በዓለም ቻምፒዮና መድረክ የሴቶች ማራቶን ድል እኤአ ከ2015 የቤጂንግ ቻምፒዮና ወዲህ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ መልሷል። ቤጂንግ ላይ በአትሌት ማሬ ዲባባ የተገኘው የማራቶን ድል ባለፉት ሁለት ቻምፒዮናዎችም በተከታታይ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሆኗል። 2022 ላይ ጎተይቶም ገብረሥላሴ፣ 2023 ላይ አማኔ በሪሶ በድሉ ደምቀዋል።
የዘንድሮውን የተለየ የሚያደርገው ኢትዮጵያውያን በማራቶን ታሪክ አረንጓዴ ጎርፍ ለመሥራት እስከመጨረሻ ያደረጉት ጥረት ነው። ይህ ጥረት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በመጨረሻው ኪሎ ሜትር በመድከሟ ለጥቂት ባይሳካም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ በርቀቱ ደማቅ ታሪክ ተፅፏል። አማኔ ቡዳፔስት ላይ ወርቁን አጥልቃለች፣ የአምናዋ ቻምፒዮን ጎተይቶም ደግሞ ያለፈው የወርቅ ሜዳሊያ ላይ የብሩን ሜዳሊያ ደርባለች።
አዲሷ ቻምፒዮን አማኔ ቡዳፔስት ላይ የተሠራው አኩሪ ገድል ከዝግጅት ጀምሮ የነበረው የቡድን ሥራ ውጤት መሆኑን ከኢፕድ ጋር በነበራት ቃለምልልስ ተናግራለች። ‹‹እዚህ ስንዘጋጅ የነበረው በቡድን እንደመሆኑ በውድድሩ ላይም በአንድነትና በመደጋገፍ ነበር የሮጥነው። በቡድኑ የተካተቱት በማራቶን ምርጥ የሚባሉ አትሌቶች መሆናቸውም ለድሉ ረድቶናል›› ትላለች አማኔ። ያለፉትን ዓመታት በጉዳት ማሳለፏን የምታስታውሰው አዲሷ የማራቶን ንግሥት፤ በቻምፒዮናው አሸንፋ ባንዲራዋን ለማውለብለብ በመብቃቷ ደስታዋ ወደር የለውም። ‹‹ፈጣሪም በዚህ ክሶኛልና ስኬታማ ስላደረገኝ አመሰግነዋለሁ›› ትላለች።
በውድድሩ ወቅት የነበረው ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ለበርካታ አትሌቶች ከባድ ነበር። ነገር ግን አማኔ ብዙም የተቸገረች ሳትመስል ነበር ውድድሯን በስኬት የፈጸመችው። ከዚህ ቀደም የሮጠችባቸው የዱባይ፣ ሙምባይ፣ ቦስተን፣… ማራቶኖች በሞቃት ነበሩ፤ ስለዚህም አማኔ በሞቃት የአየር ሁኔታ መሮጥ ምቾት ሰጥቷታል።‹‹ከቫሌንሲያ በቀር የተወዳደርኩባቸው ማራቶኖች ሞቃት በመሆናቸው ቡዳፔስት ላይ በቀላሉ ላሸንፍ ችያለሁ። ከዝናባማ ይልቅ ሞቃት ስፍራን ለውድድር እመርጣለሁ፤ በእርግጥ በቫሌንሲያ ማራቶን በዝናባማ የአየር ሮጬ የተቀደምኩት በተለየ ምክንያት እንጂ በአየሩ አልነበረም›› ብላለች።
አዲሷ የዓለም ቻምፒዮን ቀጣይ ዕቅዷ መጪው ጊዜ የኦሊምፒክ እንደመሆኑ ‹‹የወደፊቱን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው፤ የእኔ ፈንታ መሥራት ነው›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
አምና የቻምፒዮናውን ክብረወሰን በመስበር ያሸነፈችው የዘንድሮው የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ጎተይቶም በበኩሏ ‹‹በቡዳፔስት የነበረው ግብግብ ከአትሌቶች ጋር ሳይሆን ከአየር ሁኔታው ጋር ነበር። ፈታኙ ሁኔታም እሱ ነበር፤ ግን ጠንክረን በመሥራታችን ሁኔታውን ተቋቁመን ለድሉ ልንበቃ ችለናል›› ትላለች።
ወጣቷ አትሌትም በተከታታይ ቻምፒዮናዎች ወርቅና የብር ሜዳሊያ ስታስመዘግብ በኢትዮጵያ ማራቶን ታሪክ ብቸኛዋ ሴት አትሌት ነች። ይህንን ተከትሎም የፈጠረባትን ስሜት ‹‹ያሸነፍኩ ያህል ነው የተሰማኝ›› ስትል ትገልጻለች። ‹‹እንኳን በአንድ ዓመት በሁለት ዓመትም ቢካሄድ እንዲህ ዓይነት ውጤት ማግኘት ከባድ ነው። ለእኔ ይህ ትልቅ ድል ነው፤ በሠራሁት መጠንም ጥሩ ሮጫለሁ›› በማለትም ተናግራለች።
ጎተይቶም በኦሪጎኑ ዓለም ቻምፒዮና በድንቅ ብቃት ወርቅ ስታስመዘግብ በወቅቱ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ከቤተሰቦቿ ጋር መገናኘት አልቻለችም ነበር። በዚያ የተረበሸ ስሜት ውስጥ ሆና ለስኬት መብቃቷ አስገራሚ ነበር። አሁን ደግሞ ቡዳፔስት ላይ ከደረሰባት ከባድ ኀዘን በቅጡ እንኳን ሳታገግም ነበር የሮጠችው። እነዚህ ከባድ የስሜት መፈራረቆች ግን አትሌቷን ሊበግሯት አልቻሉም። ጎተይቶም ውድድሩን ስትጨርስ እጅግ የተደሰተችውም አንድም በዚሁ ምክንያት ነው። ‹‹ወደ አቋሜ እመለሳለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረኝም። በእርግጥ የወንድም ኀዘን ከባድ ነው፤ ያውም ታናሽ ወንድሜን ነው ያጣሁት። ከዚያ በኋላ በቦስተን ማራቶን ሮጬ ከብዶኝ ስለነበር ውጤቴ እንዲህ ይቀጥል ይሆን? በዓለም ቻምፒዮናውስ እንዴት እሆን ይሆን? እያልኩ ሳስብ ነበር። ነገር ግን ስፖርት እንደመሆኑ ጽናት ይፈልጋል፤ ያለፈው አልፏል ውጤቴ ወደኋላ ቢመለስም ወንድሜን ግን ልመልሰው አልችልም። ጠንክሬ በመሥራት የማገኘው ሜዳሊያ ለወንድሜ መታሰቢያ ይሆናል በሚል በጽናት ሮጫለሁ›› ትላለች እንቁዋ አትሌት ከዓለም ቻምፒዮናው በፊት የገጠማትን ስታስታውስ።
‹‹ሁሌም በመንፈስ ጠንካራ ነኝ፣ ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማምጣት እጥራለሁ። በዓለም ቻምፒዮና ለሁለት ጊዜ ተሳትፌ ባለ ሜዳሊያ ሆኛለሁ፤ በኦሊምፒክ ደግሞ ተካፍዬ አላውቅም። በመሆኑም እቅዴ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመሆንና ጠንክሬ በመሥራት የሜዳሊያ ባለቤት መሆን ነው›› በማለትም ቀጣይ እቅዷን ጠቁማለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም