ኢኮኖሚውን እንዲደግፍና ለብዙዎችም የስራ እድል በመፍጠር በርካቶችን ከድህነት እንዲያወጣ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራባቸው ካሉ ዘርፎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአምራች ኢንዱስሪው ዘርፍ ነው። የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲነሳ ታዲያ የመድኃኒትና ህክምና መሳሪዎች ዘርፍም አብሮ ይነሳል። በርግጥ በመድኃኒትና በህክምና መሳሪያዎች ዘርፍ በአብዛኛው ተሰማርተው ያሉት የውጭ ባለሀብቶች ቢሆኑም ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሀገር ውስጥ አምራቾችም ዘርፉን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ ዘ ኒው ሚሊኒየም ወርልድ ሜዲካል ዲቫይስ ማኒዩፋክቸሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰ የግል ኩባንያ ነው። ኩባንያው ከተመሰረተ አስራ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በባዮ-ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ነው። ኢትዮጵያ በዚሁ ዘርፍ ራሷን እንድትችል ትልቅ ራእይና ግብ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል። ቀደም ሲል የባዮ-ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በተለይ ደግሞ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብዓቶችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ስራ ላይ ብቻ ተሰማርቶም የቆየ ሲሆን ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ እነዚህኑ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ወደ ማምረት ተሸጋግሯል፡፡
በአሁኑ ጊዜም ምርቶቹን ለመንግስት በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ፣ ለግል ድርጅቶች እንዲሁም ለንግድ ድርጅቶች በተለይ ደግሞ ለአስመጪዎችና ቸርቻሪዎች እያቀረበ ሲሆን በአምስት አመት እቅዱ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብአቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎች ለማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል። በያዘው እቅድ መሰረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት መንግሥት ለዘርፉ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ብሎም ምርቶቹን ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ጥረት እያደረገም ነው።
አቶ ተሾመ በየነ የኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኩባንያው ከሶስት ዓመት በፊት በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቦታ ተሰጥቶት ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብዓቶችን በማምረት ላይ ይገኛል። ሙሉ በሙሉ ከውጭ ሀገር የሚገቡትን ጥሬ እቃዎችን ወደ 60 ከመቶ ዝቅ በማድረግና የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን 40 ከመቶ በመጠቀም ምርቶቹን አምርቶ ለገበያ እያቀረበ ነው።
ኩባንያው ስራ እንደጀመረ የተወሰኑ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብዓቶችን በማምረት ውጤታማ መሆን ችሏል። ይሁንና እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ከውጭ ሀገር የሚገቡ በመሆናቸውና ከአስመጪዎች ጋር በትስስር የሚሰሩ በመሆናቸው ምርቶቹን በስፋት አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ሂደት ችግሮች አጋጥመውታል።
ምርቶቹንም በእብዛኛው ለኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት፣ በአስመጪነት ለተሰማሩ የግልና የንግድ ድርጅቶች ለማቅረብ እየጣረ ቢሆንም በጨረታ ሂደት በሚታዩ የግልፅነትና ፍትሃዊነት ችግሮች ምክንያት ሀገር በቀል ምርቶቹን በሚፈለገው ልክ ማቅረብ አልቻለም።
እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ማብራሪያ፣ በ46 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ስራውን የጀመረው ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ የሚገኝ ሲሆን በዚህ የሰው ሃይሉ በዓመት 137 ሚሊዮን 800 ሺ የበሽታ መመርመሪያ ቋቶችን የማምረት አቅም አለው። ይህም መንግስት የሚፈልገውን ምርት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት ያስችለዋል፡፡
