-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
ኢትዮጵያ መልካም ገጽታን በገነባችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ስሟን ለማስጠራት የማይሰንፉ አትሌቶችን በየዘመኑ ታፈራለች። ከሄልሲንኪ እስከ ቡዳፔስት በተካሄዱ የዓለም ቻምፒዮና መድረኮች የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውለበለቡና ሜዳሊያዎችን ያስመዘገቡ በርካታ እንቁ አትሌቶች ታይተዋል። ለብዙ አገሮች ተሳትፎ ትልቅ ነገር ሜዳሊያ ደግሞ ብርቅ በሆነበት ቻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እየተፈራረቁ ስኬትን አጣጥመዋል።
ከሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የቡዳፔስት ቻምፒዮና በ9 ሜዳሊያዎች ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የተመለሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የተለያዩ ሽልማቶች እየተሰጠው ነው። ለቡድኑ ከተበረከቱ የተለያዩ የዕውቅናና ሽልማት መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ በብሄራዊ ቤተመንግስት ከትናንት በስቲያ ምሽት የተደረገ ሲሆን፤ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህም መሰረት የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች 1ነጥብ 5ሚሊየን ብር፣ የብር ሜዳሊያ ያገኙት 1ሚሊየን በር እንዲሁም የነሃስ ሜዳሊያ ያጠለቁት 700ሺ ብር ተሸልመዋል።
ሜዳሊያ እንዲመጣ ምክንያት የሆኑ አሰልጣኞች፣ የዲፕሎማ ባለቤቶች፣ ተሳትፎ ያደረጉ እንዲሁም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከቡድኑ ጋር ወደ ሃንጋሪ የተጓዙ ባለሙያዎችም እንደ አስተዋጽዋቸው መጠን
ማበረታቻ ተበርክቶላቸዋል። በዕውቅና መድረኩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ሃገራቸውን ላስጠሩ አትሌቶች የምስጋና ንግግር አድርገዋል። ‹‹የዛሬ ዓመት ከኦሪጎን ቻምፒዮና መልስ ድል የተቀዳጁ አትሌቶችን እንዳከበርን ሁሉ በቡዳፔስት በተደረገው 19ኛው የዓለም ቻምፒዮና ላይ ተካፍላችሁ ሃገራችሁንና ህዝባችሁን አስከብራችሁ በድጋሚ ለመገናኘት ስለበቃን ፈጣሪ ይመስገን። ለዚህ ውጤት የበቃችሁ አትሌቶችና ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ›› ብለዋል።
በተገኘው ድል ተገቢውን ምስጋና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ፤ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድልን በማስለመዳቸው ሁሌም ውጤት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ‹‹አትሌቶቻችን የህዝብን ተስፋና ጉጉት ይዛችሁ ውድድር ላይ ትሳተፋላችሁ። በሃገራችን ብዙ ጊዜ ችግሮች ተፈራርቀውብናል ነገር ግን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ አትሌቶቻችን የሚያስገኙት ድል ተስፋ ሆኖናል። በችሎታችሁ ተወዳድራችሁ ሃገራችሁን፣ ህዝባችሁን እና ሰንደቅ አላማችሁን አስከብራችኋል። የአምናውና የዘንድሮ ውጤታችሁ ትርጉሙ በዚሁ የሚታይ ነው፤ ሀገራችንም በበጎ ገጽታ እንድትታይ አድርጋችኋል። ከእናንተ ብዙ ተምረናል፤ የቡድን ስራ፣ መፎካከር፣ መተጋገዝ፣ ሰብዓዊነት፣ … ጥቂቶቹ ናቸው›› ሲሉም ተናግረዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንት አሳስበዋል። የመጀመሪያው ነገር ከመካከለኛና የረጅም ርቀት ሩጫዎች ባለፈ በአትሌቲክስ ስፖርት የተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ተጨማሪ ውጤት እንዲመጣ የሚል ነው። ሌላው ደግሞ ከወራት በኋላ ለሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት ውጤት እንዲመዘገብ የአደራ መልዕክታቸውን ያስተላለፉበት ነው።
ቡዳፔስት ላይ አትሌቶች ሮጠው ካስመዘገቡት ሜዳሊያ ባለፈ በፌዴሬሽኑም በኩል ተጨማሪ ሽልማት ባለፈው ሳምንት መሰጠቱ ይታወቃል። ውድድሩ ከመካሄዱ አስቀድሞ በተካሄደው 54ኛው የዓለም አትሌቲክስ ጉባኤ ላይ የዓለም አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የአትሌቲክስ አገልግሎት ‹‹ፕላክ ኦፎ ሜሪት›› ሽልማት አበርክቶላት ነበር። በዚህ ሽልማት ላይም መላው የልኡኩ አባላት ፊርማቸውን ያኖሩበት ሲሆን፤ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ አንጋፋዋ አትሌት ደራርቱ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አበርክታለች።
የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ አበራም በተመሳሳይ ከዓለም አቀፉ አካል የተበረከተለትን ሽልማት በመድረኩ ላይ ተረክቧል። ከዓለም አትሌቲክስ እአአ በ2022 በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በአካል ጉባኤው ባይካሄድም የ‹‹ቬትራን ፒን አዋርድ›› ተሸላሚ ሆኖ ነበር፤ በመሆኑም ከክቡር አቶ ቀጄላ መርዳሳ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ እጅ በክብር ተቀብሏል። ሽልማቱ የሚሰጠው ግለሰቦች ለአትሌቲክስ ስፖርት ረዘም ላለ ጊዜ በተለየ መልኩ በታማኝነት የላቀ አገልግሎት እና አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መሆኑን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በታሪክ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የኦሊምፒክንና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ያሸነፈው አትሌት ገዛኸኝ አበራ በ2000 የሲድኒ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድርን በማሸነፍ በወንዶች ከ32 ዓመታት በኋላ ድሉን የመለሰ ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው። እአአ በ2001 የኤድመንተን ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የማራቶን ባለድል በመሆንም ሃገሩን ያስጠራ ድንቅ አትሌት ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም