በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪነት በሲዳማ ክልል ይርጋለም እና ሃዋሳ ከተሞች አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ከ16 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክቶች የእግር ኳስ ምዘና ውድድር ፍጻሜውን አግኝቷል። ለዋንጫ በተደረገው ፍልሚያም በወንዶች ወላይታ ሶዶ በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ የፓይለት ቡድኖች አሸንፈዋል።
ከነሃሴ 16/2015 ዓ.ም አንስቶ በሃዋሳ እና ይርጋለም ከተሞች በርካታ ጨዋታዎች ሲከወኑ የቆዩ ሲሆን፤ ነሃሴ 26/2015 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። በሁለቱም ጾታዎች ለዋንጫ እና ለደረጃ ያለፉ ቡድኖችም ተለይተዋል። በአሁኑ ወቅት በርካታ መሰል የታዳጊ እግር ኳስ ውድድሮች በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከናወኑ ሲሆን ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራቱ ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል። በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሚዘጋጁት የፓይለት ፕሮጀክቶች የምዘና ውድድሮች ከሌሎቹ ውድድሮች ይበልጥ ትኩረት ስለሚሰጣቸው ለታዳጊዎቹ የተሻለ የመታየት እድልን እንደሚፈጥሩም ታምኖባቸዋል።
በወንዶች ይርጋለም ስታዲየም 16 ፕሮጀክቶች በአራት ምድቦች ተከፍለው የምድብ ማጣርያቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ቡድኖቹ የምድብ ማጣርያ ፍልሚያቸውን ካደረጉ በኋላ ከየምድቡ ለጥሎ ማለፍ መድረስ የቻሉ ቡድኖች ውድድራቸውን አከናውነው የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ሊለዩ ችለዋል። ለዋንጫ በተደረገው ፍልሚያም ወላይታ ሶዶ ፓይለት ፕሮጀክት አርባምንጭ ከተማ ፓይለት ፕሮጀክትን ገጥሞ በመለያ ምት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል። በዚህም አርባ ምንጭ ከተማ በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማን በመለያ ምት 4-3 በማሸነፍ ለፍጻሜ ሊደርስ ችሏል። ወላይታ ሶዶ ፓይለት እንዲሁ አፋር ሰመራ ፓይለትን በመለያ ምቶች 3-1 አሸንፎ ለፍጻሜው ፍልሚያ በመድረስ ዋንጫውን የግሉ አድርጓል። ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ሻሸመኔ ከተማ ፓይለት ፕሮጀክት አፋር ክልል ፓይለትን ፕሮጀክትን 4-2 በመርታት 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
በተመሳሳይ የተደረገው የሴቶች ፓይለት ፕሮጀክቶች ምዘና ውድድር አስር ቡድኖችን ያካተተ ሲሆን፤ በሁለት ምድቦች ተከፍለው ውድድራቸውን በማድረግ ቡድኖቹ ለዋንጫና ለደረጃ በመፋለም ውድድራቸውን ቋጭተዋል። በሴቶች ለዋንጫ በተደረገው ፍልሚያ አዲስ አበባ ከተማ ፓይለት ሲዳማ ክልል ፓይለትን በመለያ ምቶች 5-4 አሸንፎ ዋንጫውን ከፍ አድርጓል። በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ ሲዳማ ክልል ፓይለት ጋምቤላ ከተማ ፓይለትን 3-2 አሽንፎ የዋንጫ ተፋላሚ መሆኑን ሲያረጋግጥ ተጋጣሚው አዲስ አበባ ፓይለት አዳማ ከተማ ፓይለትን በመለያ ምት 4-2 አሸንፎ ለፍጻሜ ደርሷል። ለደረጃ በተደረገው ጨዋታም አዳማ ከተማ ፓይለት የጋምቤላ ክልል ፓይለትን 3-2 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታ ከ1ኛ-3ኛ ይዘው ለጨርሱ ቡድኖች የወርቅ፣ የብርና ነሃስ ሜዳለያ የተበረከተላቸው ሲሆን ከ1ኛ-4ኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ ቡድኖችም የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎ ውድድሩ ፍጻሜውን አግኝቷል። በተጨማሪም በውድድሩ ጥሩ ሥነ ምግባር ያሳዩ ቡድኖች የጸባይ ዋንጫ ተበርክቷል፤ በወንዶች ወላይታ ሶዶ በሴቶች ደግሞ ሲዳማ ክልል ፓይለትም ዋንጫዎቹን መውሰድ ችለዋል።
በ2015 ዓ.ም የፓይለት ፕሮጀክት ውድድር ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የታዳጊ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉበት ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያካሄዳቸው ዓመታዊ የታዳጊዎች ውድድር ውስጥ አንዱ ነው። ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆው ውድድር ዓላማውም በእግር ኳሱ ብቃት ያላቸውን እና ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በዘላቂነት ማፍራትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ፌዴሬሽኑ እምቅ አቅም ያላቸውን ታዳጊዎች መረጃ በመያዝ ወደ ፊት በሚኖሩት የታዳጊ ልማት መርሃ ግብሮች ላይ እንዲካተቱም ጥረት እንደሚያደርግ ውድድሩ በተጀመረበት ወቅት መጠቆሙ ይታወሳል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2015