ኩባንያው በዋናነት እያመረታቸው የሚገኙ ምርቶችም አራት ሲሆኑ እነዚህም UCG /የእርግዝና መመርመሪያ መሳሪያ/፣ URS/ አስር የተለያዩ በሽታዎችን የሚገልፅ/፣ H.payroly/ የጨጓራ መመርመሪያ / እና H.payroia Ab /በደም የሚወሰድ ምርመራ/ ናቸው። ምርቶቹንም ከውጪ ከሚገባው ምርት ባነሰ ዋጋ ለገበያ ያቀርባል። እነዚህኑ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለመንግስሥትም ሆነ ለግል ተቋማት የማቅረብ አቅምም ገንብቷል፡፡
ኩባንያው የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰም የሚገኝ ሲሆን በአቅዱ መሰረት በአምስት ዓመት ውስጥ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎች ለማዘጋጀት ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይህ እቅዱ ከተሳካ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት መንግስት ለዘርፉ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ተስፋ ሰንቋል። ምርቶቹንም ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትም ውጥን ይዟል፡፡
የህክምና መሳሪያዎችንና ሌሎች ለህክምናው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ እያመረቱ ለነዚሁ ግብዓቶች የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስቀሩ ያሉ እምራቾች መንግሥታዊ ድጋፍና ማበረታቻ በከፍተኛ ደረጃ ያስፈልጋቸዋል የሚሉት አቶ ተሾመ፤ በተለይ ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎች እጅግ አስፈላጊ እንደመሆናቸው በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱና ምርቶቹም አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባው ያመለክታሉ።
በተለይ ደግሞ እርሳቸው የገጠማቸው አንዱና ዋነኛ ችግር እነዚህን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ለማቅረብ በሚደረገው የጨረታ ሂደት ቅድሚያ የሚሰጠው መሳሪዎቹን ከውጪ ሀገር ለሚያስመጡ እንጂ በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾችን በጨረታ የተወዳዳሪነትን እድል የሚዘጋና ተስፋ የሚያስቆርጥ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ከዚህ አንፃር መንግሥት ቢቻል ለሀገር ውስጥ አምራቾች ቅድሚያ ቢሰጥ፤ ካልሆነ ደግሞ ለሀገር ውስጥ አምራቾችም ሆነ ከውጭ ሀገራት መሳሪያዎቹን ለሚያስመጡ እኩል እድል መስጠት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ከአስመጪዎች እኩል ጨረታ ተወዳድረው ምርቶቻውን የማቅረብ እድል እንዲፈጥርላቸው የሚያስችል እንደሆነም ይጠቁማሉ።
ኩባንያው ፈጣን የበሽታ መመርመሪያ መሳሪያዎችን ያለውጪ ሀገር ዜጎች ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያውያን ብቻ እያመረተ እንደሚገኝና ለሀገሪቱ የሚያስገኘው ጥቅም እንደመሆኑ እንደ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ታይቶ ሁሉም ተሳትፎበት ትልቅ ስራ ሊሰራበት የሚችል መሆኑንም ነው አቶ ተሾመ የሚናገሩት።
ሌላኛው ሀገር በቀልና በውጭ ምንዛሬ ወደሀገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለመተካት በአነስተኛ ደረጃ እየሰራ የሚገኘው ‹‹ሃንስ ዊዝ ኬር›› የተሰኘው የሚታጠቡ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች አምራች ድርጅት ነው። ድርጅቱ ወደ ስራ የገባው እ.ኤ.አ በ2021 ሲሆን በኢትዮጵያ የሚታየውን የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ምርት ተደራሽነት ችግር በማየት ነው።
በአሁኑ ጊዜም ድርጅቱ ስድስት አይነት ምርቶችን ያመርታል። እነዚህም የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ /ሞዴስ/፣ የአዋቂና ቀድመው የሚወለዱ ህፃናት ዳይፐር፣ የአረጋውያን ዳይፐር፣ በተለያየ መጠን የአዋቂ ፓንቶች፣ አልጋን ከሽንት መከላከያ ልብሶች /የህፃናትና የአዋቂ/ እና የፌስቱላ ፓንቶች ናቸው።
አሁን ባለው አቅም ድርጅቱ 350 የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ /ሞዴሶችን/ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በአንድ ፓድ ውስጥ ያለው አራት ፍሬ ሞዴስ /አንድ የማታ ሶስት የቀን/ ጥቅም ላይ ውሎ ዳግም እየታጠበ ለአንድ አመት ከስድስት ወር ያገለግላል። ምርቶቹን ለማምረት የጥጥ ጨርቆች በግብአትነት ይውላሉ። በዚህም ምክንያት ምርቶቹ ጥቅም ላይ ሲውሉ ምንም አይነት ኬሚካል በውስጣቸው ስለማይኖር በጤና ላይ የጎንዮሽ ጉዳት አያመጡም። ለዚህም ከሚመለከተው አካል የክሊኒካል ላብራቶሪ ፍተሻ ተደርጎለት የጥራት ማረጋገጫ አግኝቷል።
ወይዘሮ ሀናን አህመድ የድርጅቱ መስራችና ባለቤት ናቸው። የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቱን በዚህ መልኩ ማምረት የፈለጉበት ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በፋብሪካዎች ተመርተው የሚወጡ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋ በመናሩ ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ በመፈለጋቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እናቶች ያለፉበትን ይህን የተፈጥሮ ግዴታ ሂደት በጠበቀ መልኩ መታጠብ የሚችልና ድጋሚ ጥቅም የሚሰጥ፣ የአካባቢ ንፅህናን የሚጠብቅ፣ ኢንፌክሽንና የማህፀን ካንሰርን የሚከላከል ምርት በዘመናዊ መንገድ የማምረት ሃሳብ ስለነበራቸው ወደዚህ የማምረት ስራ እንደገቡም ይጠቁማሉ። ስራው ችግር ፈቺና ወጪ ቀናሽ በመሆኑም ጭምር የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያውን አምርተው በተለይ ደግሞ በገጠር አካባቢ ለሚገኙና የነዚህ ምርቶች እጥረት ላሉባቸው ሴቶች ተደራሽ መሆን ፍላጎት እንደነበራቸውም ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ሀናን ታጥበው ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ የጀመሩት በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉና በትምህርት ቤት ውስጥ ለሚማሩ ልጅ አገረድ ሴቶች በርዳታ መልክ በማቅረብ ነው። ወደ ገበያው ገብተው ለትምህርት ቤቶችና ለመንግሥት ተቋማት ምርቶቻቸውን በጨረታ ለማቅረብ በሚያደርጉት ጥረት ግን ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ግዢ ጨረታ ሲወጣ የጨረታው አሸናፊዎች በአብዛኛው አየር ባየር ነጋዴዎች ናቸው እንጂ እንደ እንደእርሳቸው አይነት አምራቾች እንዳልሆኑ ይገልፃሉ። የእርሳቸውን ምርቶች በአብዛኛው የሚገዙት ተጫራቾች መሆናቸውንና አትራፊዎቹም በአብዛኛው ተጫራቾቹ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ይህ አካሄድ ስላላዋጣታቸው መጀመሪያ በድጋፍ መልክ ምርታቸውን ለተቸገሩ ሴቶች በማቅረብና በማስተዋወቅ እግረመንገዳቸውን ህብረተሰቡን በማስገንዘብ ወደ ገበያው መግባት እንደፈለጉ ያስረዳሉ።
የወር አበባ ንፅህና ምርቶች ተደራሽነት በኢትዮጵያ ገና ብዙ እንደሚቀረው የሚናገሩት ወይዘሮ ሀናን እንደውም በኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች ለወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ተደራሽ እንዳልሆኑ መረጃው እንዳላቸው ይጠቅሳሉ። በተለይ በገጠር አካባቢ የሚታየው ችግር የጎላ መሆኑን እንደተመለከቱና ከዚህ አንፃር መንግሥት እንደርሳቸው አይነት አምራቾችን ማበረታትና መደገፍ እንዳለበት ይጠቁማሉ። ለአብነትም በጨረታ ከአስመጪዎች ጋር የሀገር ውስጥ አምራቾች እኩል እንዲወዳደሩ ማድረግ፣ የመስሪያ ሼዶችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎን የሚታጠቡና ዳግም ጥቅም የሚሰጡ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን በተለይ በገጠር አካባቢ ያሉ ሴቶች እዲጠቀሙ ለህብረተሰቡ ስለምርቱ ጠቀሜታ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መሰረት ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ‹‹የአምራችነት›› ቀን በሚል በመንግሥት ተሰይሟል። ይህ ቀን አምራቾች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ለሀገር እያደረጉ ያሉት አስተዋፅኦ የሚዘከርበት ነው። በህክምናው ዘርፍ ያሉ ሀገር በቀል አምራቾችም ለሀገራቸው የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነውና ከዝክሩ ባለፈ ያሉባቸው ችግሮች በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እንደሚፈቱላቸው ይታመናል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም