አዲስ ዓመት – በትውልድ መካከል

እንዴት ናችሁ ልጆች? ዛሬ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነው። እንኳን አደረሳችሁ? ‹‹እንኳን አብሮ አደረሰን!›› አላችሁ ልጆች? ጎበዞች፡፡ ልጆች በሁሉም ሠዎች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ አዲስ ዓመት ነው። አዲስ ዓመት ሲመጣ ምድሪቱ በአደይ አበባ አምራ እና ደምቃ ትታያለች፡፡ የክረምት ወቅት ተራውን ለበጋ ይለቃል። ብዙዎችም መልካም መልካሙን በመመኘት፣ ቤታቸውን ቀጤማ በመጎዝጎዝ ያሳምሩታል፡፡ ዶሮ፣ በግ፣ ፍየል፣ ድፎ ዳቦ … ብቻ ቤት ያፈራውን የተለያዩ ምግቦች እና መጠጦችን በማዘጋጀት ቤተሰብ ሰብሰብ ብሎ ያከብራል፡ ፡ እንዲሁም ዘመድ ከዘመዱ ይጠያየቃል፡፡ ጎረቤት ከጎረቤቱ ጋር በጋራ በመሆን ያከብሩታል፡፡ ልጆችም ከአብሮ አደጋቸው እና ከቤተሰባቸው ጋር ሰብስብ ብለው በመጫወት እና በመዝናናት በድምቀት ያከብሩታል፡ ፡ እናንተም ጋር በተመሳሳይ መልኩ እንደሚከበር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

ልጆች የአዲስ ዓመት የበዓል አከባበር ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በዛሬ ጽሑፋችንም አዲስ ዓመት ከዚህ በፊት ያከበሩትን እና ዛሬ ላይ ያለውን አከባበር በተወሰነ መልኩ እናቀርብላችኋለን፡፡

አቶ ታምራት ሰለሞን የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡ አዲስ ዓመት ለእርሳቸው ብዙ የልጅነት ትዝታ ያለው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለአዲስ ዓመት የ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ሥዕል ለማዞር ሥራውን የሚጀምሩት ከበዓሉ በፊት ነበር፡፡ ሥዕሎችን በመሳል እንዲሁም የተለያዩ ቀለማትን በመቀባት ያዘጋጃሉ። የበዓሉ ቀን በጠዋት ተነስቶ ለሠፈሩ ሰዎች ‹‹እንኳን አደረሳችሁ››

 እያሉ ያዘጋጁትን ይሰጣሉ፡፡ ስዕሉን አዙረው ባገኙት ገንዝብ ማስቲካ፣ ከረሜላ፣ ፊኛ (አፉፋ) እና ሌሎች መጫወቻዎችን በመግዛት በደስታ ሲያሳልፉ እንደ ነበር ያስታውሳሉ፡፡ ወንድ ልጃቸውም እርሳቸው እንዳከበሩት እንዲያከብርና የማይረሳ ትዝታ ኖሯት ለሌሎች እንዲያስተላልፍ የአቅማቸውን ያህል እያስተማሩት ይገኛሉ፡፡

ሌላ ሠው እናስተዋውቃችሁ፡፡ ሃና መኮንን ትባላለች። የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ናት፡፡ እሷም እንደ አቶ ታምራት ሁሉ አዲስ ዓመት ላይ ልዩ ትዝታ አላት። ‹‹አበባ አየሽ ወይ››ን ለመጨፈር ከአብሮ አደጎቿ ጋር ከበሮ በማስገዛት፣ ከበሮውንም ማን መምታት እንዳለበት ከተመራረጡ በኋላ፤

