የዘመናዊው ኦሊምፒክ መስራች ፒር ደ ኩበርቲን ስፖርትን የሚገልጹት ‹‹… ለእኔ የሃይማኖቴን ያህል ስሜት ይሰጠኛል›› ሲሉ ነው፡፡ በእርግጥም የስፖርት ፍቅር በቀላሉ ከውስጥ የማይወጣ በደም ስር ሲዘዋወር የሚኖር ነው፡፡ በርካቶች ከልጅነታቸው የተጠናወታቸው የስፖርት ፍቅር ተወዳዳሪነታቸውን አቁመው እንኳን ሊርቁት አይቻላቸውም፡፡ ይልቁንም እንደማግኔት እየሳበ እንዲያገለግሉት ያደርጋል፤ ምክንያቱም የሚገኘው የመንፈስ እርካታ በዚያው ልክ በመሆኑ ነው፡፡
ከተወዳዳሪነት ዓለም የራቁ ስፖርተኞች በአሰልጣኝነት፣ በቴክኒክ አማካሪነት፣ በተንታኝነት፣ በቡድን መሪነት፣ በስራ አስፈጻሚነት፣… መሰማራታቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ ስፖርትን ከሌሎች ዘርፎች ልዩ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሊተውት የማይቻል ሱስ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ስፖርተኞች ተወዳዳሪነትን ካቆሙ በኋላ በተለያዩ ስፖርታዊ ጉዳዮች ከማገልገል ወደኋላ አይሉም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አትሌቲክስ ሲሆን፤ እጅግ በርካታ አንጋፋና ሩጫን ያቆሙ አትሌቶች የወከሉትን ሃገር ዳግም በአማተርነት እያገለገሉት ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት እየመራች የምትገኘው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ደግሞ የአገልጋይነት ተምሳሌት ናት፡፡ ከባርሴሎና እስከ አቴንስ በድል ህዝቧን ያስፈነደቀችና ለሠንደቅዓላማዋም ያነባችው እንቁ አትሌት ከሩጫ ሕይወቷ ከተለየች በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን መቀላቀሏ የሚታወስ ነው፡፡ እስካሁንም በመምራትና ዝናን ያተረፈችበትን ስፖርት እንዲሁም በስፖርቱ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሁሉ በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ‹‹ቀድሞ በሩጫው ሃገሬን ሳገለግል ቆይቼ ራሴን ልለውጥ ችያለሁ፤ ከውድድር ከተሰናበትኩ በኋላ ደግሞ ባለኝ ልምድና አቅም ስፖርቱን ለማገልገል በመብቃቴ ደስተኛ ነኝ›› ትላለች፡፡
ወደ ፌዴሬሽኑ በአመራርነት የተመለሰችበትን ሁኔታም ስታስታውስ ‹‹እንደሚታወቀው በሩጫ ሕይወት አትሌቶች በጉዳት፣ ስፖርት በቃኝ በማለት፣ በወሊድ፣ ከሃገር በመውጣት፣… ከስፖርቱ ይርቃሉ፡፡ እኔም ከውድድር ዓለም ስወጣ ከስፖርቱም ርቄ ነበር የቆየሁት፤ ይሁንና ጓደኞቼ እነ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ስለሺ ስህን፣ ማርቆስ ገነቴ፣… አትሌቲክሱን ለመምራት መምጣታቸውን ተከትሎ ዘግየት ብዬ ተቀላቅያቸዋለሁ፡፡ ጥሪ ያደረገልኝ ደግሞ ቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የነበረው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው›› በማለት ተናግራለች፡፡
በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖች ቀዳሚው የዓለም አትሌቲክስ ሲሆን በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሆኑን የጠቀሰችው ደራርቱ፣ በበርካታ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ተሳታፊና ውጤታማ የሆነውን ፌዴሬሽን ማገልገል ትልቅ ክብር እንደሆነም ታብራራለች፡፡ ፌዴሬሽኑን በአመራርነት ተቀላቅላ በዓመታት ያካበተችውን ልምድ ሃገርን ወደ መጥቀም እንድትለውጥ ያደረጓትን አትሌቶችንና ከሯጭነት ዘመኗ እስከ አሁን ድረስ እያከበረ ለዚህ ያደረሳትን ህዝብም አመስግናለች፡፡
በአንጻሩ እንደ እሷ በሙያቸው በዙ ማበርከት እየቻሉ ከፌዴሬሽኑ የራቁ አትሌቶችን ወደ ፌዴሬሽኑ ተመልሰው የአቅማቸውን እንዲያበረክቱና ለተተኪዎችም ሞራል እንዲሆኑ ጥሪዋን አቅርባለች። ደራርቱ አብዛኛዎቹ አትሌቶች ከስፖርቱ ሲሰናበቱ ሙሉ ለሙሉ ከፌዴሬሽኑ የሚርቁበትን ምክንያት ‹‹ምናልባትም የስራ ድርሻ አይኖረን ይሆናል›› በሚል እንደሚሆንም ጠቁማለች፡፡ ነገር ግን በስፖርት ሕይወት የቀድሞ አንጋፋ አትሌቶች አሁን ካሉት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት በርካታ ምክር በማግኘት ትልቅ ደረጃ ይደርሳሉና እገዛቸውን ቢያደርጉ ትመክራለች፡፡
ምንም እንኳን በስፖርቱ በአሰልጣኝነት አሊያም በሌሎች ኃላፊነቶች ላይ ገብተው ባይሳተፉም በውድድር ላይ ካሉ አትሌቶች ጎን በመቆምና ሞራል በመስጠት ማገልገል እንዳለባቸውም ጠቁማለች፡፡ ስፖርቱ ያሳወቃቸው ስኬትንም የተቀዳጁበት ነውና በየትኛውም የአትሌቲክስ ዘርፍ ሃገራቸውን በድጋሚ ሊያገለግሉ እንደሚገባም አሳስባለች፡፡
ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ከአትሌትነት እስከ ብሄራዊ ፌዴሬሽን አመራርነት እንዲሁም የአህጉር አቀፉ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የቦርድ አባል ከመሆኗ ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የአትሌቲክስ ማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገለችም ትገኛለች፡፡ በዚህ ከሃገር እስከ አህጉር በተሻገረ አስተዋጽኦም ለበርካቶች ተምሳሌት ሆናለች፡፡ በዚህም የዓለም አትሌቲክስ ለረጅም ጊዜ ስፖርቱን በማገልገል ከሳምንት በፊት በቡዳፔስት ዓመታዊው ታላቅ የሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የዕድሜ ልክ ሽልማት እንዳበረከተላት ይታወሳል፡፡ ይህ ሽልማት በስፖርቱ የተለየ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የስፖርቱ ሰዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ የዘንድሮውን ጨምሮ ሶስት ጊዜ በመሸለም በኢትዮጵያ ክብሩን ካገኙ ጥቂት ግለሰቦች መካከል አንዷ ከሴቶች ደግሞ ብቸኛዋ ናት፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም