የአምራች ዘርፉን የቦታ እጥረት የመፍታት ቁርጠኝነት

ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ ሥፍራ እንዳላቸው ታምኖባቸው በትኩረት እየተሰራባቸው ከሚገኙ አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው። በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ እስከ አሁን በግብርና የተያዘውን ሥፍራ በሂደት እንዲይዝ የሚጠበቀውም ይሄው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው።

ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎም በሀገሪቱ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ ከፓርኮቹ ውጭም የግሉ ዘርፍ በርካታ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት ምርቶቹን በማምረትና ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። በዚህም ዘርፉ ለሀገር ገቢ እያመነጨ፣ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል እየፈጠረ ይገኛል። በሀገር ውስጥ የሚያስፈልጉ ምርቶችን እያመረተ ከመሆኑ ባሻገር ተኪ ምርቶችን እያመረተ የውጭ ምንዛሬ እያዳነ ነው።

የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ከሚካሄድባቸው መካከል የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ልማት አንዱ ነው። ዘርፉ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃጨርቅ፣ በብረታ ብረት፣ በእንጨት፣ ወዘተ ሥራዎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ያሉበት ነው። በእዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎችና ኢንዱስትሪዎች ነገ የሀገሪቱን ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሚቀላቀሉ ናቸው።

ይህ ለሀገሪቱና ለዜጎቿ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ዘርፍ ከቦታ፣ ከብድር፣ ከመሠረተ ልማት፣ ከገበያ እና ከመሳሰሉት እጦት ጋር በተያያዘ እየተፈተነ ይገኛል። ይህን ችግር ለመፍታት በሀገር እንዲሁም በክልሎች ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ ተግዳሮቶች የአዲስ አበባ ከተማም ፈተና ናቸው። በተለይ የማምረቻ ቦታ ችግር በአምራቾች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያሳድር ቆይቷል። ይህን የማምረቻ ቦታ ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በርካታ የመሥሪያ ቦታዎችን በዘርፉ ለተሰማሩ ወገኖች እያስተላለፈ የቆየ ቢሆንም ችግሩ ግን አልተቀረፈም።

ከተማ አስተዳደሩ ይህን ችግር ለመፍታት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ እስከ ዛሬ ከተሰሩት የኢንዱስትሪ ማዕከላት የተለየ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ክላስተር እየገነባ ይገኛል። የኢንዱስትሪ ክላስተሩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ማምረቻነት የሚውል ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ፣ ኢንተርፐራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ እንዳሉት፤ በከተማዋ ከዘጠኝ ሺህ 559 በላይ የሚሆኑ ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ያሉ አምራች ኢንተርፐራይዞች እና ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። ቢሮው ለሁሉም ኢንዱስትሪዎች በየእድገት ደረጃቸው፣ በአቅማቸው እና በፍላጎታቸው መሠረት ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከሚታዩት ማነቆዎች መካከል የእውቀት፣ የክህሎት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች፣ የቴከኖሎጂ ሽግግር በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን የሚሉት ይጠቀሳሉ። ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግር አለባቸው፤ ግብዓት በወቅቱ አያገኙም፤ የመሥሪያ ቦታ አቅርቦት አለመኖርም በስፋት ይታይባቸዋል።

እነዚህ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ አምራቾችን ማበረታታት፣ ያሉባቸውን ማነቆዎች በሙሉ መፍታት ሰፊ ሥራ መሥራትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ከመሠረተ ልማት አኳያ እና በአምራች ዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመቀነስም የመሠረተ ልማት ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆናቸውንም አቶ ኢዘዲን ጠቅሰው፣ ባለፈው ዓመት ከተነሱት ማነቆዎች ትልቁ የመሥሪያ ቦታ ችግር መሆኑን አስታውሰዋል።

አቶ ኢዘዲን ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩ አምራች ኢንተራፕራይዞችና ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የሆነ የመሥሪያ ቦታ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ይሄንን ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ባሳየው ከፍተኛ ቁርጠኝነት ርምጃ ተወስዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በከንቲባ አዳነች አቤቤ አስጀማሪነት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ክላስተሩ ግንባታ በሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሎት አንድ እና ሎት ሶስት በሚል እየተካሄደ ይገኛል። በ2015 ዓ.ም የተጀመረው የዚህ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህም ቢያንስ ከ800 በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የሚይዝና ትልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የተወሰደበት ግንባታ ነው።

ኃላፊው የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማዕከሉ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተሻሻሉት ኢንዱስትሪዎች እና ኢንተርፕራይዞች ወደዚህ ማዕከል የሚሸጋገሩበት መመሪያ ወጥቶ እንዲሸጋገሩ የሚደረግ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ክላስተሩ ላይ ከወራት በፊት የጋዜጣው ሪፖርተር ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ክላስተር ግንባታ አስተባባሪ ኢንጂነር ታደሰ ለማ በወቅቱ እንዳሉት፤ ግንባታቸው እየተፋጠነ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር እስከዛሬ ከተሰሩት የተለየ፣ ግዙፍና ዘመናዊ ነው። ካላስተሩ ሎት አንድ፣ ሁለት እና ሦስት በሚል በሶስት ተከፍሎ ነው እየተካሄደ ያለው።

ሎት ሦስት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የተበጀተለትና በሁለት ነጥብ አራት ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው፤ ስድስት ሕንጻዎችንም ይይዛል። ከነዚህ ስድስቱ ሕንጻዎች መካከል ሦስቱ ለእንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ የሚውሉ ሲሆን፣ ሦስቱ ደግሞ ኬሚካል እና ፕላስቲክ ለማምረት ይውላሉ።

ሎት አንድ ደግሞ በአንድ ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር ላይ የሚያርፍ መሆኑን ኢንጂነር ታደሰ ጠቁመው፣ ጂ+4 የሆኑ አራት ሕንጻዎችን የሚያካትት ነው ብለዋል። ሕንጻዎቹ ለአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ ማምረቻነት ታሳቢ ተደርገው እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ሼዶቹ ለእንጨትና ብረታ ብረት፣ ለኬሚካልና ፕላስቲክ እንዲሁም ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ከመዋል ባሻገር ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የኤሌክትሮኒክስ እና መድኃኒት ፋብሪካ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም ለኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻነትም ይውላሉ። በከተማዋ ኢንዱስትሪያሊስቶች በጥናት የተለዩ የኢንዱስትሪ ስብስቦችን ይይዛሉ። ከኢንዱስትሪ በተጓዳኝ አገልግሎቶችን ሊሰጡ የሚችሉ ማዕከላትንም ያካትታሉ።

ፕሮጀክቱ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቱ ከተማ አስተዳደሩ ለኢንዱስትሪ የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ብለው ነበር። በከተማ አስተዳደሩ በጀት እና እቅድ የተገነባ የመጀመሪያው ነው ብለዋል። የፕሮጀክቱ ፋይዳም ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባት እንዲችል አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ቃል ገብተዋል።

ክላስተሩ የማምረቻ ቦታ ችግርን ከመቅረፍ ጀምሮ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘት፣ ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ በዘርፉ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ተስፋ ተጥሎበታል።

አቶ ኢዘዲን ክፍለ ከተሞችም በተመሳሳይ መልኩ ከሥራ እድል ፈጠራ ወደ አምራችነት እንዲገቡ በርካታ ሼዶችን መገንባታቸውን ጠቁመው፣ ይህም በየደረጃው ትልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የተወሰደበት እንቅስቃሴ መሆኑን ነው ያስታወቁት። እንደ መብራት መሠረተ ልማት ያሉትን በማሟላት በኩልም ብዙ መሠራቱን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ትራንስፎርመሮች መስመር ማሻሻል ሥራ መሠራቱን ኃላፊው አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ በግብዓት፣ በኃይል፣ በመሥሪያ ቦታ ችግሮች ላይ ከ2ሺ400 በላይ ከጥቃቅን እስከ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ችግር እንዳለባቸው ተለይቶ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ቢያንስ ከ77 ከመቶ በላይ ችግራቸው እንዲፈታ ማድረግ መቻሉንም ነው የጠቀሱት፤ ችግሩ የነበረባቸው ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተው የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ፣ ችግራቸው ከበድ ያለው ቀሪዎቹ ኢንዱስትሪዎች ጉዳይ ደግሞ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

