ስፖርትን በተለይም እግር ኳስን በዘመናችን ከውድድርነት ባለፈ አርቆ አለመመልከት አላዋቂነት ነው። ይህ የዓለማችን ቁጥር አንድ ተወዳጅ ስፖርት እግር ኳስ ተሰባስቦ ቂሪላ ከማልፋት በእጅጉ የተሻገረ ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው እየጎላ ስለመምጣቱ ብዙ ምሳሌዎችን ማስቀመጥ ይቻላል። ዘወትር የትችት ናዳ በሚወርድበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንኳን ስፖርቱ ከሚፈስበት ረብጣ ገንዘብ አንፃር ውጤቱ ሀገርን ባይመጥንም ፋይዳው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕዝብ የሚመጥነውን ውጤት ባለማግኘቱ ምክንያት የስፖርቱ ማኅበራዊ ፋይዳ ብዙ ጊዜ ጎልቶ ሲነገር አይታይም። የዛሬው ዕለት የበጎነት ቀን ነውና የኢትዮጵያ እግር ኳስ የበጎነት ተምሳሌቶችን ማመስገን ለሌሎችም አርአያ ይሆናል። ይህም በስፖርቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚገኙ ለሌሎች ለበጎ አድራጎት እንዲነሳሱ ከማድረግ ባሻገር በጎነቱ እያላቸው ወደ ተግባር መግባት ላልቻሉትም እንዲያስቡበት ያደርጋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስና በጎ ተግባራት እንቅስቃሴዎች ጉዳይ ሲነሳ የስፖርት ቤተሰቡ በተመሳሳይ ድምፅ የሚመሰክረው አንድ ነገር አለ። ይህም የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች ናቸው። የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በተናጠል በመሠረቱት ማኅበርም ይሁን ከማኅበራቸው እንቅስቃሴ ውጪ በጎ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ብዙ ነገር ሠርተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንደ ክለብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዋልታና ማገር ሆነው ማገልገላቸውና እያገለገሉ እንደሚገኙም ይታወቃል። ሁለቱ ክለቦች እንደ ተቋም የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለማኅበረሰቡ ያበረክታሉ። ከዚያ በዘለለ ግን የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በማኅበራቸው በኩል የሚያደርጉት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በገንዘብ የማይተመን ለሌሎችም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። የደጋፊ ማኅበራቱ በሥራቸው በሚገኙ በርካታ ውብ ደጋፊዎች አማካኝነት ባለፉት በርካታ ዓመታት የሥራቸውን ያህል አልተነገረላቸውም እንጂ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ያላደረጉት ነገር የለም።
የአንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በታላቁ የክለባቸው አርማና የኢትዮጵያ ስፖርት አባት ‹‹ዝክረ ይድነቃቸው ተሰማ›› በሚል በየዓመቱ የደም ልገሳ መርሃግብር ያደርጋሉ። በየዓመቱ በተለያዩ ዙሮች የደም ልገሳ መርሀ ግብራቸው ደም በማሰባሰብ ግንባር ቀደም የሆኑበት ታሪክ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚረሳ አይደለም። ይህ የበጎ ፍቃድ ተግባራቸው በየዓመቱም ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በዚህ ረገድ የተለየ ታሪክ የላቸውም። ቡናማዎቹ በተለይም በየአመቱ በሚያካሂዱት የጎዳና ላይ የቤተሰብ የሩጫ ውድድር ላይ የደም ልገሳ መርሃግብርን ጨምሮ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለማበርከት ሁሌም ከፊት ተሰላፊ ናቸው።
የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ የዓለም ስጋት በነበረበት በዚያ በጨለማ ዘመን በተለያዩ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ከማኅበረሰቡ ዘንድ የቆሙበት አጋጣሚ ታሪክ የሚዘነጋው አይደለም። በርካታ ገንዘብ በማዋጣት የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ገዝተው ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በየጎዳናው እጅ እያስታጠቡ ማኅበረሰቡ ከወረርሽኙ ራሱን እንዲከላከል ተግተው ሠርተዋል። ግንዛቤ ከማስጨበጥ ሥራዎች ጎን ለጎን ገንዘብ እያሰባሰቡ በወረርሽኙ ሳቢያ ድሃው ማኅበረሰብ ለችግር እንዳይጋለጥ ጥረዋል። በዚህም የብዙዎችን ቀዳዳ ደፍነዋል፣ ለበርካቶችም የዕለት ጉርስ ሆነዋል።
ሁለቱ የኢትዮጵያ ኃያላን ክለቦች በሜዳ ላይ ተቀናቃኝ ሆነው ቢታዩም ውብ ደጋፊዎቻቸው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ብዙ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ አለ። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በተጨማሪ የአረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን የረድኤት ተቋማትን በተለያየ ጊዜ መደገፍ መለያቸው ነው። አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት መሣሪያ ቁሳቁስ በማሰባሰብ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በችግኝ ተከላና ሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለሀገር አበርክተዋል። መቀመጫቸው ከሆነችው አዲስ አበባ ውጪም በተለያዩ ከተሞችና ገጠር ጭምር ዘልቀው የእንቦጭ አረምን ነቅለዋል፣ አንበጣን ለመከላከል ከገበሬው ጋር ሰብል ሰብስበዋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሁለቱ ታላላቅ ክለቦች ባሻገር በርካታ የከተማ ክለቦች በተለያየ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ተሳታፊ ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ክለቦች ጠንካራ የደጋፊ ማኅበር በማቋቋም ረገድ ካለባቸው ክፍተት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል ደጋፊዎቻቸው እምብዛም የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ሲያከናውኑ አይስተዋልም። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የበርካታ ክለቦች ደጋፊዎች እንደ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁሉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ብዙ ነገሮችን የመለወጥ አቅም አላቸው። በየአካባቢያቸው በተለያየ መልኩ የተቸገሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሕይወት መቀየር ይችላሉ። ጥቂት ቢሆኑም በርካታ ደጋፊዎች ያሏቸው አንዳንድ ክለቦች ወጥ ሆኖ ባይዘልቅም ጥሩ ጅምር አላቸው። የሚያስተባብር ጠንካራ የደጋፊ ማኅበር የመፍጠር አቅም ላይ ሲደርሱም ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጡና የእግር ኳስን ትርጉም ከፍ እንደሚያደርጉም ይታመናል። ለዚህ ግን ከሁለቱ የበጎ አድራጎት ተምሳሌቶች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ብዙ መማር ይጠበቅባቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም