በሃንጋሪ ቡዳፔስት ሲካሄድ የቆየው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የአዘጋጅነት ተራውን ለጃፓኗ ቶኪዮ አቀብሎ ከትናንት በስቲያ ተጠናቋል። ለ9 ቀናት በተካሄደው ቻምፒዮና ላይ ሲካፈል የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድንም ዛሬ ማለዳ ከ12 ጀምሮ ወደ አገሩ ይመለሳል። ቡድኑ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የእንኳን ደህና መጣችሁ ደማቅ አቀባበል ይጠብቀዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች ሁሉ ቀዳሚ የሆነው የዓለም ቻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ በመድረኩ ተሳታፊና ውጤታማ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በመካከለኛው አውሮፓ አገር ሃንጋሪም ቡድኑ የውድድሩ ድምቀት በመሆን ያለፉትን ቀናት አሳልፏል። ከአንድ ወር በላይ በዝግጅት ላይ ቆይቶ ወደ ውድድሩ የተጓዘው ቡድኑ 9 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
በሴቶች 10ሺ ሜትር ርቀት በአትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ የተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ በሴቶች ማራቶንም ተደግሞ ኢትዮጵያን የ2 ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት አድርጓታል። በእነዚህ ርቀቶች ሁለት የብር እና የነሃስ ሜዳሊያዎች በአትሌት ለተሰንበት ጉዳፍ፣ ጎተይቶም ገብረስላሴ እንዲሁም እጃጋየሁ ታዬ ተመዝግቧል። በሴቶች 1 ሺ500 ሜትር በአትሌት ድርቤ ወልተጂ እንዲሁም በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል በዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ ተጨማሪ የብር ተገኝተዋል። በወንዶች 10ሺ ሜትር ደግሞ በአትሌት ሰለሞን ባረጋ እና በወንዶች ማራቶን አትሌት ልዑል ገብረስላሴ የተገኙት የነሃስ ሜዳለያዎችም በሰንጠረዡ ሊካተቱ ችለዋል።
በዚህም በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ስፔን፣ ጃማይካ፣ እና ኬንያ ተበልጣ በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ላይ ልጥቀመጥ ላለች። ዓምና በኦሪገን ከተካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ቁጥር አንጻር በአጠቃላይ በአንድ ሜዳሊያ ሲያንስ፤ በደረጃ ሰንጠዥ ልዩነት በሚያመጣው ወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በሁለት ያነሰ ሆኗል። ለሜዳሊያ ይጠበቁ በነበሩ ርቀቶች በተለያዩ ምክንያት ውጤት ባይገኝም በአንጻሩ ከወርቅ እስከ ነሃስ ያሉትን ሜዳሊያዎች የግላቸው ያደረጉት የ 10ሺ ሜትር የሴቶች ቡድን ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
ቡድኑ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የአበባ ጉንጉን በማበርከት አቀባበል ያደርጉለታል። ለብሄራዊ ቡድኑ የአቀባባል መርሃ ግብር ያዘጋጀው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ትናንት በሰጠው መግለጫ፣ ቡድኑ ወደ አገሩ ሲመለስ እረፍት በስካይላይት ሆቴል ካደረገ በኋላ በአዲስ አበባ የተመረጡ የተለያዩ ጎዳናዎችና አደባባዮች የመዘዋወር ከሕዝብ ጋር ደስታውን ይገልፃል። ይኸውም መነሻውን ከስካይላይት ሆቴል በማድረግ በመስቀል አባባይ፣ እስጢፋኖስ፣ 4ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ቸርቸር ጎዳና፣ ብሄራዊ፣ ለገሃር፣ መስቀል አደባባይ በማድረግ ወደ መዳረሻው ስካይላይት ሆቴል የሚሆን ነው።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የቡድኑን አቀባበል መርሃ ግብር አስመልክቶ በመግለጫው እንደተናገሩት የተገኘው ውጤት ቀላል አይደለም። በውድድሩ የነበረው ፍልሚያ እንዲሁም በቡዳፔስት የነበረው ሙቀት ከባድ ከመሆኑ አንጻር የተገኘው ጥሩ ውጤት መሆኑን አስታውሰውም፣ ካለፈው ዓመት አንጻር የተገኘው ሜዳሊያ ቁጥር ቢያንስም የሚናቅ አይደለም ብለዋል። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርት እንደመሆኑ አሁን ካለበት አሳድጎና አስፍቶ ማስቀጠል ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በመሆኑም መጪውን ኦሊምፒክ ጨምሮ በቀጣይ ውድድሮች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ርበርብ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
በተለይ ስፖርቱ እያስተናገደ የሚገኘውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ችግር በተለይም የመም አለመኖርን ለመቅረፍም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ እንደሆነም ተጠቅሷል። በዚህም የአዲስ አበባ ስታዲየም መም በቀጣይ 2 ወር ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል። በድሬዳዋም በተመሳሳይ እየተገነባ ሲሆን፤ ሥራው በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአትሌቲክስ ቡድኑ የሽልማት መርሃ ግብር በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረግ ሲሆን፤ በቀጣይ ውድድሩን እና ውጤቱን በሚመለከት ደግሞ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን እንደሚነጋገሩም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2015