ጀግኖቹ በፓሪስ ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ቃል ገብተዋል

በ19ኛው የቡዳፔስቱ ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎ ከዓለም ስድስተኛ፣ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከትናንት በስቲያ በፌዴሬሽኑ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ሀገሩ ሲገባ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ይታወሳል፡፡

በቡዳፔስት ሞቃታማ አየር ንብረት እንዲሁም በአትሌቶች ቅንጅት ማነስ የታጡ ሜዳሊያዎች ብዙዎችን አስቆጭተዋል። የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ አሰልጣኞችና አትሌቶችም ይህን ቁጭት በሽልማት ስነስርዓቱ ወቅት አንፀባርቀዋል፡፡ በዚህም በቀጣዩ 2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ የታዩ ድክመቶችን አርሞ የስፖርት ቤተሰቡ የሚጠብቀውን ውጤት ለማስመዝገብና ለመካስ ከወዲሁ ቃል ገብተዋል፡፡

በዓለም ቻምፒዮና ያጋጠሙትን ችግሮች በመቅረፍ በፓሪስ ኦሊምፒክ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና ቃልን በተግባር ለመለወጥ እንደሚሰሩም አሰልጣኞችና አትሌቶች ተናግረዋል፡፡

በማራቶን ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳለያ እንድታስመዘግብ የቡድን ስራውን በፊት አውራሪነት የመራችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በመጨረሻዎች ኪሎ ሜትሮች በመድከማ የነሐስ ሜዳሊያ ለጥቂት አምልጧታል፡፡ ይህች ኮከብ አትሌት በውድድሩ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ ተሸላሚ ሆናለች።ያለምዘርፍ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረገችው ንግግር ውድድሩ በጣም ጥሩ እንደነበር ገልፃለች፡፡ ‹‹ከፊት እየመራን ስለነበር አረንጓዴውን ጎርፍ ለመድገም አስበን ነበር። ግን አልሆነም ሀገሬ ወርቅ በማግኘቷ ደስተኛ ነኝ›› ያለችው ያለምዘርፍ በውድድሩ የገጠማት ፈተና ለሀገሯ ባይሆን ላትጨርሰው እንደምትችል ተናግራለች፡፡ በውድድሩ ወቅት የነበረውን ከባድ ሙቀት ልትቋቋመው ካለመቻሏ የተነሳም አምስተኛ ሆና ማጠናቀቀን እንኳን ሀኪሞች ነበሩ የነገሯት። ያም ሆኖ ብርቱዋ አትሌት የኢትዮጵያ ህዝብን ለመካስ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ጠንክራ እንደምትሰራም ጠቁማለች፡፡

ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው ሁለት ወርቆች አንዱን በእልህ አስጨራሹ የ10ሺ ሜትር ፍልሚያ ማስመዝገብ የቻለችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በበኩሏ፣ በ5ሺ ሜትር በደረሰባት ጉዳት ውጤታማ መሆን ባትችልም በ10ሺ ሜትር ባስመዘገበችው ድል ደስተኛ እንደሆነች ጠቅሳለች፡፡ በመሆኑም ወርቅም ሆነ ብር ቢመዘገብ ለሀገር በመሆኑ በፓሪስ ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደምትዘጋጅ አስረድታለች፡፡ ለውጤቱ መመዝገብምም አሰልጣኞቿን አመስግናለች፡፡

በማራቶኑ ውጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ሚናን ከተጫወቱት አሰልጣኞች አንዱ ገመዶ ደደፎ፣ ለቀድሞ አትሌቶችና አሰልጣኞች ያለውን ክብርና ምስጋና በመግለፅ ‹‹በትንሽ ስህተት አሸንፈናልም ተሸንፈናልም›› በማለት በሴቶች የተመዘገበውን ትልቅ ድልና በወንዶች ለጥቂት ከእጅ ስለወጣው የብር ሜዳሊያ ተናግሯል፡፡ ውጤቱ የመጣውም በአትሌቶች ከፍተኛ መሰዋዕትነት እንደሆነ ገልጧል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቡድኑ መሪ አትሌት ገዛኸኝ አበራ እንደተናገረው፣ ቡድኑ ከወር በላይ ተሰባስቦ ዝግጅት አድርጓል። በመሆኑም አትሌቶቹ ወደ ውድድሩ ስፍራ እስከ ሚጓዙበት ጤንነታቸውና አቋማቸው ጥሩ የሚባል ነበረ። በውድድሩ ቦታ ያለው ከፍተኛ ሙቀት ግን ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የ5 እና 10ሺ ሜትር ርቀት ውጤት ማምጣት እንዳትችል አድርጓል። በዚህም በቀጣይ ቴክኒካል የሆኑትን ጉዳዮች በማስተካከል ለኢትዮጵያ ውጤት ለማምጣት የእርምት ርምጃ ይወሰዳል። በፓሪስ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ባልተመዘገበባቸው ርቀቶች ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግና የተስተዋሉ ችግሮችን በማስተካከል ህዝቡን ለመካስ እንደሚሰሩም አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ ቡድኑ ያደረገውን ተሳትፎና አጠቃላይ ቆይታ አስመልክታ ባደረገችው ንግግር በቡዳፔስቱ የተስተዋለውን እና በፓሪስ ኦሊምፒክ መደረግ ስለሚኖርበት ጉዳይ አጽንዖት ሰጥታለች፡፡ በውድድሩ ስፍራ በነበረው የአየር ጸባይና በአትሌቶች ቅንጅት ማነስ የተፈለገው ውጤት ባይመዘገብም በፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት እንዲመጣ አስፈላጊው ድጋፍ እና ዝግጅት እንደሚደረግ ቃል ገብታለች። ለዚህም ተገቢውን ዝግጅት ለማድረግና ለመደገፍ ጥረት እንደምታደርግ ተናግራለች፡፡

ቡድኑ በቡዳፔስት ላስመዘገበው ውጤት ማበረታቻና ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማነቃቂያ እንዲሆን ወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳለያን ላስመዘገቡት አትሌቶችና አሰልጣኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ወርቅ፣ ብር እና የነሃስ ሜዳሊያን ላስመዘገቡ አትሌቶች የ60፣ 40ና 30 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላውና ጸሃይ ገመቹ በልዩ ተሸላሚነት የ50ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡ በተጨማሪም ለአሰልጣኞችና ለውጤቱ መመዝገብ ሚና ለተጫወቱ አካላትም ሽልማትና እውቅና ተሰቷል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You