አምራቾች /ኢንዱስትሪዎች/ የመሥሪያ ቦታ ከተመቻቸላቸው ብዙ የሥራ እድል መፍጠር እንዲሁም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚችሉ ኃላፊው ጠቅሰው፣ የኃይል መቆራረጥ ባይፈጠር በፈረቃ እንደሚሰሩ እና ይበልጥ አምራች እንደሚሆኑም ነው የገለጹት። ቦታ መጨመር ሳያስፈልግ እዛው ምርታማነትን መጨመር እና የሥራ እድል ፈጠራን ማሳደግ እንደሚችሉም ተናግረዋል። የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከተመቻቸ አምራቾቹ ኢንዱስትሪያቸው ሳይቆም በውጭ ያሉ ግብዓቶችን በመግዛት ብቻ የተሻለ ማምረት እንችላለን የሚል ሀሳብ እያቀረቡ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል። የሰለጠነ የሰው ኃይልና ግብዓት ወቅቱን ጠብቆ ይቅረብ የሚሉ ጥያቄዎችንም እያነሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አምራች ኢንተርፕራይዞቹ ለማደግ ያላቸው ፍላጎት እየታየ እና እየተመዘነ በየዓመቱ የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ኢዘዲን ጠቅሰዋል፤ ባለፈው ዓመት 84 በዚህ ዓመትም ከ260 በላይ ከአነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። በ2014 ዓ.ም 100 እና ከ100 በላይ ሠራተኞችን የመያዝ አቅም ካላቸው ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ያደጉት ሁለት ብቻ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ በ2015 ደግሞ ከ90 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያላቸውን 12 ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። ይህም ዘርፉ በየጊዜው ዕድገት እያሳየ እንደሚያመለክት ጠቅሰዋል።

መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪውን /ማኑፋክቸሪንጉን /የሚደግፈው፣ እንደ ኃይል አቅርቦት ያሉትን መሠረተ ልማቶችን የሚሰራው በዋናነት የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት መሆኑን አቶ ኢዘዲን ይገልጻሉ። ሌሎች ሀገሮችም ከበለፀጉት ሀገሮች ተርታ የሚሰለፉት በኢንዱስትሪ ሲያድጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአዲስ አበባ ከተማም ከተሜነት እና ኢንዱስትራላይዜሽን አብሮ ተሳስሮ እንዲሄድ ራዕይ ተቀምጦ እየተሰራበት ይገኛል። ይህ በመሆኑም በገቢ ምርትም፣ በወጪ ምርትም የገቡ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን በማሻሻል ሰፊ ለውጦች እያመጡ ይገኛሉ ይላሉ።

ቢሮው ዛሬ እየተከበረ ያለውን የአምራችነት ቀንን “ከሸማችነት ወደ አምራችነት” በሚል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር ጠቅሰው፣ በዚህም አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እና የገበያ ትስስሩን ለማጠናከር የሚያግዙ ባዛሮች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመትም የአምራችነት ቀን መከበሩን ኃላፊው አስታውሰው፣ በዘንድሮው የአምራችነት ቀን እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ለመሥራት ጭምር ያለንን የአምራችነት አቅም በውል በመረዳት በሀገር ውስጥ የተመረቱ የኢትዮጵያ ምርቶችን በበዓል ባዛሮች በማስተዋወቅ ያሉንን እድሎች እና አቅም ለማስገንዘብ ነው ብለዋል። በዚህም አምራቹን በማበረታታት ከዓመት ዓመት የመሠረተ ልማትና የምርት አቅም እየጨመረ እንዲመጣ እገዛ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም እና በሀገር ውስጥ ምርት መኩራት እንዲችሉ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አንዱ በበዓላት ወቅት በየክፍለ ከተሞቹ የሚካሄደው ባዛር መሆኑን ጠቅሰዋል። በዋጋም በጥራትም የሀገር ውስጥ ምርት የተሻለ መሆኑን ለማህበረሰቡ ለማስገንዘብ ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

አምራችነትን ለማበረታታት ከሚደረጉ ጥረቶች ባሻገር ምርቶቹም በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲታወቁና ተፈላጊነት እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ የባሀል አልባሳት፣ የጋርመንት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ እና ሌሎች ምርቶች ትልቅ የገበያ እድል እንዳላቸው አስታውቀዋል። ይህን ገበያ ለማግኘትም ተወዳዳሪነት ያለው በጥራት የተሻለ የሀገር ውስጥ ምርት ማምረት ከተቻለ አምራቹም ሕዝቡም ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ብለዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You