የመስከረም ወር መጣሁ፤ መጣሁ እያለ ነው። ጭል፤ ጭል የምትለው ዝናብ የክረምቱን መገባደድ ታበስራለች። አጭሯ የጳጉሜን ወርም አሮጌውን ዓመት ሸኝታ አዲሱን ለመቀበል ሽር ጉድ እያለች ነው። ተሰማ መንግስቴ፤ ዘውዴ መታፈርያ እና ገብረየስ ገብረ ማርያም ማምሻ ግሮሰሪ ውስጥ የደራ ጨዋታ ይዘዋል።
የጨዋታቸው ርዕስ ስለመስዋዕትነት ነው። መስዋዕትነትን ሶስቱም ከመገናኛ ብዙሀን በሰሙት እና በራሳቸው መንገድ እየተነተኑ አንዳንድ ጊዜ በመስማማት ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ አንዱን ለማሳመን በመሞከር ጨዋታውን አግለውታል። አንዱ ያነሳውን ሃሳብ ሌላው እየጣለና ለራሱ የሚሆን ማስረጃ እያቀረበ ሃሳቡን ለማስረጽ የሚያደርገውም ጥረት አካባቢያቸው ያለውንም ሰው ቀልብ ስቧል።
ዘውዴ መታፈርያ ውይይቱን በአንክሮ ካዳመጠ በኋላ ተራውን ወሰደ። ብዙ ጊዜ የመከራከርያ ነጥብ አድርጎ የሚያቀርበውን ሃሳብ ዛሬም ለተነሳው ሃሳብ ማጠናከርያ አድርጎ አመጣው።‹‹ እኔ ወደዳችሁም፤ ጠላችሁም ስለመስዋዕትነት ካነሳን የአያት ቅድመ አያቶቻችን ያህል መስዋዕትነት የከፈለ አለ ብዩ አላምንም። ጎጆዋቸውን ዘግተው፤ ሚስትና ልጆቻቸውን ትተው ቅድሚያ ለሀገሬ ብለው በዱር በገደሉ ተዋድቀዋል።
በደም በአጥንታቸው ባንዲራዋን ከፍ አድርገዋል። በየዘመኑ የመጣን ወራሪ ኃይል አሳፍረው በመመለስ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ከፍ ያለ ዝና እንዲኖራት አድርገዋል። እነሱ ወድቀው ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋል። የኢትዮጵያ ከፍ ማለትም ሌሎች ለነጻነታቸው እንዲነሳሱና ቅኝ ገዢዎችን ከሀገራቸው እንዲያባርሩ አርማ ሆኖ አገልግሏል።
በዶጋሊ፤ በአድዋ፤ በማይጨው፤ በካራማራ እና በመሳሰሉት አያቶቻችን ታሪክ ሰርተዋል። ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ታሪክ ጽፈዋል። ዛሬ እኔና እናንተም በዚች የነጻነት ምድር ላይ እንድንኖር መሰረት የሆኑም እነሱ ናቸው። ስለዚህም ከነዚህ ጀግኖች በላይ ማን ስለመስዋዕትነት ምሳሌ ሊሆን ይችላል ›› ብሎ በአሸናፊነት መንፈስ ወደ ጓደኞቹ ተመለከተ።
ዘውዴ ንግግሩን መጨረሱን ያረጋገጠው ተሰማ መንግስቴ ከፊቱ የቀረበለትን ቢራ አንድ ጊዜ ከተጎነጨ በኋላ ጉሮሮውን ጠራርጎ ያሳምንልኛል ብሎ ያሰበውን ሃሳብ ሰነዘረ። ‹‹እርግጥ ነው አያት ቅድመ አያቶቻችንን ይህችን ሀገር በማጽናት መስዋዕትነት ከፍለዋል። ለእኛም ነጻ ሀገር አስረክበውናል። ሆኖም ትላንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለሀገራችው ነጻነት በዱር በገደሉ ህይወታቸውን የሚገብሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ።
ስለመስዋዕትነት ካነሳን ደግሞ በቅደሚያ ማንሳትና ማመስገን ያለብን መከላከያ ሰራዊታችንን ነው። መከላከያ ሰራዊታችን ደሙን አፍስሶ፤ አጥንቱን ከስክሶ የዚህችን አገር ህልውና አስቀጥሎልናል።
