ሥነ-ኮከብ እና የኢትዮጵያ አበርክቶት

ኮከብህ ከኮከቤ የገጠመ ለታ፣

ለማሪያም መቀነት ለገብርኤል ኩታ፣

(ድምፃዊት ፍቅረአዲስ ነቅአጥበብ)

በአሁኑ ጊዜ የሥነ-ኮከብ ጥናት ሳይንስ ለብዙዎች ብርቅ አይደለም። ብርቅ አይሁን እንጂ ቀላል ደሞ አይደለም። በብዙዎችም የሚሞከር ነው ማለት አይቻልም፡፡ የኮከብ ቆጠራ እንዲህ እንደምናወራው ቀላልና “የጠንቋይ ስራ አይደለም” የሚሉ ተከራካሪዎች ኮከብ ቆጠራ በፕላኔቶች እና በከዋክብት አንፃራዊ አቀማመጥ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው የሚያሰምሩበት።

የወደፊቱን ለመመልከት፣ ለወደፊቱ ስለሚጠብቁ ክስተቶች እና ማስጠንቀቂያዎች ለመማር ፋይዳው ብዙ ነው ባይ ናቸው። ኮከብ ቆጠራ ከፍተኛ የሆነ የእውቀት ዘርፍ እንደሆነና በከፍተኛ የትምህርት ተቋምና የጥናት መስኮች ውስጥ ጥናት ይደረግበታል፡፡ ተመራማሪዎችም በዚህ ዘርፍ እስከ ከፍተኛ አካዳሚክ ማዕረግ ድረስ ይዘልቁበታል።

አስትሮሎጂ “የጠንቋይ ስራ” አለመሆኑን የምንረዳው ‹‹ጥንቆላ›› አስማትና ምትሀት ከአስትሮሎጂ ጋር ተቀላቅለው (ለጥፋትና ለማጭበርበሪያ ዘዴ) ያዳበሩት በአስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ነበሩ፡፡ ይህም የአስትሮሎጂ ጥናት ላይ የራሱን መጥፎ ጥላ አጥልቷል። ‹‹በአሁኑ ጊዜ ማጂካል (ምትሀታዊ) አስትሮሎጂ ጊዜ ያለፈበትና ምንም ጥቅምና እውቀት የሌለበት እንደሆነ ታውቋል›› ሲሉ ዶክተር አብነት ስሜ በመፅሃፋቸው ገፅ 283 ላይ አስፍረዋል፡፡

የዶ/ር አብነት ስሜ መፅሃፍ መግቢያ አረፍተ ነገር እንደሚለው አስትሮሎጂ ኮከቦች (12ቱ ነገደ ከዋክብት) በሰው ልጆች ስብእና ላይ ያላቸውን ተፅእኖ የሚያጠና ሲሆን በርካታ ዘርፎችም (ለምሳሌ የህክምና አስትሮሎጂ) ቀደምት የጥናት መስክ መሆኑን ያመላክታል።

በተለያዩ ርእሶች፣ ለምሳሌ “የልደት ቀንዎ ስለ እርስዎ ምን ይናገራል?”፣ “የተወለደቡት ቀን እና ኮከብዎ ስለ እርስዎ ምን ምን ባህሪያትን ይገልፃል?”፣ “የእርስዎን ተፈጥሯዊ ምንነት ያንፀባርቃሉ የሚባሉት የ ‹‹ዞዲያክ›› ምልክቶች እነማን እንደሆኑና በመሳሰሉ ርእሶች የተለያዩ ፀሀፍት የተለያዩ መፃህፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ እለታዊውም ሆኑ ሳምንታዊ ጋዜጦች፤ ሳምንታዊም ሆኑ ወርሀዊ መጽሔቶች ለ ‹‹ሆሮስኮፕ›› ልዩ ቦታን ሰጥተው ሲያስነብቡ ነው የኖሩት። ዛሬም እንደዚሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን፣ ያረዳድ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ ጉዳዩ እንዲህ እንደምንለው ቀላል አለመሆኑን ነው።

እንደ “የእሳት ደህንነት ኢንሳይክሎፒዲያ” መረጃ ከሆነ ዞዲያክና ምልክቱ “የአንድን ሰው ባህሪ እና ዕጣ ፈንታ ለመረዳት ቁልፍ ይሰጣል፡፡ ቆጠራው በፕላኔቶች እና በከዋክብት አንጻራዊ አቀማመጥ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገን ለመመልከት ያግዛል፡፡ ምልክቶቹ (12ቱ) የእኛን የተፈጥሮ ምንነት ያንፀባርቃሉ፡፡ በአንድ ወይም በሌላ የዞዲያክ ምልክት ስር ስለተወለደ ሰው ስውር እና ምናልባትም የማይታወቁ ባህሪያትን፣ ተሰጥኦዎችን፣ ችሎታዎችን ለማወቅ፣ በህይወት ውስጥ ግንዛቤን እንድናገኝ ይረዳናል።

ስለራሳችን፣ ስለምናውቃቸው እና ስለጓደኞቻችን ብዙ አስደሳች እና ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘት ያስችለናል። ራሳችንን ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች ለመጠበቅ ያግዛል፡፡ ይህ የኢንሳይክሎፒዲያው ብያኔ በሌሎች በርካታ ምሁራን ስራዎች ውስጥም ተንፀባርቆ የሚገኝ ብያኔ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ዶክተር ሮዳስ ያበረከተው “አንድሮሜዳ” መፅሃፍም ይንንኑ ያረጋግጣል፡፡

ይህ ከባህረ ሀሳብ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ ፍካሬ ቁጥር (ኒሞሮሎጂ) እና የመሳሰሉት ጋር ቀጥተኛ ዝምድናና ተደጋጋፊነት ያለው የጥናት መስክ እንዲህ እንደ ዛሬው በዓለም ላይ ከመናኘቱ በፊት፣ በጋዜጦችና ኢንተርኔት ገፆች ከመሰራጨቱ አስቀድሞ እነ ማን ጋር ነበር?፣ የእነ ማንስ አእምሮ አፈለቀው? ምን ምን ገፅታዎችስ ነበሩት? የሚሉትን ማየቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ይህ የኮከብ ጉዳይ በበርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ሁሉ እየገባ የአንዳንድ አበይት ጉዳዮች መገለጫ ሆኖ ሲያገለግል ይታያል። ለዚህም አስረጂዎቹ “ኮከባችን አልገጠመም”፣ “ኮከባችሁ ባይገጥም ነው”፣ “ኮከባችን ገጥሟል” የሚሉት አገላለፆች ናቸው። እነዚህ ደግሞ ለፍቅር፣ ለ“የፍቅር ኬሚስትሪ”ም (ከላይ የፍቅረአዲስን ዜማ – ናፍቆት፣ መሻትና ስዕለት (ለማሪያምና ለገብርኤል ስለት) ልብ ይሏል) ለወዳጅነትም ሲያገለግሉ ይታያል። እዚህ ጋር “Astrology: Love and Lifestyle” በሚል ርዕስ የተዘጋጁትን የአንጄላ ማኮርሚክ ስራዎች ቅጽ 1 አንድና ቅጽ 2 ማመሳከር ጉዳዩን በአግባቡ ተረድቶ ለማለፍ ያግዛል።

የኮከብ ቆጠራ ፍልስፍና የግለሰብ ኮከቦችን እንዴት አድርጎ እንደሚገልፃቸው፤ የአገላለፅ ዘዴና ስልቱ እንዴት እንደሆነ መመልከቱም ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ካፔዎችን (የዞዲያክ ምልክታቸው ካፕሪኮርን (Capricorn Zodiac) የሆኑትን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡፡

“ካፕሪኮርን (ከታህሳስ 23 — ጥር 20 የተወለዱ) ሰዎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ሰዎች መንፈሰ ጠንካራ፣ የማይበገር አመለካከት ያላቸው እና ሰዎች እንዲህ አድርጉ ብለው እንዲመክሯቸው የማይፈልጉ ናቸው። በዚህ ወር የተወለዱ ሰዎች ጎበዝ፣ ነገር ግን ሌሎችን የማይሰሙ፣ ጥሩ አለቃ የሚወጣቸው፤ በተፈጥሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማስተማር ብቃት ያላቸው ሲሆኑ ጠንካራ የስራ ስነ-ምግባርን የተላበሱ ናቸው።