አበባ አየሽ ወይ፣ ለምለም

አበባ አየሽ ወይ፣ ለምለም

ባለእንጀሮቼ

ግቡ በተራ

እንጨት ሰብሬ

ቤት እስክሠራ

እንኳን ቤት እና

የለኝም አጥር

እደጅ አድራለሁ

ኮከብ ስቆጥር

ኮከብ ቆጥሬ

ስገባ ቤቴ

ትቆጣኛለች

የእንጀራ እናቴ

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ …

 በማለት ጭፈራቸው ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም፤

ከብረው ይቆዩ ከብረው፣

በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው፣

ሰላሳ ጥጆች አስረው፣

ከብረው ይቆዩ ከብረው፡፡

በማለት ይመርቃሉ፡፡ ጨፍረው ያገኙትን ገንዘብ በመከፋፈል ከረሜላ፣ የጸጉር ማስያዣ (ጌጣ ጌጥ) እና ሌሎች ነገሮችን በመግዛት እንደሚያሳልፉትም ታስታውሳለች፡፡ የበዓሉ ቀንም አዲስ ልብስ በመልበስ እና ጸጉሯን በመተኮስ አምሮባት በዓሉን በደስታ እንደምታሳልፍ ትገልጻለች፡፡

ሃና አዲስ ዓመትንም ይሁን ሌሎች በዓላት ማክበር ደስ ይላታል፡፡ ባህሉ እየተቀዛቀዘ ነው በሚል ቁጭት፤ ልጆቿ የቅርብ ጎረቤት እንዲሁም አያቶቻቸው ጋር ሄደው ‹‹አበባ አየሽ ወይ›› እንዲሉ ከበሮ በመግዛት፣ ዜማ እና ግጥሙን በማለማመድ እንዲጨፍሩ ታደርጋለች፡፡ ወንድ ልጇም ሥዕል አዘጋጅቶ “እንኳን አደረሳችሁ” እንዲል ታበረታታዋለች፡፡ በቤተሰቦቻቸው እና ጎረቤቶቻቸውም ‹‹እደጉ፤ ተመንደጉ፡፡ ዓመት ዓመት ያድርሳችሁ፡፡›› ተብሎ መመረቅ ትልቅ እድል እና የሚበረታታ ባህል እንደሆነ ትናገራለች፡፡

 ኤፍራታ አለሙ የአስር ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ ሦስት ወንድሞች አሏት፡፡ እርሷ አበባ አየሽ ወይ የምትጨፍረው ለብቻዋ ነው፡፡ ለምን? ብትሉ ጓደኞቿ መጨፈር ባለመፈለጋቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አያቶቿ ቤት ስትሄድ ከአጎቶቿ እና አክስቶቿ ልጆች ጋር በመጨፈር በደስታ እንደምታሳልፍ ትገልጻለች፡፡

የ 11 ዓመቱ ናታን ስለሺህ የእንኳን አደረሳችሁ ሥዕሎቹን በማዘጋጀት ለጎረቤቶቹ ይሰጣል፡፡ እነርሱ አካባቢ ብዙ ሠዎች ስለሚኖሩ ብዙ ሥዕሎቹን አዙሮ ከጨረሰ በኋላ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት እና ከጓደኞቹ ጋር በደስታ ስለሚያሳልፍ አዲስ ዓመት ሲመጣ በጣም ደስተኛ እንደሚሆን ይናገራል፡፡

አቶ ሰለሞን እና ሃና የአዲስ ዓመት አከባበር የተለየ ነገር እንዳለው ያምናሉ፡፡ በዓል አከባበሩ ለልጅ ልጅ እንዲተላለፍ ከተፈለገም ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከአካባቢያቸው ሳይርቁ በመጨፈር፤ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ››ም በመባባል በዓሉን እንዲያከብሩት መደረግ እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

ልጆች እናንተስ ሥዕል እያዞራችሁ፤ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ለማለት አላሰባችሁም? ታዲያ ከሰፈራችሁ ብዙም መራቅ የለባችሁም፤ እሺ ልጆች፡፡ ‹‹አበባ አየሽ ወይ›› የምትጨፍሩ ሴት ልጆችም በተመሳሳይ ከሠፈራችሁ ብዙም ሳትርቁ እና መንገዶችን ስታቋርጡ በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ ሌላው፣ ልጆች በበዓል ወቅት ስትመገቡ በልክ እና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት መዘንጋት የለባችሁም። እሺ ልጆች፡፡

ልጆችዬ፣ ለዛሬ በመልካም ምኞት እንሰነባበት አይደል?። አዲሱ ዓመት የስኬት፣ የጤና እና የደስታ ይሁንላችሁ!!!

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን     ጳጉሜን  5 ቀን  2015 ዓ.ም

Recommended For You