አዲስ ዓመት – አዲስ የተስፋ ፍኖት!

 ፍኖት – በብርሃን የተሞላ መተላለፊያ ነው። ብርሃናማ መተላለፊያ ደግሞ ወደ ሕልማችን መግቢያ በር፤ ወደ ሕልማችን መዳረሻ መንገድ፤ የሕልማችን መገለጫ አውድ ሜዳ/አደባባይ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አዲስ ዓመትን ስንቀበል አዲስ ሕልም ይዘን፤ አዲስ ግብ አስቀምጠን፤ አዲስ ስኬትን በመሻት ነው። ለዚህ ሕልማችን እውን መሆን፤ ግባችን መሳካት እና ስኬታችን እውን መሆን ፍኖት (በር፣ መንገድና መገለጫ አደባባይ) ያስፈልገናል።

ይህ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በመጀመሪያ ሕልሞቻችንንና መሻታችንን ይዘን የምንዘልቅበት የመግቢያ በር ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ የመሻታችን ፍኖት በር ሆኖ ያገለግለናል። ይሄ በአዲሱ ዓመት ለያዝነው ሕልምና መሻት እውን መሆን የመጀመሪያው መግቢያ በራችን ደግሞ የዓመቱ የመጀመሪያው ወር፤ ከወሩም የመጀመሪያው ዕለት መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡

በእለተ እንቁጣጣሽ የብሩህ መሻታችን ተምሳሌት በሆነ መልኩ ደምቀንና አምረን የምናሳልፈው የወርሃ መስከረም የመጀመሪያው ቀን ታዲያ፤ የዓመቱ ጉዟችን፣ የሕልማችን ከፍታ አውድ ሆኖ ይገለጣል። በዕለተ እንቁጣጣሽ የፍኖት በርነት አንድ ብለን የምንጀምረው አዲስ ዓመት በመጀመሪያው ቀን ውሏችን የምንሰንቀው ከፍ ያለ የደስታ፣ የፍቅርና የአብሮነት አቅም ለዓመቱ ጉዟችን ብርታት ሆኖ ያገለግለናል፡፡

በዕለተ እንቁጣጣሽ በርነት ሕልምና መሻታችንን ይዘን የዘለቅንበት አዲስ ዓመት ታዲያ፤ በቀጣዩቹ ቀናት፣ ሳምንታትና ወራት ዑደት ውስጥ ወደ ግባችን እንድንራመድ ያስገድደናል። ለግባችን መዳረሻ ደግሞ መንገድ ያስፈልገናል፤ ብርሃናማ መንገድ፤ በእንቅፋትና እሾህ የማይስተጓጎል መንገድ፤ በፍቅርና አብሮነት፣ በሰላምና ይቅርታ፣ በሃሴትና ፌሽታ፣ በትጋትና በጥበብ የታጀበ መንገድ፡፡

ይህ ፍኖት/መንገድ ለሕልማችን መሳካት የምንራመድበት እንደመሆኑ፤ በዕለተ እንቁጣጣሽ የገለጥነውን የአብሮ መዋልን፤ የአብሮ መብላትን፤ የአብሮ መደሰትን፤ አብሮ የመራመድን፣… በድምሩ በኅብርና በኅብረት መገለጥን ይሻል። ይሄ ኅብረት ነው ኃይልም፣ ጥበብም ሆኖ ወደ ግባችን የሚያራምደን፤ ይሄ አብሮነት ነው ወደ ብልጽግናችን በምናደርገው ግስጋሴ ፍኖት ሆኖ ከግባችን የሚያደርሰን፡፡

አዲሱ ዓመትም ይሄንን አብሮነት አብዝቶ ይሻል። ምክንያቱም አብሮነት አቅም ነው፤ አብሮነት ጥበብ ነው፤ አብሮነት አሸናፊነት ነው፤ አብሮነት ሰላም ነው፤ አብሮነት ለሰው ልጆች ሕልምና ምኞት መሳካት፤ ከፍ ላለችው ኢትዮጵያ የበለጠ ከፍታ መጎናጸፊያ ሰንደቅ ነው። በመሆኑም ዛሬ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያው ዕለት ላይ ሆነን የምናሳያው አብሮነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ በቀጣዮቹ ቀናት፣ ሳምንታትና ወራት ጅረት ውስጥ የማይቋረጥ ወንዝ ሆኖ መፍሰስ ይኖርበታል፡፡

