ሴቶችና የበዓል ውሎ

አዲሱ ዓመት እንዴት እያለፈ ነው? የቄጤማው፣ ከዶሮው፣ ከጠላው ሽታ ጋር ቡናውም በእጣን ታጅቦ ቤቱ በመልካም መአዛ ታውዶ፣ ቤተሰቡ ከወዳጅ ዘመድና ከጎረቤቱ ጋር ተሰባስቦ እየበላ እየጠጣ፣ አበባዮሽ የሚጫወቱ ታዳጊዎች፣ የእንኳን አደረሳችሁ በወረቀት የተሳለ የአበባ ስጦታ የሚያበረክቱ ወዶች ልጆች አካባቢን እያደመቁ በዓሉን በደስታ እያሳለፋችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን። በሀገር ባህል ልብስ መድመቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው ታዲያ። በዚህ መካከልም በትምህርት፣ በትዳር፣ በኑሮ፣ በሌላም የልባቸው መሻት እንዲሳካላቸው ምርቃቱ፣ ለሀገር ሰላም መመኘቱ በአዲስ ዓመት የተለመደ ነው፡፡

በዓል በዚህ ድባብ ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ሴቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ለበዓል የሚሆነውን ገበያ ከመገብየት ጀምሮ ተሳትፎአቸው በእጅጉ የጎላ በመሆኑ ነው ሚዛኑ ወደ ሴቶች ያደላው። ምግቡን አዘጋጅቶ ማቅረቡ በመስተንግዶውም ብሉልኝ ጠጡልኝ የሴቶች ድርሻ ትልቅ ነው። በዓልን ምክንያት በማድረግ በመዲናችን ዞር ዞር ብለን ሴቶችና የበዓል ውሎአቸውንና በበዓላት ወቅት ያለባቸውን የሥራ ጫና በተመለከተ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ ያሉ እንስቶችን አነጋግረናል፡፡

ታዲያ ካነጋገርናቸው አንዳንዶቹ በሙያ ማነስ ይሁን ድካምን ለመቀነስ ግልጽ አላደረጉትም ግን በተወሰነ ደረጃ በወላጆቻቸው ቤት የበዓል ሥራ እንደሚያሰሩ ነግረውናል። ከዛ በተቃራኒው ደግሞ ለሥራቸው ቅድሚያ የሚሰጡ እንስቶችም አጋጥመውናል።

በበዓል መዳረሻ ሥራ ከሚበዛባቸው የአገልግሎት መስጫዎች መካከል የውበት ሳሎኖች ተጠቃሽ ናቸው። ሴቶች በዓሉን አምረውና ደምቀው ለመዋል በዘመናዊው ስቲም፣ በባህላዊው ወይባ ጢስ፣ በፀጉር ተኩስና ሹሩባ እንደምርጫቸው ይጠቀማሉ። የውበት ሳሎን ሥራ ላይም በስፋት የሚገኙት ሴቶች ናቸው፡፡

በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት በዓልና ሥራን እንዴት አጣጥመው እንደሚያሳልፉ ቦሌ አካባቢ ከሚገኙ የሴቶች ውበት መጠበቂያ ሳሎን ወደ አንዱ ጎራ በማለት የፋና ወይባ ጢስና ስፓ ባለቤት ወይዘሮ ፋና ኤጀሬን አገኘናቸው። በመልካም ፈገግታ የተቀበሉን ወይዘሮ ፋና ምንም እንኳን አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋና በአዲስ መንፈስ ሁሉም ሊቀበለው እንደሚገባ ቢያምኑም ደስታውን ቅድሚያ የሚሰጡት ለደንበኞቻቸው ነው። እንደ ፍላጎታቸው አስተናግደው ተውበውና ተደስተው ሲሄዱ ነው የበለጠ የሚያስደስታቸው፡፡

