ኮከብ ስፖርተኞችን በየፈርጁ ማፍራት የቻለው አካዳሚ

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በይፋ ተመርቆ ስራውን ከጀመረ እነሆ አስር ዓመታት ተቆጥረዋል። በሀገሪቱ ብቸኛና የመጀመርያው የስፖርት አካዳሚ ሆኖ ከተመሰረተበት 2005 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በማስጠራትና ውጤታማ የሆኑ ወጣት ስፖርተኞችን ማፍራቱን ቀጥላል። በተጨማሪም በስፖርቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የጥናትና ምርምር እንዲሁም የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች 172 ሰልጣኞች¬ን በመያዝ ስልጠናውን የጀመረው አካዳሚው ከጊዜ ወደ ጊዜ የምልመላ ሂደቱን እና የሰልጣኞቹን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ውጤታማና ወጣት ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈራ ይገኛል።

በእግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ቦክስ፣ ውሃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ብስክሌትና አትሌቲክስ ስፖርቶች ውጤታማና የኢትዮጵያን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ማውለብለብ የቻሉ አትሌቶችን አበርክቷል። ለሀገር፣ አህጉርና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአእምሮ የላቁ እንዲሁም በስነምግባር የታነፁ ወጣት ስፖርተኞችን በማፍራት ተስፋ ሰጪ ቁመና ላይ ይገኛል፡፡

አካዳሚው ከ2008 ዓ.ም እስከ 2012 ዓም በሀገር ውስጥ ውድድሮች ባደረገው ተሳትፎ በአትሌቲክስ 268 ሜዳሊያዎችን እና በርካታ ዋንጫዎችን ወስዷል። በውሃ ዋና 97 ሜዳሊያና 2 ዋንጫ፣ በቦክስ 19 ሜዳሊያና 1 ዋንጫ፣ በወርልድ ቴኳንዶ 5 ሜዳሊያ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና ብስክሌት 7 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብም ችሏል። በተጠቀሰው ዓመት ውስጥ አካዳሚው በእነዚህ የስፖርት ዓይነቶች በድምሩ 129 ስፖርተኞችን ለብሄራዊ ቡድን ማስመረጥ የቻለ ሲሆን በእስከ አሁኑ ጉዞው በአጠቃላይ 284 ስፖርተኞችን አስመርጧል። በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የወከሉት እነዚህ ስፖርተኞች ለኢትዮጵያ በድምሩ 36 ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል። በሀገር አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃ ውጤታማነታቸውን ማስመስከር ችለዋል። ኦሊምፒክን ጨምሮ በሌሎች ዓለምአቀፍ ውድድሮች ደግሞ 21 ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል።

አካዳሚው በአሁኑ ወቅት የስልጠናውን ዘርፍ ወደ አስር ስፖርቶች ያሳደገ ሲሆን በዚህም መሰረት 684 ስፖርተኞችን ሳይንሳዊ ስልጠና በመስጠት ለተለያዩ ክለቦች ማስተላለፍ ችሏል። በዘንድሮ ዓመትም በአስሩ ስፖርቶች ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞች ለሰባተኛ ጊዜ አስመርቆ ለክለቦች ማስረከቡ ይታወሳል። የአሰላውን ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማዕከልን ጨምሮ በአስሩ የስፖርት ዓይነቶች 614 ሰልጣኞች ሳይንሳዊ ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ መኮንን ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ አካዳሚው የተቋቋመው የተተኪ ስፖርተኞችን እጥረት ለመቅረፍ ሲሆን ባለፉት በርካታ ዓመታት ታዳጊ ስፖርተኞችን ከተለያዩ አካባቢዎች በመምረጥና ስልጠና በመስጠት ለክለቦችና ለብሄራዊ ቡድን ማበርከት ተችላል። አካዳሚው የምልመላ ሂደቱን አሳድጎ በሁለት ዙሮች ብቃት ያላቸውን ታዳጊዎች መልምሎ ወደ ስልጠና እንዲገቡና ክፍተኛ ጥራት ያላቸውን ስፖርተኞች የማበርከቱን ሚና ማሳደጉንም ሃላፊው ይገልጻሉ።

ብዙ ውጤታማና አንጸባራቂ ኮከቦች መነሻቸው ይህ አካዳሚ ሊሆን ችሏል። ከነዚህ ፈር ቀዳጆችና ውጤታማ የአካዳሚው ፍሬዎች መካከል በአትሌቲክስ በ3 ሺ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያን በመወክል ውጤታማ የሆኑት ጌትነት ዋለና ለሜቻ ግርማን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ አትሌቶች ኢትዮጵያ በማትታወቅበት ርቀት ውጤት ማስመዝገብ እንድትችል በማድረግ የአካዳሚው ድርሻ የጎላ እንዲሆን አስችለዋል። ሌሎች ከአካዳሚው የተገኙ ምርጥና ኢትዮጵያን ማስጠራት የቻሉ አትሌቶች እአአ የ2022 የለንደን ግማሽ ማራቶን አሸናፊና የክብረወሰኑ ባለቤት ያለምዘርፍ የኋላው፣ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አሸናፊና የክበረወሰን ባለቤት አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ፣ የ2022 የኮሎምቢያ ካሊ ወጣቶች ቻምፒና በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ኤርሚያስ ግርማ፣ አብረሃም ስሜ፣ መልካሙ ዘገዬ፣ መልኬነህ አዘዘንና በፓራሊምፒክ ገመቹ አመኑን የመሳሰሉ ኢትየጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት የቻሉ ውጤታማ አትሌቶችን ማበርከትም ችሏል። ከአጭር ርቀት እስከ ማራቶን ድረስ እጅግ ብዙ ውጤታማ ወጣት አትሌቶችን በማፍራት ለክለቦችና ለብሄራዊ ቡድን እየመገበም ዘልቋል፡፡

በወርልድ ቴኳንዶም ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈችበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዲፕሎማ ማስመዝገብ የቻለው ሰለሞን ቱፋና የኮንጎ ብራዛቪል መላው የአፍሪካ ጨዋታዎች የነሀስ ሜዳለያ ተሸላሚ ናርዶስ ሲሳይ ተጠቃሽ ናቸው። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ደረጃ ከምትታወቅባቸው ስፖርቶች አንዱ በሆነው ብስክሌት ደግሞ ሄለን ፍሰሃ፣ ስንታየሁ መለስና ሰርካለም ታዬ ከአካዳሚው ወጥተው ኢትዮጵያን በብስክሌት በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች መወከል የቻሉ ስፖርተኞች ናቸው። በእግር ኳስ ሱሌማን ሀሚድ፣ አረጋሽ ካልሳና ሌሎች በርካታ ተጫዋቾች ከአካዳሚው በመውጣት በክለብና በብሄራዊ ቡድን ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You