የንግድ ባንክ ሴቶች የሚያስቆጭ የሴካፋ ፍፃሜ ሽንፈት

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ ፍፃሜ ደርሶ ዋንጫ ማንሳት ሳይችል ቀርቷል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትናንት በፍፃሜ ጨዋታ ከታንዛኒያው ጄቲኬ ኩዊንስ ጋር የተፋለመ ሲሆን በመለያ ምት 5ለ4 ተሸንፏል።

ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው የጨዋታ ጊዜ 0ለ0 በሆነ ውጤት በማጠናቀቃቸው ተጨማሪ ሰላሳ ደቂቃ የተፋለሙ ሲሆን በጭማሪው ሰዓትም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በዚህም ቻምፒዮኑን ለመለየት ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቷል።

ንግድ ባንክ በመደበኛውም ይሁን በተጨማሪ ደቂቃው ፍልሚያ ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት የበላይነት ነበራቸው። ያምሆኖ ያገኙትን ተደጋጋሚ ለጎል የቀረበ ዕድል ኳስና መረብ ማገናኘት ባለመቻላቸው አሳዛኝ ተሸናፊ ሆነዋል።

በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን ዋንጫ ቢያነሳ ኖሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮትዲቯር በምታዘጋጀው የካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን መወከል ይችሉ ነበር። ይህ ባለመሳካቱ የውድድሩ ቻምፒዮን ጄቲኬ ኩዊንስ በአፍሪካ መድረክ ታንዛኒያን ወክሎ የሚሳተፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን በዘንድሮው የሴካፋ ቻምፒዮንስሊግ ውድድር ለፍፃሜ ሲደርስ በየጨዋታዎቹ አስደናቂ ብቃት በማሳየት አድናቆት አግኝቷል። በውድድሩ ሦስት ጨዋታዎችን አሸንፎ በአንዱ ብቻ አቻ ተለያይቷል። የጅቡቲውን ኤፍ ኤዲ 8ለ0 በማሸነፍ ውድድሩን የጀመረው ንግድ ባንክ በሜዳና በደጋፊው ፊት ከተጫወተው ካምፓላ ኩዊንስ ጋር 1ለ1 ተለያይቷል። የደቡብ ሱዳኑን ዬይ ጆይንት ስታርስን ደግሞ 4ለ0 በመርታት በአስር ነጥብ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተቀላቅሏል። በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያም የአምናውን የውድድሩ ቻምፒዮን የኬንያው ቪጋ ኩዊንስ የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሙሉ ሰዓት ውጤት በሎዛ አበራ ግብ አንድ አቻ ከተለያየ በኋላ በጭማሪ ደቂቃ በተገኘው የአረጋሽ ካልሳ ጎል በማሸነፍ የፍፃሜው ተፋላሚ ሆኗል። ይህም በውድድሩ የሦስት አመት ታሪክ በተከታታይ ለፍፃሜ የቀረበ የመጀመሪያው ክለብ አድርጎታል።

ንግድ ባንክ ዘንድሮ በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያ የገጠመው ቪጋ ኩዊንስ ባለፈው ውድድር ኬንያ ላይ በሜዳውና በደጋፊው ፊት በፍፃሜ የገጠመው ቡድን ነው። በዚያ ፍፃሜ ፍልሚያም ግልፅ በሆነ የዳኝነት በደል ንግድ ባንክ ዋንጫ ማጣቱ ይታወቃል። ዘንድሮ ግን ንግድ ባንክ ቪጋ ኩዊንስን ከፍፃሜ አስቀርቶ ቁጭቱን ተወጥቷል። በጨዋታውም የቡድኑ አምበል እና የውድድሩ ድምቀት የሆነችው ሎዛ አበራ የሠራችው አዲስ ታሪክ በሴቶች እግር ኳስ ላይ የሚዘነጋ አይሆንም። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የማሸነፊያ ግሩም ግብ ያስቆጠረችው አረጋሽ ካልሳ በውድድሩ ከተቆጠሩ ግቦች አስገራሚ እንዲሁም ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈች ግብ ነበረች። የዩጋንዳው ክለብ ካምፓላ ኩዊንስ ተጫዋች የሆነችው ፋዚላ ኢክዋፑት ስምንት ግቦች በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን ሎዛ አበራ አምስት ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛ ሆናለች። ሎዛ በዛሬው ጨዋታ ያገኘቻቸውን በርካታ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ተጠቅማ ቢሆን ኖሮ ከዩጋንዳዊቷ እኩል ወይም የበለጠ ግብ አስቆጣሪ ሆና የማጠናቀቅ ዕድል ነበራት።

ሦስተኛው የካፍ የቻምፒዮንስ ሊግ በኮትዲቭዋር አቢጃን ኅዳር 2016 ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በአምስት ዞኖች 36 ክለቦች የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ከዞኖቹ መካከል አንዱ ሲሆን በዚህ ዞን ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብን ጨምሮ ዘጠኝ ክለቦች የቻምፒዮንስ ሊጉ ቦታውን ለማግኘት ተፋልመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከዚህ ቀደም በኬንያ እና ታንዛንያ በተካሄዱ የካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድሮች በቅደም ተከትል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን፣ በማጣሪያ ውድድሩ ተሳታፊ የሆነው የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 25/2015

Recommended For You