‹‹ሴቶች ለበዓል ያዘጋጁት ምግብ ብቻ ሳይሆን እነርሱም ሲዋቡ በዓሉ ይደምቃል። ለዚህ ነው ሴቶችን ለማስዋብ ቅድሚያ የሰጠሁት›› የሚሉት ወይዘሮ ፋና የሴቶች ውበት ሳሎን ከመክፈታቸው በፊትም በኪነጥበቡ ውስጥ ስለነበሩ የሥራ ዘመናቸው ሁሉ ሌሎችን በማስደሰት ነው ያሳለፉት። እራሳቸውን ለሌሎች ደስታ እንደተፈጠሩ አድርገው ነው የሚያዩትም፡፡

ለሌሎች ደስታ ለመፍጠር እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በሥራቸው ያሉ ሠራተኞች ጭምር ተባባሪያቸው እንደሆኑ ይገልጻሉ። ሙሉ ጊዜያቸውን ለደንበኞቻቸው ቢሰጡም ለበዓል የሚጠበቅባቸውን የሴትነቱ ጉዳይም ቢሆን እንደማይቀርባቸውና በሙያ እንደማይታሙ አጫውተውናል። በቤት ውስጥ በሥራ መተጋገዙ እንዳለና እርሳቸውም አጋዥ እንዳላቸው ነው የነገሩን። የበዓሉ ዕለትም ለበዓል የተዘጋጀውን ምግብና የሚጠጣውንም በመያዝ በሥራቸው ቦታ ከሠራተኞቻቸው ጋር ደመቅ አድርገው እንደሚውሉና እግረ መንገዳቸውንም ደንበኛ ከመጣ ሥራቸውም እንደማይስተጓጎል ነው የገለጹልን፡፡

ወይዘሮ ፋና ሥራቸው በደማቸው ውስጥ የገባ ያህልን ነው በነበረን ቆይታ የተረዳነው። በሥራቸው የበለጠ ደንበኞቻቸውን ለማስደስት እንዲያስችላቸው ከኪራይ ቤት ወጥተው በግላቸው የሚሰሩበት የመሥሪያ ቦታ ለማግኘት ምኞታቸውና ፍላጎታቸው ነው። በ2016 ዓ.ም እድሉ እንዲገጥማቸው ይመኛሉ። በእናታቸው ሞት የተጎዳው አእምሯቸውም ነፃ ሆኖ አዲሱ ዓመት የሰላም እንዲሆንላቸውም እንዲሁ ተመኝተዋል፡፡

ሌላዋ ያነጋገርናት ወጣት መድኃኒት ሳይመን ትባላለች። መድኃኒት በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ ያደገች ቢሆንም ቤተሰቦችዋ የጋምቤላ ክልል ተወላጆች በመሆናቸው በዚያ አካባቢ ለበዓል የሚደረገውንም ዝግጅት የማየቱን እድል አግኝታለች። እናትዋም ስለአካባቢው ባህል ስለሚነግሯት ጠንቅቃ ታውቃለች። በመሆኑም በጋምቤላና በምትኖርበት አዲስ አበባ ከተማ ለበዓል የሚደረገውን ዝግጅትና የሴቶችን የሥራ ጫና በንጽጽር እንዲህ አጫውታኛለች፡፡

ወጣት መድኃኒት በጋምቤላ ቤተሰቦችዋ ለበዓል ስለሚያደርጉት ዝግጅት እንደነገረችኝ፤ ለበዓል ዝግጅት ሴቶች ምግብና የሚጠጣ ነገር ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ቤት ማሳመርም ይጠበቅባቸዋል። ቤት የማሳመሩ ሥራ ከባድ ነው፡፡አሮጌው ቤት ለአዲስ ዓመት አዲስ እንደሆን ስለሚፈለግ ባህላዊ የሣር ቤት ከሆነ የሣር ክዳኑ ይቀየራል። ግድግዳው በጭቃ፣መሬቱም እንዲያምር ይደረጋል። የሣር ክዳኑን ለመቀየር ካልሆነ በስተቀር ወንዶች አይሳተፉም። ሴቶች ናቸው የሚያሳምሩት። ዘመናዊ ቤትም ቢሆን ቀለም በመቀባት ለማሳመር ጥረት ይደረጋል። በመተጋገዝ የሚሰራ ቢሆንም ቤት ማሳመሩ ጊዜ የሚወስድና አድካሚ ነው፡፡

