ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ህይወት በብዙ አሻሽሏል፡፡ ጥራት ያለው መረጃና የተቀላጠፈ የመረጃ ልውውጥ ከምንፈልገው ይዘት፣ መጠን፤ አይነትና ጊዜ አንጻር ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
ከትምህርት ከጤና፤ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታና የአጠቃቀም ሂደቱን ብንመለከት እንደ ዘርፎቹ አይነት ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድም ይለያያል፣ የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎችም እንዲሁ እንደ አገልግሎቱ አይነትና ስፋት ይለያያሉ፡፡
የመረጃዎቹ አይነት፣ መጠንና ይዘትም እንዲሁ አንድ አይደለም፤ ይህም ሲባል በፅሁፍ፣ በምስል፣ በድምፅ፣ በቪዲዮ ወዘተ በስፋትና በበቂ ሁኔታ፤ የተደራጀ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ፤ ለተለያየ አገልግሎት እየዋለ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።
ዓለም አንድ መንደር ሆነች ሲባል በሌላ አገላለፅ በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ተሳሰረች ማለት ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲነፃፀር ገና በለጋ እድሜው በሰው ልጆች ዘንድ ተቀባይነትና እምነት አግኝቷል፡፡
በአጭሩ ተወዷል፤ ስራን አቀላጥፏል፣ ውጣ ውረድን ቀንሷል፣ ጉልበትንና ወጪን ቆጥቧል፤ ምርትና ምርታማነትን ጨምሯል፤ በየሰው ጓዳና ቤት ድረስ ገብቷል፤ በጥቂት ቁስ አካል የሚፈልጉትን ያህል መጠን መረጃ መያዝ፤ ማደራጀት መለዋወጥ ተችሏል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂ ፋይዳው ከምንለው በላይ ትልቅ ነው። በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር፣ የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ለትምህርት ለግብርና ለጤና ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ የማይታሰብ ከሆነ ሰነባብቷል።
ወጣት ምስክር አዳነ ተወልዶ ያደገው በሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ነው። ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል በተለምዶ ዊንጌት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ኮከብ በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት እንደሌለ ወጣት ምስክር ይናገራል።
በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉ ወይም የደረጃ ተማሪዎች መካከል የነበረው ምስክር በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሏል።
በ2000 ዓ.ም ለትምህርት ባህርዳር የደረሰው ምስክር፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አሁን ላለኝ ማንነት ትልቅ መሰረት የያዝኩበት ነው ይላል፤ ወጣት ምስክር እንደሚናገረው፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮሚፒዩተር የመማር ፍላጎት የነበረው ቢሆንም እርሱ ባህርዳር ዩንቨርሲቲ ሲቀላቀል በጊቢው ይሰጥ ያልነበረው የኮምፒውተር ሳይንስና ኢንጅነሪንግ የትምህርት ፕሮግራም እንደ አጋጣሚ ሆኖ እርሱ ዩኒቨርሲቲውን በተቀላቀለበት ዓመት መጀመሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጥሮታል።
ለትምህርት ፕሮግራሙ የመጀመሪያ ተማሪዎች እንደመሆናቸው በከፍተኛ ትኩረት ነበር ”ትምህርታችንን እንድንከታተል ያደረጉን”” የሚለው ምስክር የነበሩት መምህራን በዘርፉ በቂ እውቀት ያላቸው ስለነበሩ የዳበረ ዕውቀት ይዘን እንድንወጣ አግዘውናል ይላል።
‹‹በልጅነቴ በዋናነት ለመሆን እመኝ የነበረው አስትሮኖመር ነበር›› የሚለው ወጣት ምስክር ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ከባድ ነው ብሎ በማሰብ ትኩረቱን በኮምፒውተር ላይ ማድረጉን ይናገራል።
ሃርድዌር ለሆኑ ነገሮች ትኩረት ይሰጥ የነበረው ምስክር ባህርዳር ዩንቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት ሁለት ወር ለሚቆይ የተግባር ልምምድ አንድ መስሪያ በሄደበት ወቅት ከታዘበው ነገር በመነሳት ኢትዮጵያ ውስጥ የሃርድዌር ማቴሪያል እጥረት መኖሩን በመገንዘብ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ሶፍትዌር ላይ በማድረግ እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ ይናገራል።