ይህ ሲሆን ወደ ሦስተኛው ፍኖት እንደርሳለን። ሦስተኛው ፍኖት፣ ሜዳ ወይም አደባባይ ነው። በኅብር ደምቀን ከሕልማችን ጋር በመስከረም በር እንደዘለቅን ሁሉ፤ በኋላም በቀናት ድልድይነት በተገነባው መንገድ በወል ተራምደን ወደ ግባችን ካመራን፤ በመጨረሻ ግባችንን መትተን በስኬት ሜዳ/ አደባባይ መዋላችን አይቀሬ ነው። ምክንያቱም በፍቅር የተከፈተ በር፤ በአብሮነት የተጀመረ መንገድ መዳረሻው ከከፍታ ነውና፡፡

እናም ዛሬ ወደ ሕልማችን መዳረሻ መስከረም አንድ ላይ ከፍተን የገባንበት እና መንገድ የጀመርንበት አዲሱ የ2016 ዓመተ ምሕረት፤ ቀን ቀንን እየተካ፣ ሳምንታት ወራትን እየወለዱ አዲስ ብለን የተቀበልነውን ዓመት አሮጌ ብለን መሸኘታችን አይቀርም። ይሄ ሲሆን ደግሞ ሕልምና መሻታችን በግቡ ይመዘናል፤ ከስኬቱም አንጻር ይወራረዳል፡፡

ታዲያ የዛኔ፣ ሕልመኞች ብቻ ሆነን ልንገኝ አይገባም። ይልቁንም የምናልም፤ ለሕልማችንም የምንተጋ፤ ካስቀመጥነው ግብ ደርሰንም በስኬታችን የምንገለጥ ልንሆን የተገባ ነው። ለዚህም ነው ፍኖት የሚያስፈልገን። ምክንያቱም ፍኖት ወደ ሕልማችን መግቢያ በር ነው፤ ፍኖት ወደ ግባችን መራመጃ መንገድ ነው፤ ፍኖት ሕልማችን ሰምሮ በስኬት ሜዳ ወይም አደባባይ የምንገለጥበት አውድም ነው፡፡

በመሆኑም አዲሱ ዓመት ሕልም ብቻ ሳይሆን ፍኖትም ሊኖረን ይገባል። ይሄ ፍኖት ደግሞ የሰላም ፍኖት ነው፤ የአብሮነት ፍኖት ነው፤ የይቅርታ ፍኖት ነው፤ የመተሳሰብ ፍኖት ነው፤ አንዳችን የአንዳችን አለኝታ የመሆን ፍኖት ነው፤ በኅብር የደመቀ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የማድረግ ፍኖት ነው፤ ስለ ሕዝብና ስለ ሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ራስን አሳልፎ የመስጠት ልዕልናን የመላበስ ፍኖት ነው፤ ተነጋግሮ የመግባባት፣ ተመካክሮ ለይቅርታ የመዘጋጀት ሰብዕናን የመጎናጸፍ ፍኖት ነው፡፡

ይሄ ፍኖት ነው ኢትዮጵያን የሚያልቃት፤ ይሄ ፍኖት ነው ኢትዮጵያውያንን በክብርና በሞገስ የሚገልጠው፤ ይሄ ፍኖት ነው በአዲስ ዓመት ልናሳካ የምናልማቸውን ነገሮች ከግብ እንድናደርስ አቅም የሚሆነው፤ ይሄ ፍኖት ነው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን በማድረግ ጉዞው የጥበብም፣ የሞራልም ስንቅ የሚሆነው። አዲሱ ዓመትም በአዲስ ሕልም፣ በአዲስ መዳረሻ እና በአዲስ ስኬቶች ሊገለጥ የሚችለው ይሄ ሲሆን ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ዛሬ አንድ ብለን የጀመርነው የ2016 ዓመተ ምህረትም ከቀን ቀመርነት የተሻገረ ነው። ምክንያቱም ዓመቱ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የብዙ ተስፋዎች ዓመት ነውና። የመልማት ዓመት ነው፤ የሰላም ዓመትም ይሆንልናል፤ የመመካከርና የመግባባት ዓመትም ነው፤ በቂምና በቀል ፈንታ ለፍቅር ተሸንፎ በይቅርታ የመሻገር ዓመታችንም ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊው፣ ኢኮኖሚያዊው፣ ፖለቲካዊው፣ ዲፕሎማሲያዊው መስክ ብዙ ሠርተው ብዙ የሚያተርፉበትም ነው። በጥቅሉ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ፍኖት ሆኖ የሚገለጥ ነው!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You