ለበዓል የሚሆን ምግብና መጠጥ የማዘጋጀቱ ሥራም የሴቷ በመሆኑ ከቀናት በፊት ጀምሮ ነው ሴቶች ሥራ የሚጀምሩት። ለበዓል የሚዘጋጀው ምግብ በአካባቢው አጠራር ‹‹ኮብ›› ይባላል። ግብዓቱ የበቆሎ ወይንም የስንዴ ዱቄት ሲሆን የራሱ አሰራር ሂደትም አለው። ለማባያ የሚዘጋጀው ደግሞ አሣ ወይንም ጎመን በሥጋ በቅቤ ነው። ጣፋጭ የሆነ ለበዓል ብቻ የሚዘጋጅ ምግብ እንደሆነ ነው መድኃኒት የነገረችን፡፡

ስለመጠጥ ዝግጅቱም መድኃኒት እንደገለጸችልን፤ መጠጡ ከሰሊጥ የሚዘጋጅ ሲሆን ሰሊጡ በባህላዊው ወፍጮ በሰው ጉልበት ተፈጭቶ በደንብ ከላቆጠ በኋላ ውሃ ውስጥ ይዘፈዘፋል። እንዲፈላም እርሾ፣ ለጣዕሙ ደግሞ ስኳር ይገባበታል። በዚህ መንገድ ለተወሰነ ቀን ከቆየ በኋላ ውሃው ጠልሎ ለመጠጥ ይዘጋጃል። በአካባቢው አጠራርም ‹‹ከኛ›› ይባላል። የበዓል እለትም ዘመድ፣ ጎረቤት ተጠርቶ በጋራ ይጠጣል ፡፡

ለበዓል የሚዘጋጀው የምግብ እና የመጠጥ ልዩነት ካልሆነ በአዲስ አበባ ከተማም ቢሆን እርሷ እንዳየችው የበዓል ዝግጅት ለሴቶች አድካሚ ነው። ቤት ማስዋቡ߹ የቤት ውስጥ የእቃ አቀማመጥ መቀየር፣ ቤቱንና የሶፋ ልብሶችን ማጠብ አለ። በምግብ ዝግጅት በኩልም ዶሮና ሥጋ ነው የሚሰራው። የበዓል ሥራን በመተጋገዝ ካልሆነ በአንድ ሰው ከባድ እንደሆነም ገልጻለች። እርስዎ ከወላጆችዋ ጋር ስለሆነች ከእህቶችዋ ጋር እናታቸውን በሥራ እንደሚያግዙ ነው የነገረችን፡፡

ሌላዋ ሃሳባቸውን የሰጡን ወይዘሮ አዜብ ይልማ ይባላሉ። ወይዘሮ አዜብም ለረጅም ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ ነው የኖሩት። በተለያየ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ቢመጡም በየትኛውም በዓል ላይ የመገኘት እድሉ አልገጠማቸውም። አሁን ላይ ግን ኑሮአቸውን በሀገራቸው አድርገዋል። 2016 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሀገራቸው የመጀመሪያ በዓላቸውም ነው።

በውጭ ሀገር ሲኖሩ ሥራቸው ከተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በመሆኑ ምግብ አዘጋጅተው በዓል ለማስመሰል እድሉ አልነበራቸውም። በልጅነት ከቤተሰብ ጋር ሆነው ለበዓል የሚደረገውን ዝግጅት በማስታወስ በመከፋት፣ ቤተሰብ ጋር ስልክ ደውለው በማልቀስ ነበር የሚያሳልፉት፡፡

