ልጆች ለአዲስ ዓመት ምን አቅዳችኋል?

ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ክረምቱ አልቆ ለበጋ ተራውን ሊለቅ ትንሽ ቀናት እንደቀሩት ታውቃላችሁ አይደል? ክረምቱን ቤተሰብ በማገዝ፣ በጨዋታ፣ በንባብ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ የክረምት ትምህርት በመማር፣ ዘመድ በመጠየቅ፣ የጓሮ አትክልቶችን በመንከባከብ፣ የእጅ ሥራዎችን በመሥራት፣ በበጎ ፈቃደኝነት በማገልገል እና መሰል ተግባራትን በመከወን እንዳሳለፋችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም።

‹‹መስከረም ሲጠባ፤ አደይ ሲፈነዳ

እንኳን ሰው ዘመዱን፤ ይጠይቃል ባዳ››

ብሎ አዲስ ዓመትን ለመቀበል የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ነው የቀረን። ታዲያ አዲስ ዓመት ሲመጣ ብዙ ሰዎች እቅድ ያወጣሉ። እቅድ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚተገብሩት በዝርዝር ጽፈው ያስቀምጣሉ። ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል›› እንደሚሉት አባቶቻችን እቅዳቸውን እንዳይዘነጉት ይጽፉታል። ልጆች እናንተስ? አዲስ ዓመትን ለመቀበል ምን ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው? እንዴትስ ለማሳለፍ ነው ያቀዳችሁት? ሴቶች ‹‹አበባ አየሽ ወይ?›› ብላችሁ ለመጨፈር፤ ወንዶች ደግሞ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ለማለት፣ የእንቁጣጣሽ ሥዕል በመሳል እንዲሁም በአቅራቢያችሁ ለማደል አልተዘጋጃችሁም? ‹‹ተዘጋጅተናል›› የሚል ምላሽ እንደምትሰጡኝ እተማመናለሁ።

ልጆች ዛሬ ስለ እቅድ እንድንነጋገር ወደድን። እቅድ ማውጣት የሚጠቅመው ለምን መሰላችሁ? የምታከናውኗቸው ነገሮች ቅደም ተከተል እንዲኖራቸው እና ትኩረታችሁም የምትሠሩት ሥራ ላይ ብቻ እንዲሆን ያግዛችኋል። በተጨማሪም ያቀዳችኋቸውን ነገሮች እንዴት መከወን እንደሚቻል እና መቼ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ የተጠና አካሄድ እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል። ልጆችዬ እናንተ ተማሪዎች ስለሆናችሁ በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት ልታመጡ የምትችሉበትን መንገድ ማወቅ ይኖርባችኋል አይደል? ስለዚህ እቅድ ማውጣት አለባችሁ። እንዴት እንደሚታቀድ ካላወቃችሁ ደግሞ የወላጆቻችሁን ወይም የመምህሮቻችሁን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልጋችኋል። እናም ልጆች ማቀድ በትምህርታችሁ ጎበዝ እንድትሆኑ ከማድረግ ባለፈ ለወደፊት ሕይወታችሁ እንዲሁም ምኞታችሁን ለማሳካት በሚገባ ያግዛችኋል።

ልጆች ከእናንተ ቤተሰብ፣ ሀገር ብዙ እንደሚጠብቅ ታውቃላችሁ አይደል? የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች መሆናችሁን አውቃችሁ መቼ መጫወት እንዳለባችሁ፤ መቼ ደግሞ ማጥናት እንዳለባችሁ በማቀድ በትምህርታችሁ ውጤታማ እንድትሆኑ ያስችላችኋል። እቅዳችሁ እንዲሳካ ደግሞ ሁልጊዜም እንደምንላችሁ ወላጆቻችሁ ጓደኞቻቹ አሊያም ለቅርብ ቤተሰባችሁ በማማከር እና በመንገር መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም እቅዳችሁን በዝርዝር በመጻፍ የዕለት፣ የሳምንት፣ የወር … እቅዳችሁን ከመጻፍ በዘለለ፤ ምን ያህሉን እንዳሳካችሁ? ለምን እንዳላሳካችሁ? ራሳችሁን በየጊዜው በመፈተሽ እና በማረም ውጤታማ መሆን ትችላላችሁ።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ለአዲስ ዓመት አሁንም ጥቂት ቀናቶች እንዳላችሁ በመረዳት፤ የደንብ ልብሶቻችሁን በማዘጋጀት፣ ቦርሳችሁ የሚታጠብም ከሆነ በማጠብ፣ አዲስ የሚገዛላችሁ ከሆነ በጥንቃቄ በመያዝ ለትምህርት የሚያግዟችሁን ቁሳቁሶች ማዘጋጀት ይጠበቅባችኋል።