እነዚህ ሰዎች የማይታመን ትዕግስት እና ጽናት አላቸው። ረጅሙ ጉዞ እንኳን የሚጀምረው በአንድ ትንሽ እርምጃ እንደሆነ፤ የመጀመሪያው እርምጃ ሁል ጊዜ በጣም ከባድ መሆኑን ስለሚያውቁ ሁል ጊዜ ግባቸው ላይ ይደርሳሉ። የመሰላቸውን ለመናገር ወደ ኋላ የማይሉም ናቸው።

ሌሎችንም በዚሁ መንገድ መግለፅ የዚህ ጥንታዊ ልሂቃን ፍልስፍና የሆነው ኮከብ ቆጠራ (አንድ ሰው የተወለደበትን ቦታ ጂኦግራፊያዊ መጋጠሚያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አንድ ሰው በተወለደበት ጊዜ ከዞዲያክ ምልክቶች ጋር በተያያዘ የፕላኔቶች ሥፍራ) አይነተኛ መለያ ነው።

ኮከብ (Astro – “logy” ሲጨመርበት “Astrology” በመሆን ወደ ጥናት መስክነት (ሥነ-ኮከብ ወይም የኮከቦች ሳይንሳዊ ጥናት) ከፍ የሚል ሲሆን፤ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ የባህርይ፣ የተግባር፣ የማንነት መገለጫ የሚመስለን ቁጥራችን ቀላል አይደለም። እንደ ባለሙያዎቹ ድምዳሜ ከሆነ ይህ “ስህተት” ነው። ማንኛውም አካል ኮከብ አለው፤ በዛ ኮከቡና ኮከብ ቆጣሪው (ሆሮስኮፕ) አማካኝነት ባህሪይው፣ አመሉ፣ ማንነቱ፣ ተክለ ሰውነቱ፣ ጤናው ይመዘናል፡፡ ይለካል፤ ይፈተሻል። ከዶ/ር አብነት ስሜ “ፍካሬ ኢትዮጵያ” መጽሐፍም የምንረዳው ይህንኑ ነው።

ፍካሬ ኢትዮጵያ እንደሚያስነብበን ከሆነ፣ የመጀመሪያው ሰው ”አዳም” እና “መከላከያ ሚኒስቴር” ኮከባቸው ኤሪስ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር ቪርጎ ሲሆን፤ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ካፕሪኮርን ነው። ኤሪሶች ኮከቡ “አዳም” በመሆኑ ምክንያት “ዓለም የእኛ ናት፤ መግዛትም ያለብን እኛ ነን” የሚል አስተሳሰብና አቋም ያላቸው መሆኑ ይነገራል።

በፈጠራው ዓለም ውስጥም ኮከብ የሚሰራ ሲሆን የፍቅር እስከ መቃብሮቹ ገፀባህሪያትም የየራሳቸው ኮከቦች አሏቸው። በዚሁ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ እንደምንመለከተው ጉዱ ካሳ አኳሪየስ ሲሆን፤ ሰብለወንጌል ደግሞ ስኮርፒዮ ናት።

በኃይማኖት (መላእክት) ዘንድም ኮከብ የሚሰራ ሆኖ የምናገኘው ሲሆን፣ ጴጥሮስ ኤሪስ፤ እንድሪያስ ካንሰር፤ ፊሊጶስ ቪርጎ፤ ቶማስ ስኮርፒዮ፤ ማቴዎስ ካፕሪኮርን ሆነው እናገኛቸዋለን። (በዘኒከማሁ፣ ገጽ 384 — 385) እንደተፃፈው፡፡

ወደ አገራትና ከተሞችም ስንመጣ በተመሳሳይ የየራሳቸው ኮከቦች ያላቸው ሲሆን፣ አገረ ግብፅ እና ለንደን ከተማ ጄሚኒዎች፤ ደቡብ አፍሪካ እና ደብረሊባኖስ ፓይሰስ ናቸው። ኢትዮጵያስ?