ለቅሶውም መከፋቱም አልፎ ሀገራቸው ገብተው የመጀመሪያቸውን በዓል አዲስ ዓመትን ለማክበር በመጓጓታቸውም ከሳምንት በፊት ጀምሮ የበዓል ድባብ ለእርሳቸው ልዩ ነበር። ታዲያ ለበዓል ዝግጅት ድርሻቸው ምን ይሆን ብለን ስንጠይቃቸውም ሳቅ ነበር የቀደማቸው። ሙያው ጠፍቶባቸው እንደሆን ጠየቅናቸው። የልጅነቱ እንዳልተረሳና በምግብ ዝግጅቱ ትልቁን ድርሻ ባይዙም ቤት በማጽዳትና በማሳመሩ እንዳሉበት ተናግረዋል፡፡

ቤተሰባቸው ሰፊ እንደሆነና ቀደም ሲል ጀምሮ ሰፋ ባለ ሁኔታ ዝግጅት እንደሚደረግ ነው ወይዘሮ አዜብ የነገሩን። ወደኋላም መለስ ብለው እንዳጫወቱን አባታቸው በሕይወት በነበሩ ጊዜ ለበዓሉ ለእርድ የሚዘጋጀውን በግ መርቀውና ለቤተሰባቸው፣ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ቸር ተመኝተው ነው የሚባርኩት። በሀገር ባህል አልባሳት ቤተሰቡ ደምቆ በዓሉን ለማሳለፍ የነበረውን ሁኔታ በመልካም ጎኑ ያስታውሳሉ፡፡

ሴቶችና የበዓል ሥራ ጫናን በተመለከተም ወይዘሮ አዜብ እንደገለጹት፣ በዓሉ የደመቀ እንዲሆን፣ ቤቱ ጽዱ እንዲሆንና እንዲያምር ማድረግ፣ ገበያ መገብየት፣ የማጀቱ ሥራ፣ መስተንግዶው የሴቶች ድርሻ በመሆኑ ከአዘቦቱ የበዓሉ ሥራ ጫና አለው፡፡

ወይዘሮ አዜብ በውጭ በኖሩባቸው ሀገራት ለበዓል የሚደረግ ዝግጅትና በኢትዮጵያ ካለው ጋርም በንጽጽር ሲገልጹ እዛ ሥራን በሚያቀሉ ማብሰያ ስለሚጠቀሙና የምግብ ዝግጅቱም እንዲሁ እንጀራና ኮስተር ያለ ወጥ ባለመሆኑ ድካሙ ይለያያል። በኢትዮጵያ ግን ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ሴቶች ሁሉ እረፍት እንደሌላቸውና ሥራውም በአድካሚ ሂደት ውስጥ እንደሚያልፍና ሰፊ ቤተሰብ ያለው ደግሞ ዝግጅቱም ሰፊ እንደሚሆን ነው ያስረዱት፡፡

ወይዘሮ አዜብ የውጭውንም የሀገራቸውንም የበዓል አካባበር ሁኔታ የማየቱን እድል ቢያገኙም የሀገራቸው የበዓል አከባበር እንደሚያስደስታቸው ነው የገለጹት። አሁን ላይ ያለው ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ እንደቀደመው በዓልን ለማድመቅ የሚመች እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ አዲሱ ዓመት የሰላም እንዲሆን መመኘት ደግሞ ግድ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በአዲሱ ዓመት ሀገራችን ሰላም እንድትሆን፣ ሕዝቧም በፍቅር ተሳስቦ እንዲኖር ነው ምኞቴ። በዓሉን የምናከብረው፣ ልጆቻችን ተምረው ነገን ተስፋ የሚያደርጉት እኛም ሰርተን ለማደግ ሰላም ያስፈልጋል›› በማለት ሰላም ያለውን ዋጋ በማስቀደም በዓልና ሴቶችን በተመለከተ ሀሳቧን ያካፈለችን ደግሞ ወይዘሮ ሰላም ሀብቶም ትባላለች።