በትምህርታችሁ ጎበዝ እንድትሆኑም ያለፈውን ዓመት ደብተራችሁን ፈተሽ ፈተሽ በማድረግ ራሳችሁን ማዘጋጀትም ከእናንተ ይጠበቃል። በአዲስ ዓመት የምትማሯቸውን የትምህርት ዓይነቶችም ከታላላቆቻችሁ በመጠየቅ፤ አጋጣሚው እና ሁኔታው ከተመቻቸላችሁ ደግሞ ትምህርታዊ የቴሌግራም ቻናሎችን በመከታተል መዘጋጀት ትችላላችሁ።

አስተውላችሁ ከሆነ ልጆች፤ በብዙ ነገር ጎበዝ የሆኑ ልጆች አሉ። ለምሳሌ በትምህርታቸው ጎበዝ ሆነው ሥዕል መሳል የሚችሉ፣ ጨዋታዎችን ከጓደኞቻቸው ጋር የሚጫወቱ፣ ቤተሰባቸውን የሚያግዙ፣ መጽሐፍትን የሚያነቡ ብዙዎች ናቸው። እንዴት ይህንን ማድረግ ቻሉ? ብላችሁ አልጠየቃችሁም? መልሱ ምን መሰላችሁ? እቅድ አውጥተው በመንቀሳቀሳቸው ነው።

ስለዚህም አሮጌውን 2015 ዓመት እንዴት እንዳሳለፋችሁ በማጤን፤ ምን ዓይነት ስህተቶችን እንደሠራችሁ እና እነዚያን ስህተቶች በአዲሱ ዓመት ላለመድገም ማቀድ ይኖርባችኋል። ሌላው ደግሞ በትምህርት ቤት፣ በሠፈራችሁ እንዲሁም ከቤተሰባችሁ ጋር የተጣላችሁ ትኖራላችሁ። ለመታረቅ አላሰባችሁም? በእርግጠኝነት መልሳችሁ ‹‹አስበናል›› የሚል እንደሆነ አልጠራጠርም። እናም ከሁሉም ሰው ጋር በፍቅር፣ በደስታ እንድትኖሩ እና አዲሱ ዓመት በይቅርታ፣ በፍቅር እና በደስታ እንድታከብሩ የበደላችሁን ‹‹ይቅር›› ማለት፤ እናንተን የበደላችኋቸውን ሰዎች ደግሞ ‹‹ይቅርታ አድርጉልኝ?›› በማለት እርቅ መፍጠር ይኖርባችኋል።

ሌላው ልጆች ከትምህርታችሁ ጎን ለጎን የሚያስደስታችሁን ነገር ለማድረግ አላሰባችሁም? ለምሳሌ የፈጠራ ሥራ የመሥራትም ይሁን ሌላም ፍላጎት ቢኖራችሁ ከትምህርታችሁ ጋር ሳይጋጭባችሁ በእቅዳችሁ መሠረት ማሳካት ትችላላችሁ። ክረምቱን በጨዋታ፣ ቴሌቪዥን በመመልከት በሚገባ ያሳለፋችሁ አላችሁ አይደል? እናም ልጆች ቴሌቪዥን ይሁን ለትምህርታችሁ የማይጠቅማችሁን ነገሮችን በመቀነስ፤ ትምህርታችሁ ላይ በሚገባ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስን በእቅዳችሁ ውስጥ ብታስገቡ መልካም አይመስላችሁም?

የእናንተ ወላጆች እንዲደሰቱባችሁ፤ ሀገራችንም በእናንተ የምትኮራባችሁ እንድትሆኑ ትምህርታችሁን በሚገባ በመከታተል፣ የቤት ሥራ በመሥራት፣ ያልገባችሁን በመጠየቅ እንዲሁም ከጓደኞቻችሁ ጋር በጋራ በማጥናት ጎበዝ ተማሪዎች ለመሆን እንዳቀዳችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ታዲያ እቅድ ስለታቀደ ብቻ ማሳካት አይቻልም። ከዚህ ይልቅ ወደ ተግባር በመቀየር ያሰባችሁትን ማሳካት ትችላላችሁ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You