የአዲሱ ትውልድ የአትሌቲክስ ነፀብራቅ

70 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች ከፍ እያደረገ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ከታሪካዊው ፈርቀዳጅ ጀግና አትሌት አበበ ቢቂላ አሁን እስካለው የትውልድ ሰንሰለት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያጀገነ ኮከብ ነጥፎ አያውቅም። በምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ባርሴሎና ኦሊምፒክ ላይ የተቀጣጠለው የድል ችቦም አሁንም ድረስ ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሰ ኢትዮጵያን ያኮሩ አያሌ ጀግና አትሌቶችን መፍጠር ችሏል።

በቅርቡ በተካሄደው 19ኛው የቡዳፔስት ዓለም ቻምፒዮና ከተገኙ ሜዳሊያዎች መካከል አንዱ በ 1ሺ 500 ሜትር ሴቶች የተመዘገበው የብር ሜዳሊያ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ሜዳሊያ ደግሞ የዚህ ትውልድ የአትሌቲክስ ነፀብራቅ በሆነችው በ21 ዓመቷ ወጣት አትሌት የተመዘገበ ነው። በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫዎች ስኬት የገነነችው ኢትዮጵያ፤ በዓለም ቻምፒዮና የ 1500 ሜትር ውድድር 1 የወርቅ 2 የብር እና 2 የነሃስ ሜዳሊያዎች በታሪኳ ተመዝግበዋል፡፡ አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ፣ ገንዘቤ ዲባባ እና ጉዳፍ ጸጋይ የሜዳሊያዎቹ ባለቤቶች ሲሆኑ፤ አትሌት ድርቤ ወልተጂም ከሰሞኑ የተቀላቀለች የዚህ ትውልድ ኮከብ ነች። ይህች ወጣት ኮከብ የአዲሱ ትውልድ ምሳሌና የወደፊቱም ተስፋ ናት።

ቀደም ሲል በ800 ሜትር የምትታወቀው አትሌት ድርቤ ገና በ16 ዓመቷ ነበር በዓለም ከ18 ዓመት በታች የዓለም ቻምፒዮና ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለችው። የሪዮ ኦሊምፒክና የኦሪጎኑን የዓለም ቻምፒዮና ጨምሮም በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተስፋ ሰጪ አቅም እንዳላት አሳይታለች። ባለፈው ዓመት በፖላንድ በተካሄደ ዳይመንድ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ ተካፍላም አትሌት ጉዳፍ ጸጋይን በመርታት ጭምር በርቀቱ ያላትን ተስፋ አሳይታለች፡፡ በዚሁ ቀጥላም በዓለም ቻምፒዮና መድረክ ከጠንካራ አትሌቶች ጋር ተፎካክራ ሜዳሊያ ልታጠልቅ ችላለች፡፡ ይህንን ተከትሎም ‹‹ከውድድሩ አስቀድሜ ሰርቼበት ስለነበር በውድድሩ ውጤት ላመጣ ችያለሁ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፡፡ ይህን ውጤት በቀጣይ ወደ ወርቅ ልቀይር እንደምችልም አሳይቶኛል›› ትላለች ወጣቷ ኮከብ።

በዘንድሮው ቻምፒዮና የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ኬንዊቷ ፌይዝ ኪፕየጎን እንዲሁም በዓለም ቻምፒዮና 1500 ሜትር 1 የወርቅ እና 2 የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ሲፈን ሃሰን መሳተፋቸው ውድድሩ ከባድ ግምት እንዲያገኝ አድርጎት ነበር፡፡ ውድድሩ ከተጀመረም በኋላ የሁለቱ አትሌቶች ፉክክር በእጅጉ ቢጠበቅም ዙሩን በተመሳሳይ ብቃት ስታሸፍን የቆየችው ወጣቷ አትሌት ድርቤ የሜዳሊያ ፉክክር ማድረጓ ያልታሰበ ክስተት ሆኗል። በአስደናቂ ብቃትም ወጣቷ ኮከብ ሆላንዳዊቷን አትሌት ሲፋን ሀሰንን አስከትላ መግባት ችላለች፡፡

ድርቤ ውድድሩን ስታስታውስ ‹‹ከእነዚህ አትሌቶች ጋር መሮጤ ሞራል ሆኖኝ ነበር፤ ያለሁበትን ደረጃ ሊያሳየኝ የሚችል ውድድር በመሆኑ ደስተኛ ነበርኩ›› ትላለች፡፡ በአትሌቷ የተገኘውን የብር ሜዳሊያ በርካቶች ‹‹ከወርቅ እኩል የሆነ›› በሚል ነበር የሰየሙት፡፡ ይህም የድሉን ደረጃ የሚያሳይ ሲሆን፤ ድርቤ ሜዳሊያውን ከእጇ ማስገባቷንና በዚህ ርቀት ከዓለም ምርጥ አትሌቶች ተርታ መሰለፏን ስታረጋግጥ የተሰማት ስሜት ምን እንደሚመስልም አብራርታለች፡፡ ‹‹አብረውኝ የሮጡት አትሌቶች ልምድ ያላቸውና በበርካታ ውድድሮች ላይም በርቀቱ ስኬታማ መሆን የቻሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነሱ ጋር ተፎካክሬ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችያለሁ፡፡ በእርግጥ ውጤታማ ልሆን የቻልኩት ዝግጅት በማድረጌ ብቻም ሳይሆን ያጋጥሙኝ የነበሩትን ችግሮች በጽናት መወጣት በመቻሌም ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሞራል የሚሰጥና በቀጣይ እንዴት መሮጥና ውጤታማ መሆን እንደምችል ያሳየኝ ሆኗል። የሁልጊዜ ምኞቴ በዚህ ርቀት በዓለም አቀፍ ውድድር ለሀገሬ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ነበር፤ እንዳሰብኩትም ተሳክቶልኛል፡፡ ይኸውም ከዚህ በላይ መሮጥ እንደምችልና ጥንካሬዬንም የሚያረጋግጥ ነው›› ብላለች፡፡

ከማይነጥፈው የኢትዮጵያ አትሌቶች የትውልድ ጅረት ውስጥ የተገኘችው እንቁዋ አትሌት ለበርካቶች አዲስ ተስፋን ያሳየች ሆናለች፡፡ በርቀቱ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ውጤታማነት እንደምትመለስ ያስመሰከረች ሲሆን፤ በቀጣይም እንደ ጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ለሀገሯ ታሪክ ማስመዝገብ ህልሟ መሆኑን ትናገራለች። በመጪው ኦሊምፒክ እንዲሁም ከዚያ በኋላ በሚኖሩ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርቀቱ ነግሳ ለመቆየት ጠንክራ እንደምትሰራም ቃል ገብታለች፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን     ጳጉሜን  5 ቀን  2015 ዓ.ም

Recommended For You