ሰላም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተምርቃለች። በተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ‹‹በካሜራ እይታ ውስጥ ኖዎት›› የሚሉ መልእክቶች ተለምደዋል። እሷም ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ ካሜራዎችን ከውጭ ሀገራት በማስመጣት ሥራ ላይ ነው የምትገኘው።

ወይዘሮ ሰላም እንደቀደመው የሚበላውንም የሚጠጣውንም ለማዘጋጀትና በሀገር ባህል ደምቆ በዓሉን ለማሳለፍ የኑሮው ሁኔታ ምቹ እንዳልሆነ ትገልጻለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በዓልን ማሰብ ቀርቶ የእለት ጉርስ የቸገረው ብዙ ወገን ባለበት በተለየ ሁኔታ ለበዓል ዝግጅት ማድረጉ ብዙም አልታያትም። ካላት አካፍላ ወይንም እገዛ አድርጋ ሌሎችንም አስቦ መዋሉ ላይ ሁሉም ሰው ትኩረት እንዲያደርግ ነው መልእክቷ፡፡

የኑሮ ውድነቱን ማዕከል አድርጋ በጎ ተግባሩንም ሳይቀርባት በዓሉን እንደቤቷ ለማክበር መዘጋጀቷንም ገልጻልናለች። ታዲያ በሙያው በኩልም የሚስተካከላት እንደሌለ ነው የተናገረችው ወይዘሮ ሰላም አንዳንዶቹ በእናቷ እገዛ ነው የሚሟሉት ልክ እንደ ‹‹ቴክ አዌይ›› መሆኑ ነው፡፡

ሥራውን ለማቅለልም እንደ ሽንኩርት መፍጫ ያሉ ዘመን ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ድካምን ለመቀነስ ጥረት እንደምታደርግም ነው የገለጸቸው። በዚህኛው አዲስ ዓመት ካለው ሀገራዊ ሁኔታ በዓልም ቀለል ለማድረግ ስለሆነ ፍላጎትዋ ከዚህ ቀደም ሰፋ ያሉ ዝግጅቶች እንደማይኖሩና ድካምም እንደማይኖርባት አስረድታለች፡፡

ወይዘሮ ሰላም እንደምትለው የበዓል ሥራን አድካሚነት እየተገነዘበች የመጣችው ትዳር ከያዘች በኋላ ሲሆን ቤተሰቦችዋ ጋር ከነበረችበት ጊዜ ኃላፊነቷ ጨምሯል። በቤት ውስጥ ለበዓል ዝግጅት የሚያስፈልጉትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ለበዓል ጥየቃ ወደ እርሷም፣ ወደ ባለቤትዋ ቤተሰብ ቤት መሄድ ተጨማሪ ሥራዎች ናቸው። በዓል ሥራው ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች ለረጅም ሰዓት ተቀምጠው በመብላትና በመጠጣት የሚያሳልፉት ጊዜም አድካሚ እንደሆነና የበዓል ድካም መቀነስ እንዳለበት ትገልጻለች፡፡

አሮጌ ዓመት አልፎ በአዲስ ሲተካ ሁሉም የሚጠብቀው ተስፋ አለ ወይዘሮ ሰላም ግን ‹‹ለእኔ ከአንድ ቀን ወደ ሌላኛው ቀን ስሸጋገር አዲስ ነው። የአንድ ዓመት እድሉ ሲሰጠን ደግሞ የበለጠ የተሻለ ነገር ሰርተንና ጥሩ ሆነን መገኘት አለብን ብዬ ነው የማስበው›› በማለት ሰዎች በሥራው ለማደግም ሆነ ከመጥፎ ባህሪያቸው ለመለወጥ አንድ ዓመት ሙሉ መጠበቅ እንደማያስፈልግ፣ ሰዎች በየቀኑ እየተቀየሩ መሄድ እንዳለባቸው በዚህ አጋጣሚ መልእክት አስተላልፋለች፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You