት ንጹህ ወረቀት ሰጥቶናል።

በእያንዳንዱ ገጽ ላይ የወደድነውን እንድንጽፍበት ተፈቅዷል። በእነዚህ ቀናቶች ሀገር፣ ወገንና ዓለምን የሚጠቅምና የሚያኮራ ስራ ልንሰራበት ይገባል ነው ያሉት። ዘመን ለመቁጠር ለመስፈር፤ ጸሃይ፣ ጨረቃ ከዋክብት ያስፈልጋሉ። ለጸሃይ አቆጣጠር ካሌንደር መቀመር ይቻላል። በጨረቃ አቆጣጠር ዘመንን መቀመር እንደሚቻልም አመልክተዋል።

ጥንት ኢትዮጵያውያን ሰማይን፣ ጸሃይን፣ ከዋክብትንና ጨረቃን በአጠቃላይ ሰማያዊ አካላትን በመመርመራቸው ምክንያት ልዩ የዘመን አቆጣጠር ስርዓት ለመስራት እንደቻሉም ተናግረዋል። በጸሃይ አቆጣጠር ሥርዓት ዛሬ 2016 ዓ.ም ላይ ገብተናል። ምክንያቱም አንድ ዓመት ኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ወይም 06 ካሊት ይባላል፤ ከ06 ሰዓት ከሁለት ደቂቃ እንደሆነም በምሳሌ አስረድተዋል።

በጨረቃ አቆጣጠርም 354 ዕለት ከ22 ኬክሮስ ከ01 ካሊት፣ ከ37 ሳልፊት ከ52 ራቢት ከ48 አምፊት እንደሚባል። አውዳመቷ የምትጨርስበት ወቅት መሆኑም ነው የገለጹት። ስለዚህ በጨረቃ አቆጣጠር 2077 ዓመተ ምህረት ላይ እንደተገባም ተናግረዋል። ‹‹ኢትዮጵያውያን በየሕይወታቸው ምዕራፍ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ታሪክ መጻፍ ይገባቸዋል›› – ዶክተር ሮዳስ ታደሰ የጥንታዊ መዛግብት ተመራማሪና ፀሃፊ ጸሃይን በመቀመር የጸሃይ ዘመን አቆጣጠር ካሌንደርን፣ በጨረቃ በመቀመር ደግሞ ሉናር ካሌንደርን በመስራታቸው ምክንያት በሁለቱም መቀመር የሚችል የዘመን አቆጣጠር እንዲኖር ማስቻሉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከምእራባውያኑ የዘመን ቀመር ጋር የሰባት ዓመት፣ የ 11 ዕለታት ልዩነት እንዳለውም ነው የጠቀሱት። ኢትዮጵያውያን ጳጉሜን 13 ኛ የመጨረሻ ወር ሲኖረን እነርሱ ግን ጳጉሜን ስላጠፉ እያንዳንዱ ወራቸው 31፣ 30፣ አንድ ወር የካቲት 28 አላቸው። በኢትዮጵያ 30 ዕለታት አሉ፤ እነዚህ ነገሮች ብዙ ልዩነትን አስከትለዋል ብለዋል። በመሰረታዊ ልዩነቱ የ 753 ዘመን ነበር።

አሁን ተቀራርቦ ሰባት ዓመት ሆኗል። በተለይ ኢትዮጵያን ሌሎች በቤዛንታይን ግዛት የነበሩ ይከተሉት የነበረ የዘመን ቀመር ዓመተ ፍጥረት ወይም ዓመተ ዓለም የሚባል ነው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለውን ይቀምሩ ነበር። ከክርስቶስ ዘመን በፊት የነበረውን ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ በማለት ይቀምሩ የነበሩት የሮም ከተማ የተመሰረተችበትን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 753 ዘመንን አንድ ብሎ በመቁጠር እንደነበረም ነው የጠቆሙት።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You