በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከተሳተፉት ሀገራት መካከል የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ መግባት የቻሉት 46 ብቻ ናቸው። የውድድሩ ድምቀትና የሜዳሊያ ተፎካካሪ የሆነችው ኢትዮጵያም ባስመዘገበቻቸው 9 ሜዳሊያዎች አማካኝነት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ልትሰለፍ ችላለች። ከ5 በላይ ሜዳሊያዎችን ካስመዘገቡ 6 ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በወርቅ ሜዳሊያዎች በመበለጧ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ቻምፒዮናውን አጠናቃለች።
ለዘጠኝ ቀናት በተካሄደው ቻምፒዮና ወራት ብቻ ለሚቀሩት የፓሪሱ ኦሊምፒክ የቤት ሥራ የሰጠ እንዲሁም ቡድኑ ያለበትን ችግር በግልጽ ያመላከተ ሆኖም ነው የተደመደመው። በአስቸጋሪና ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ውስጥ አልፎ የዚህ ውጤት ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ትናንት ማለዳ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች በ34 አትሌቶች የተሳተፈው ልኡኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስ በከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች የአበባ ጉንጉን ተበርክቶላቸዋል።
በደማቁ የአቀባበል መርሀ ግብር ላይም የቡድኑን ቆይታ እንዲሁም የተገኘውን ውጤት የተመለከተ ንግግር ተደርጓል። ቡድኑን በመምራት ወደ ቡዳፔስት ያቀናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ አበራ፤ ለብሔራዊ ቡድኑ ለተደረገው አቀባበል ምስጋናውን አቅርቧል። ለአንድ ወር ተኩል ያህል ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ በውድድሩ የተሳተፈው ቡድን ያስመዘገበው ውጤት ሕዝቡ ከለመደውና አምና ከተገኘው ውጤት አንጻር ያነሰ ቢሆንም ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ ግን ጥሩ የሚባል መሆኑን ገልጿል። ከ34- 35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርስ ሙቀት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ውጤት ማግኘት ቢቻልም፤ በሚጠበቁትና እንደ የ5ሺ ሜትር ባሉት ርቀቶች ደግሞ ውጤት አለመገኘቱ ቅር የሚያሰኝ መሆኑን ጠቁሞ፤ አትሌቶቹ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሷል። በዚህም ሕዝቡ ባይረካም በመጪው ኦሊምፒክ ግን የሚካካስ መሆኑን ቃል ገብቷል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ ቡድኑ ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ ጀምሮ ስለማጠናቀቁ ጠቁማለች። እንደ ደራርቱ ገለፃ፣ አስቀድሞ የታቀደው ከአምናው ያነሰ ውጤት ላለማምጣት ነበር። በአትሌቶቹ ጥረትም ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች የሏትም። ነገር ግን አትሌቶች በግላቸው በሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም ውድድሩ ሲቃረብ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በሚደረግ ዝግጅት ሀገራቸውን ይወክላሉ። ይህ የራሱ ተጽዕኖ ቢኖረውም ብሔራዊ ቡድኑ ግን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና በስፖርታዊ መርሆች በመመራት ውድድራቸውን በማጠናቀቃቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ለፓሪሱ ኦሊምፒክ ደግሞ ውጤቱ የሰመረ እንዲሆን ከወዲሁ ተጋግዞ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።
ሁሉም አሸናፊ ለመሆን በሚወዳደሩበት መድረክ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ በመሆናቸው እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ናቸው። አትሌቶች በቡዳፔስት ያለውን ከፍተኛ ሙቀት በመቋቋም እዚህ በመድረሳቸውም ክብር እንደሚገባቸው ተናግረዋል። መጪው ኦሊምፒክ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው የተለያዩ ስፖርቶች መካከል መገለጫዋ በሆነው አትሌቲክስ ከወዲሁ ሰፊ ዝግጅት ይደረጋል። ኮሚቴው ከሚያደርገው ዝግጅት ባለፈ መንግሥትም አትሌቶች በልዩ ሁኔታ የሚደገፉበትን እንዲሁም አስቸጋሪ የሆነው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመኖር እንዲቀረፍ ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በኦሊምፒኩ ላይ በመላው አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቡድኑን ለመደገፍ ፓሪስ ላይ እንዲገኙ ለማድረግ እየተሠራ በመሆኑ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ‹‹አትሌቶች ያደረጉት ተጋድሎ አስደናቂ ነበር፤ በዚህም ሀገራቸውን በማስጠራታቸው ምስጋና ይገባቸዋል። የተገኘው ውጤትም የሚናቅ ሳይይሆን አጥጋቢ ሊባል የሚችል ነው። በተለይ ሴት አትሌቶች ለውጤት ያደረጉት አስተዋጽኦ አኩሪ ነው።›› በማለት ሴቶች ጠንካራና ኃላፊነትን የመሸከም አቅማቸው የታየበት መሆኑንም አንስተዋል። ለቡድኑ አባላት በቅርቡ የዕውቅና መድረክ እንደሚዘጋጅም ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015