”አንድ ኮምፒውተር እና ኢንተርኔት ካለ ዓለም በመዳፍ ላይ እንዳለች አድርጌ ወሰድኩ፤ በቀላሉ ኮምፒውተርና ኢንተርኔት ማግኘት ከቻልኩ የራሴን ሥራ መፍጠር እና ማደግ እችላለሁ ብዬ በማሰብ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ትኩረቴን ሙሉ በሙሉ ሶፍትዌር ላይ አደረኩ፡፡ ይህም ዛሬ ላይ ደርሶ ውጤታማ እንድሆን አድርጎኛል ›› ሲል ይናገራል።
ሙያ ሎጂ ስለተሰኘው የፈጠራ ሥራው ወጣት ምስክር ሲናገር፤‹‹ ለአንድ የፕሮጀክት ሥራ የካሜራ ባለሙያ ስንፈልግ፤ የምንፈልገውን ብቃት ያለው ባለሙያ ማግኘት አልቻልንም፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቁ የሆኑ የፎቶግራፍና ቪዲዮ ማሰልጠኛ ተቋማት ባለመኖራቸው መሆኑ ተረዳን፡፡
የፎቶግራፍ ትምህርት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ይሰጡ የነበሩት ሶስት የማይሞሉ ተቋማት ነበሩ፡፡ እነርሱም ቢሆን ያሉት አዲስ አበባ ከተማ እንጂ ክፍለ ሀገር አገልግሎት አይሰጡም፡፡ በዚህ አጋጣሚ መነሻ ሰዎች ባሉበት ሙያ መማር እንዲችሉ በማሰብ ይህንን በመቅረጽ ወደ ሥራ ገባሁ›› ይላል የሙያ ጥንስሱን ሲያስታውስ፡፡
ይህንንም መነሻ በማድረግ ሙያሎጂ የተሰኘውን የኦላይን የስልጠና ማዕከል መመስረቱን ያስረዳል። በዚህ የቴክኖሎጂ ውጤት የተለያዩ ሙያዎችን ሰዎች ባሉበት ሆነው መማር እንዲችሉ ዕድሉን መመቻቸት ችለናል የሚለው ወጣቱ በኢትዮጵያ ደግሞ ሰዎች ውጤታማ መሆን እንዳይችሉ አንዱ ችግር ቋንቋ መሆኑንና ይህንኑ ለመቅረፍ በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት በመስጠት የተለያዩ ሙያዎችን ኢትዮጵያውያን መማር እንዲችሉ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ተነግሯል።
ሙያ ሎጂ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤት ለብዙዎች እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም የሚለው ወጣቱ ድርጅቱ 17 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለ ተናግሮ በስሩ ከፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ተጠቅመው ብዙዎች የሙያና የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ እንደቻለ፤ ይህም ትልቅ ደስታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ገልጿል።
አሁን ባለው ሁኔታ ወጣቶች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ምጣኔያቸው እየቀነሰ ነው የሚለው ወጣት ምስክር ዩንቨርሲቲ መግባት ብቸኛ አማራጭ እንዳልሆነና ማንም ሰው የተለያየ ሙያ በመማር እራሱን ማሳደግና መለወጥ እንደሚችል ያለውን እምነት ይናገራል። ለዚህም በፈጠረው ቴክኖሎጂ አማካኝነት በተለያየ የሙያ መስክ በቂ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በመጠቀም በሚያውቁት ቋንቋ ሙያ ተምረው ወደ ሥራ መስክ እንዲሰማሩ መንገዱን መክፈቱን ይናገራል።
አሁን ሁላችንም እየሄድን ያለነው ወደ ቴክኖሎጂ ነው የሚለው ወጣት ምስክር፤ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ በመሆኑ አንድ ሰው በቂ የቴክኖሎጂ እውቀት ማዳበር ከቻለ ብዙ ዕድሎች አሉት ይላል። ከኢትዮጵያ አንፃር እንኳ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኘው በቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ ሰው እንደሆነና በዚህ ረገድም ወጣቶች እራሳቸውን ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው ይመክራል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ እንዳለ የሚናገረው ወጣት ምስክር፤ ይህም ለወጣቶች ብዙ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ያስረዳል፡፡ ከኢኮኖሚው ትሩፋቶችም ለመጠቀምም ወጣቶች አቅደው መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ይናገራል፡፡
ነገር ግን ብዙዎች ወጣት የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በካፒታል እጦት, በቶሎ ተስፋ በመቁረጥ እና የንግድ ትምህርት እጦትና መሰል እንቅፋቶች ስለሚያጋጥሟቸው እነዚህን ተግዳሮቶች አልፈው ውጤታማ ለመሆን እንደሚቸገሩ ይገልጻል። ሆኖም ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ማለፍ እንደሚገባቸው ምክሩን ይለግሳል፡፡
ከዚህ ቀደም አብዛኖቹ ሶፍትዌሮች ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ ነበሩ የሚለው ወጣት ምስክር በዚህም ብዙ ሚሊዮን ዶለር ሀገሪቱ ስታጣ እንደቆየች ያስረዳል፡፡ ሆኖም እሱን በመሰሉ ወጣቶች የሚበለፅጉ ሶፍትዌሮች የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራል። ቴክኖሎጂ በጥቂት የሰው ሀይልና ቦታ ትላልቅ ሥራዎች ለመስራት ምቹ መሆኑ ዘርፉን በብዙ ተመራጭ እንደሚያደርገው ይናገራል።
ጊዜው ሰዎችን በአንድም ሆነ በሌላም መንገድ ለቴክኖሎጂ ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ቢሆንም አብዛኛው ሰው ግን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንጂ ወደ ገንዘብ ለውጦ ለመጠቀም ብዙም ሙከራ እንደማያደርግ ይናገራል፡፡ ሚስጢሩ የገባቸው ግን ቢዝነስ አድርገውት እየተለወጡ ይገኛሉ ይላል።
በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ለሀገር ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ የሚናገረው ወጣት ምስክር በተለይ ቴሌ፣ ባንክ፣ ከፊት ለሚጠብቃቸው ውድድር በማሰብ ለቴክኖሎጂ ቅርብ እየሆኑና በራቸውን እየከፈቱ መምጣታቸው ትልቅ ነገር ነው ይላል። እነዚህ ተቋማት በዘርፉ ብዙ የቴክኖሎጂ የሰው ኃይል ቀጥረው የማሰራት አቅማቸው የተሻለ በመሆኑ በዘርፉ የሥራ ዕድል የሚከፍት ነው ይላል።
የተለያዩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እየተስፋፉ እየመጡ ነው የሚለው ምስክር በትራንስፖርት እና በእቃ ማድረስ /Delivery/ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም በተመሳሳይ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ተቋማት እየሆኑ መምጣታቸውን ያስረዳል፡፡ እነዚህ ተቋማት ቢያንስ በአማካይ ከ20 እስከ 30 ሰው ቀጥረው እንደሚያሰሩም ያስረዳል። ነገር ግን አገልግሎቱ በመዲናዋ ብቻ የተገደበ መሆኑ አብቅቶ በክልል ከተሞች ላይም መስፋፋት እንዳለበት ይናገራል።
ወጣት ምስክር እንደሚናገረው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቴክኖሎጂ በትምህርት መቶ ሚሊዮን ህዝብ ማስተማር እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነ ህዝብ ህክምና ተደራሽ ማድረግ አይቻልም። በግብርናውም በቴክኖሎጂ ተጠቅመን ካልሰራን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ መመገብ አይታሰብም፡፡ ትልቅ ቁጥር ያለው ህዝብ ነው ያለውና ወደ እያንዳንዱ ቤት መድረስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ እንደ ሀገር ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህም ጊዜው አሁን ነው ይላል።
ወጣት ምስክር እንደሚለውም በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ጨምረዋል። የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው። ቢሆንም አብሮ መስራት ላይ ችግር እንዳለባቸው የሚናገረው ወጣት ምስክር፤ ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ሌሎችም ተቋማት በራሳቸው መንገድ ነው የሚሄዱት፡፡ ይህ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን የሚወስደውን ጊዜ ረዥም እንደሚያደርገውና እርስበርስ ተነቦ መስራት የሚቻልበት መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ይናገራል።
ቴክኖሎጂ በባህሪው የሚታይ ውጤት ለመምጣት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፣ ስለዚህም ገና በጅምር እያለ ከተኮረኮመ ማደግ እንደማይችል እና አዲስ የተገኘን የቴክኖሎጂ ውጤት የማያዋጣና መጥፎ አድርጎ በመውሰድ ከመግፋት ይልቅ ተስፋ ሰንቆ በመበረታታት ብዙ ነገር ማትረፍ እንደሚቻል ያስረዳል።
ኢትዮጵያ ያላት አማራጭ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሆነ የሚናገረው ምስክር ለዚህ ደግሞ ትምህርት ወሳኝ መሆኑንና የሰው ልጅ የሚቀየረው በመማር ብቻ መሆኑን ያስረዳል። ለትምህርት ደግሞ ቴክኖሎጂ ትልቁ መፍትሔ ነው ይላል።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በማስተማር ብዙዎችን መለወጥ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ፍላጎቱ መሆኑን ተናግሯል።
‹‹ወጣቶች ህይወታቸውን ለመቀየር ከፈለጉ ቀላሉ መንገድ ቴክኖሎጂ ነው። ኮምፒዩተር በመጠቀም ህይወታቸውን መለወጥ ይችላሉ፡፡ ግን ጊዜና ትጋት ይፈልጋል ››የሚለው ምስክር በቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ ገደብ የሚባል ነገር እንደሌለና ከሌላው ሙያ በበለጠ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ ከፍተኛ መሆኑንም ያስረዳል፡፡
ስለዚህ ወጣቶች ለትንሽ ጊዜ ተቸግረውና መስዋዕትነት ከፍለው ትልቅ ውጤት ለማየት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2015