ዶክተር አብነት በመፅሃፋቸው ገጽ 26 እንዳሰፈሩት ኢትዮጵያ በዋና ኮከቧ አኳሪየስ ስትሆን በአሴንዳንቷ (በስርቀተ ፀሀይ ወይም በመሬት ኮከቧ) ኤሪስ ነች። በሁሉም ነገር ቀዳሚ የመሆን እና የአትንኩኝ ባይነቷ ባህርይ ከዚህ የሚነሳ ነው። በዚህ የአኳሪየስ ዘመን የኤሪስ ኮከብ ባለቤት የሆኑ ልጆቿም በኢኮኖሚው፣ በሥነ-መንግሥቱ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ከመሬት እስከ ማርስ የሚደርስ እመርታን እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል። የኤሪሶችን ችቦ ፓይሰሶች፤ የፓይሰሶችን ችቦ ደግሞ አኳሪየሶች ይቀበላሉ። ያኔ ኢትዮጵያም “ኢትዮጵያ” ትሆናለች።

በበርሊኑ ጉባኤ (እ.ኤ.አ 1884 እና እ.ኤ.አ 1885) አፍሪካን የመቀራመት ውል አሁንም እየተስተዋለ ነው የሚሉ ወገኖች እየበዙ ነው። ለምሳሌ ሊ ዌንግራፍ የተባሉ ፀሀፊ በ“Extracting Profit: Imperialism, Neoliber¬alism and the New Scramble for Africa” (እ.ኤ.አ 2016) ስራቸው ይህንኑ ነው የሚነግሩን፡፡ በዚሁ መሰረት ዋና ዋና የአፍሪካ ተቀራማቾች እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ሲሆኑ፣ የሶስቱም ኮከብ ኤሪስ ነው።

ወደ ጥንታዊው ፍልስፍና ስንመለስ ደግሞ የዓመቱ አስራ ሁለት ወራት በዞዲያክ ህብረ ከዋክብት የተከፋፈሉ መሆናቸውን ያስታውሳል፡፡ በአገር ደረጃ የሚጠቀሱት አራት አገራት ኢትዮጵያ፣ ኢራቅ፣ ቻይና እና ጃፓን ናቸው። የሌሎቹን ትተን ኢትዮጵያን ብንመለከት እንኳን ከጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትነት ምድብ ስር ከአናት እንድትገኝ ካደረጓት አንዱ ይኸው የኮከብ ቆጠራ ሳይንስ እውቀቷ ነው።

ዛሬ ካፕሪኮርን፣ ጂምኒ፣ አኳሪየስ ወዘተ እያልን በዘመን አመጣሽ ስማቸው እናቆላምጣቸው እንጂ ጥንትም በኢትዮጵያ አስትሮሎጂ አዋቂዎች ዘንድ የነበሩና ሐመለ እሳት (ኤሪስ)፣ ስውር መሬት (ቶረስ)፣ ገውዝ ነፋስ (ጄሚኒ)፣ ሸርጣን ውሃ (ካንሰር)፣ አሰድ እሳት (ሊዮ)፣ ሰንቡላ መሬት (ቪርጎ)፣ ሚዛን ነፋስ (ሊብራ)፣ አቅራብ ውሀ (ስኮርፒዮ)፣ ቀውስ እሳት (ሳጁታሪየስ)፣ ጀዲ መሬት (ካፕሪኮርን)፣ ደላዊ ነፋስ (አኳሪየስ)፣ ሑት ውሃ (ፓይሰስ) በሚል የሚታወቁ ነበሩ።

የኮከብ መመሳሰል የተግባር መመሳሰልን ያስከትላል የሚል ድምዳሜ ይህ ጸሐፊ አላጋጠመውም። አያጋጥመው እንጂ በበርካታ ተመሳሳይ ኮኮብ ባላቸው አካላት መካከል የተግባር ተመሳስሎ ሲያጋጥም ግን ይታያል፡፡ ለምሳሌ ዶክተር አብነት እንደጠቀሱት እኛም እንደምናውቀው፣ ፊታውራሪ መሸሻ እና አፄ ኃይለሥላሴ ስርአትን ከማስቀጠል አኳያ)።

ይህንን እንበል እንጂ፣ ይህ የተግባር ተመሳሳይነት አንድ አይነት ተግባርን ከመፈፀም ጋር ሊያያዝም፣ ላይያያዝም ይችላል። ትልቁ ተመሳስሎ እሱ አይደለም። ወሳኙ የመመሳሰል ሁኔታ የሚታየው በአንድ ተግባር ጎላ ብሎ መታየት፣ ወይም ታዋቂ በመሆን ነው፡፡ ለምሳሌ “ጀግና” መሆን። የጀግንነት መገለጫው በተሰማሩበት ሙያ ጀግኖ ሆኖ መገኘት እንደ መሆኑ መጠን በሙያቸው ጀግና የሆኑ፤ “አንቱ”ም የተባሉ በርካቶች ሲሆኑ፤ ይህም ከኮከባቸው ጋር እየተያያዘ ሲገለፅ ይታያል። ጀግና ያልሆነውም እንደዛው ጀግና አለመሆኑ ይተነተናል።

በበርካታ ጥናቶች ላይ ስንመለከት እንደ ኖርነው፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው አለ ከማለት ያላበረከተችው የለም ማለቱ ይቀላል። ሌላው ቀርቶ ከዚህ ከሥነ-ኮከብ ጥናት አኳያ ያለውን ብቻ ብንመለከት የአስተዋፅኦዋ መነሻ አሻራ ከ“ዓውደ ነገሥት” መጽሐፍ ይጀምራል። እዛ ላይ ሁሉም ተብሏል፡፡ ሁሉም ተገልጿል። ምናልባት በአሁኑ ዘመን መነፅር ተመልክተን ይህ ይጎላል፤ ይህ ይበዛል ካላልን በስተቀር።

በዶክተር አብነት መፅሀፍ ውስጥ ተገቢውን ስፍራ ከሰጣቸው የመረጃ ምንጮቹ አንዱ ይሄው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሊቃውንት ውጤት የሆነው ዓውደ ነገሥት ነው። ይህንኑ ተንተርሰው የውጪው ዓለም ቀደምት ምሁራን አስፈላጊውን ጥናትና ምርምር ካደረጉ በኋላ ስለዚሁ መፅሀፍና ስለ ኢትዮጵያ ብሎም ኢትዮጵያዊያን አስተዋፅኦ በጉልህ ያሰፈሩት በዚሁ መጽሐፍ ላይ እንደ ወረደ፣ በመገኛ ቋንቋው በመጽሐፉ አባሪነት ተያይዞ ይገኛል።

ዶክተር አብነት በመፅሃፋቸው ገጽ 386 ላይ በ“ድህረ ቃል” ስር “አልበርት ፓይክ ስለ ኢትዮጵያ የአስትሮሎጂ ጥበብ ጀማሪነት” በ1871 ያሰፈሩትን፤ በገጽ 389 ላይ “ጆን ጃክሰን ስለ ኢትዮጵያ የአስትሮሎጂ ጥበብ ጀማሪነት (“The Ethiopians were the first who invented the science of Stars” (1926) በሚል ርእስ) የፃፈው” እና ሌሎችንም በዋቢነት አስፍሮ እናገኛለን።

በዚህ ውስጥ የተጠቀሱትም ሆነ ያልተጠቀሱ ሌሎች በርካታ ስራዎች መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያ በየዘርፉ የነበራትን እውቀት ብቻ ሳይሆን የነበራትን ተፅእኖ ፈጣሪነት፤ የነበራትን የፍልስፍና ደረጃ፤ የነበራትን ዓለም አቀፍ ብስለት፤ ከሁሉም በላይ የነበራትን የተፈጥሮ እውቀት ነው። አሁን ጥያቄው “እንዴት አድርገን ያንን እናስቀጥል?” የሚለው ነው ራስ ምታቱ። እንዴት እናስቀጥል፣ ወይስ “ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን” በሚለው ተስፋ እንቆዝም? ነፍሳቸውን በገነት ያኑረውና አማረ ማሞ እንዳሉት ጉዳዩ ያነጋግራል፤ ያወያያል፤ ያመራምራል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 27/2015

Recommended For You