መከላከያችን በደምና በአጥንቱ ሉአላዊነትታችን አስከብሯል፤ ነጻነታችንንም አረጋግጧል። አልፎ ተርፎም በኮርያ፤ በኮንጎ፤ በላይቤሪያ፤ በሶማሊያ፤ በሩዋንዳና ብሩንዲ እንዲሁም በሱዳን በመዝመት በግጭትና በጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራትን አረጋግቷል፤ ወደ ሰላማቸውም መልሷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማማበት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሰራዊት ነው። ሰራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለዓላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጨለማን ማሻገር የሚችል ልበ ሙሉ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ በጦርነት ወቅት ጀግና ሆኖ በስኬት በመራመድ ላይ ይገኛል። ስለዚህም ለእኔ መስዋዕትነትን ሳስብ ቀድሞ በህሊናዬ የሚመጣው መከላከያ ሰራዊታችን ነው።›› ብሎ ሃሳቡን ቋጨ።
ገብረየስ በተመስጥኦ ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ‹‹ ጓደኞቼ ሁለታችሁም የተናገራችሁት ሃሳብ መሬት ጠብ የሚል አይደለም። እውነት ነው ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ እና ከአብዛኞቹ የዓለም ሀገራትም ረጅም የስርዓተ መንግስት ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ይህቺ ጥንታዊት ሀገር በየዘመናቱ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በማለፍ ያላትን ክብርና ሞገስ ጠብቃ ዛሬ ላይ ደርሳለች። አድዋንና ካራማራን በመሳሰሉ የጦር አውድማዎች የሀገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿም ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ከነክብሯ ለዛሬው ትውልድ አስረክበዋል።
መከላከያ ሰራዊታችንም ቢሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የጀግንነት መገለጫ ጥግ ነው። ሰራዊቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ እራሱን ለህዝብና ለሀገር አሳልፎ ይሰጣል፤ የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነትን ይከፍላል። በዱር በገደሉ ይዋደቃል። ደሙን ያፈሳል፤ አጥንቱን ይከሰክሳል። ዛሬ እንኳን እኔና እናንተ በሰላም ቁጭ ብለን ለመጫወት የበቃነው የመከላከያ ሰራዊታችን በየዱር ገደሉ በሚከፍለው መስዋዕትነት ምክንያት ነው።
ሆኖም ስለመስዋዕትነት እያወራን የዛሬውን ትውልድ ልንረሳው አይገባም። አንዳንድ መዛነፎች ቢኖሩም የዛሬው ትውልድ ለሀገሩ ምንም እንዳላበረከተ ሲቆጠር ያመኛል። እንደው የትላንቱን ማመስገን እና የዛሬውን ማጣጣል ስለምንወድ እንጂ ልብ ብለን ካስተዋልነው የዛሬውም ትውልድ ለሀገሩ የሚከሰተው ነገር ያለ አይመስለኝም።
በእርግጥ በመጤ ባህል እና በመሰል ዘመናዊ ልማዶች ወጣቱ ትውልድ ላይ አንዳንድ መዛነፎች ይኖራሉ። አልፎ ተርፎም አንዳንድ ወጣቶች ከሀገራቸው ባህልና ወግ ይልቅ የውጭውን ሲናፍቁ ሊታዩ ይችላሉ። ታላቅን ማክበር፤ ለታናሽ ማዘን፤ መታዘዝና እንግዳን መቀበል የመሳሰሉት እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መሄዳቸው እንደ እናንተ ሁሉ እኔንም ያሳስበኛል። ሆኖም እነዚህን ጉድለቶች በማጉላት ብቻ የዚህን ዘመን ትውልድ በጎ ስራዎች ጥላሸት እንዳንቀባው እሰጋለሁ።
የዛሬው ትውልድ የአያትና ቅድመ አያቶቹን አደራ በመረከብም በጦር ሜዳ ውሎውም ሆነ በልማት ዘርፉ አሻራውን በማሳረፍ ላይ ይገኛል። ለሀገሩ ሉአላዊነት መታፈርና ለዳርድንበሩ መከበር በተጠራበት መስክ ሁሉ በመዋደቅ የቀደምት አያቶቹን ታሪክ ጽፏል። ከዛም አለፍ ብሎም ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ እንዳልሆነ በመረዳትም የአባይ ግድብ የመሳሰሉ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶቹን በገንዘቡና በዕውቀቱ በማገዝ ኢትዮጵያ ከብልጽግና ማማ ላይ ለማቆም በመጣር ላይ ይገኛል።
በዚህ ትውልድ ጠንሳሽነት ግንባታው በመገባደድ ላይ የደረሰው የአባይ ግድብ በርካታ ፈተናዎችና አሜኬላዎች ቢገጥሙትም በዚህ ትውልድ አይበገሬነት ዛሬ ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን መሆን ችሏል። የኢትዮጵያን መበልጸግ የማይፈልጉ ሀገራት ግድቡን ለማሰናከልና የትውልዱንም ተስፋ አብሮ ለማጨለም ያልፈነቀሉት ድንጋይ ባይኖርም በዚህ ትውልድ በሳል አመራርና በህዝብ ጽናት የአባይ ግድብ ከዳር ደርሷል። ኢትዮጵያውያንም የአባይን ግድብ ከዳር በማድረስ እንደ አድዋ ሁሉ ዛሬም ለአፍሪካ ሀገራት ብርሃን ሆነዋል።
ኢትዮጵያውያን ከ31 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከልም ታሪክ ጽፈዋል። ሀምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ቀን 569 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል አዲስ ታሪክ ጽፏል። አስታውሱ በዚህ ዕለት የተሳተፈው የሕዝብ ብዛት ከ34 ሚሊዮን በላይ ነው። ይህ እንግዲህ የበርካታ አፍሪካ ሀገራትን ሕዝብ ያክላል። ይህ ሕዝብ ጊዜውን፤ ጉልበቱን፤ ገንዘቡን ሳይሰስት ቀኑን ሙሉ ሀገሪቱን አረንጓዴ ዐሻራ ሲያለበስ ውሏል።
በዓለም ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውንና በቀጣይም የዓለም ሀገራት ስጋት ይሆናል ተብሎ የሚሠጋውን የበረሃማነት መስፋፋት ከወዲሁ ለመመከት ይህ ትውልድ እጁን ከአፈር ጋር በማወዳጀት ምቹ ዓለምን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል። ይህንኑ ተመክሮም በርካታ እንደ ኬኒያ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በመውሰድም አፍሪካን የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያንም ጥረትም በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት 36 ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ አድናቆትን በማግኘት አንዱ የዚህ ትውልድ ደማቅ ዐሻራ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በአድዋ ወራሪዎችን በማሳፈር የድል እና የነጻነት ተምሳሌት ነች። ሆኖም በጦር ሜዳ የተገኘውን ድል በልማቱም መስክ በመድገም ከስንዴ ለማኝነት ለማውጣት የሚደረገው ጥረት ግቡን ሳይመታ ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን ግን ታሪክ መቀየር ጀምሯል። ይህ ትውልድ ከእርዳታ ጠባቂነት የሚያላቅቀውን ስንዴን አምርቶ ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ በቅቷል። በዚህ ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው።
ሆኖም የኢትዮጵያ ችግር በአንድና በሁለት ዓመታት የስንዴ ምርት የማይፈታና ተከታታይ በሆነ መልኩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚጠይቅ ነው። ስለዚህም ባለፉት አራት ዓመታት የተደረጉ ለውጦች ኢትዮጵያን ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት ለማሸጋገር አብቅቷታል። ስለዚህም ትጋትና ትዕግስት ከታከለበት ለዘመናት የተከማቹ ችግሮች በሂደት እየተራገፉ እንደሚመጡ አመላከች ነው።
በተለይም የዛሬው ትውልድ ችግሮችን በመነጋገርና በውይይት መፍታት ከቻለ አሉ የሚባሉትን ችግሮች ሁሉ ወደ ምቹ አጋጣሚ መቀየር ይቻላል። ለዚህ አብነት የሚሆነው ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ መንግስትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የቆየውን ጦርነት የውጭ ኃይል ሳይገባበት በምክክርና በውይይት መፍታት መቻሉ ኢትዮጵያን በአዲስ አስተሳሰብ ጎዳና እንድትራመድ አድርጓታል። ኢትዮጵያም የሚገጥሟትን ችግሮች ሁሉ በራሷ አቅም የመፍታት አቅም እንዳላትም አሳይቷል።
ስለዚህም አሁን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ግጭቶችን ማስወገድ ከተቻለና ችግሮችን በውይይትና ምክክር የመፍታት ባህል ከዳበረ እመኑን መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ነው።
ግን እዚህ ላይ ለመድረስ በቅድሚያ ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት ማዳበር ይጠበቅብናል። ወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም።
አሁን ያሉት አለመግባባቶች ተወግደው በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው። ሀገራዊ ምክክሩ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና የመወያየትና የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ይረዳል። በመወቃቀስ ላይ የሚያተኩረውንም የፖለቲካ ባህላችንንም ወደ መነጋገር፤ መተባበርና መደጋገፍ እንዲመጣ ያደርጋል።
እመኑኝ አሁን ያሉት ችግሮች ነገ ከነገ ወዲያ አይኖሩም። ይህ ትውልድ ከጦርነትና ከግጭት ምንም እንደማያገኝ እየተረዳ መጥቷል። ከጦርነት ሞት፤ የአካል መጉደል፤ መፈናቀልና ስደት እንጂ እድገትና ብልጽግና እንደማይገኝ ገብቶታል። በእርግጥ ከጦርነትና ግጭት የሚያተርፉ አካላት ኢትዮጵያ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ ይፈልጉ ይሆናል።
እመኑኝ ይህ ትውልድ ምኞታቸውን ይቀጨዋል። በቃችሁ ይላቸዋል። ይህ ትውልድ በእነዚህ የግጭት ነጋዴዎች የሚሞትበት፤ የሚቆስልበት፤ የሚፈናቀልባትና የሚሰደድበት የታሪክ አጋጣሚዎች የሚዘጉበትና በምትኩ ሰላም፤ እድገትና ብልጽግና የሚረጋገጥበት ጊዜ ቅርብ ነው።
ለዚህ ደግሞ ይህ ትውልድ መስዋዕትነት ይከፍላል። ለጦርነት ሳይሆን ለሰላም መስዋዕትነት ይከፍላል። ሰላምን ያጸናል፤ ዕድገትን ያስቀጥላል፤ ብልጽግናን ያጸናል።›› ብሎ ፊቱን ወደ ጓደኞቹ መለሰ።
ዘውዴ መታፈርያና ተሰማ መንግስቴም መስማማታቸውን ለመግለጽ ጽዋቸውን አነሱ።
ማምሻ ግሮሰሪም የአዲሱን ዓመት መዳረስ በሚያመላክቱ ጥኡመ ዜማዎች ደምቃለች። በብዙዎቹ ፊት ላይም ተስፋና ደስታ ይነበባል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም