ጎይቶም ገብረዮሐንስ ይባላል። የሁለት ፈጠራ ሥራዎች ባለቤት ነው። እነዚህም ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠም አደጋን መከላከል የሚያስችል አውቶማቲክ ጠቋሚ መሣሪያ እና የጫማ ሶልን በኬሚካል የሚያጸዳ ማሽን ናቸው። በፈጠራ ውጤቶቹ በ2012ዓ.ም ከአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የፈጠራ ባለቤትነት መብት አግኝቷል።
ጎይቶም ለፈጠራ ሃሳቦቹ መነሻ የሆነው ለነገሮች ያለው ምልከታና ጥልቅ ፍላጎቱ ቢሆንም፣ ወደ ፈጠራ ሥራው እንዲገባ ያደረጉት ዋንኛዎቹ ምክንያቶች ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተመለከታቸው ክስተቶች ናቸው። የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እንዲያስችል የፈጠረው ቴክኖሎጂ ሃሳብ ጥንስስ የሆነው በአንድ አጋጣሚ የተመለከተው ክስተት እንደሆነ ያስታውሳል። ይህም ከመገናኛ ወደ ቦሌ በመሄድ ላይ እያለ ያጋጠመው ነው። በዚያን ወቅት ኤምፔሪያል አካባቢ ሲደርስ እሱ የተሳፈረበት ታክሲ ሹፌር ታክሲዋን አቁሞ አንዲት እናት እንዲሻገሩ ይፈቅዳል። እኚህ እናት ልክ መሻገር ሲጀምሩ በቀኝ በኩል ደርቦ በፍጥነት የሚመጣ ተሽከርካሪ ሳይገጫቸው ለትንሽ ይተርፋሉ።
በወቅቱ ሴትዬዋ በዝግታ ሲሻገሩ ስለነበርም ነው ከአደጋው የተረፉት። እናም በዚያች ቅጽበት ሊፈጠር የነበረውን አደጋ ሲያስበው በእጅጉ ይዘገንነዋል። በዚያው ልክ ደግሞ አጋጣሚው የመፍትሔ ሃሳብ አመንጭ እንዲሆንም እድል ሰጥቶታል። ‹‹ለዚህ የመኪና አደጋ መፍትሔ ያስፈልጋዋል›› እንዲል አደረገው። ወደ ተግባር ሲገባም መጀመሪያ ወደ በአእምሮው የመጣለት ተሽከርካሪው ላይ የሚገጠም መሣሪያ መሥራት ነው፤ ተሳክቶለትም ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠም አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሣሪያ መሥራት ቻለ።
ሁለተኛው የፈጠራ ሥራውም እንዲሁ አጋጣሚ የወለደው መሆኑን ይገልጸል። ኮቪድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለምን ሲያስቃይ የነበረበት ወቅት። እናም ኮቪዲን ጨምሮ ሌሎች በጫማችን ሶል አማካኝነት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታ አመጪ ተህዋስያንን መከላከል የሚያስችለው ማሽን ጎይቶም መሥራት እንዳለበት አምኖ ወደ ተግባር ገባ። ማሽኑ የጫማ ሶልን በኬሚካል ማጽዳት የሚያስችል ነው።
ጎይቶም ሁለቱም የፈጠራ ሥራዎቹን የፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ ሦስት ዓመት ያህል ፈጅቶበታል። ለዚህም ምክንያቶቹ ሁለት ነገሮች ናቸው፤ የመጀመሪያው ወቅቱ ኮቪድ የጠነከረበት በመሆኑ በቢሮዎች የሚያልቁ ተግባራት ማለቅ አለመቻላቸው ነው። ሌላኛውና ሁለተኛው ደግሞ የፈጠራ ሥራዎቹን የሚሰራው ከመደበኛ ሥራው ውጭ ትርፍ ጊዜውን ተጠቅሞ መሆኑ ነው።
ጎይቶም ተሽከርካሪዎች ላይ ስለሚገጠመው አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሣሪያ ጥቅም ሲናገር፤ በተለምዶ ከቀኝ ወደ ግራ የሚሻገሩ እግረኞችም ሆኑ መኪናዎች ሲያጋጥሙ ቆም ተብሎ እንዲያልፉ እድል ይሰጣል። በግራ እስፖኪዮ ስናይ ግን በግራ በኩል ደርቦ የሚመጣ ተሽከርካሪ ስለሚኖር ግራ እጅን አውጥቶ ምልክት በመስጠት እንዲቆም ይደረጋል። በተቃራኒ በኩል ከግራ ወደ ቀኝ የሚሻገሩ ሲጋጥሙን ግን ምልክት መስጠት ስለማይቻል በቀኝ በኩል ደርቦ የሚመጣ ተሽከርካሪ ከፊቱ የሚያልፉ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ስለማይታየው ከፍተኛ አደጋ ሊያደርስ ይችላል። የፈጠራ ሥራው አስፈላጊነት እዚህ ላይ ነው ሲል ያብራራል።
ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠም አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሣሪያ ቀኝ እጃችንን ተክቶ የሚሰራ ሲሆን፤ ከዳሽ ቦርድ ላይ ተገጥሞ ጫን ሲደርግ በቀኝ በኩል ደርቦ የሚመጣ ተሽከርካሪ ፍጥነቱን እንዲቀንስና እንዲቆም ምልክት ይሰጣል።
ጎይቶም እነዚህን የፈጠራ ውጤቶችን ለመሥራት የሚጠቀምባቸው ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ አይነት በጣም ቀላል ቁሳቁስ መሆናቸውን ይናገራል። ለአንድ ተሽከርካሪ በሀገር ውስጥ ግብዓቶች ተጠቅሞ አውቶማቲክ አደጋ ጠቋሚ መሣሪያ ለመግጠም ከ5ሺህ እስከ 6ሺህ ብር ያስፈልጋል። እስካሁን መሣሪያው በአራት ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሟል። ለስምንት ተሽከርካሪዎች ለመግጠም የሚያስችሉ ግብዓቶች ተዘጋጅተዋል።
የመሣሪያ አስፈላጊነት አስመልክቶ መሣሪያው ከተገጠመላቸው አራት ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች እንዲሁም ሌሎች አሽከርካሪዎች ግብረ መልስ መሰብሰብ መቻሉን የሚናገረው ጎይቶም፤ አሽከርካሪዎቹ እስከ ዛሬ እንደዚህ አይነት መሣሪያ ባለመኖሩ ምክንያት የሚደርሰው አደጋ በእጅጉ ከባድ ስለመሆኑ አስተያየት ሰጥተዋል። ‹‹አሽከርካሪዎቹ እግረኞችን ለማሳለፍ ቆመን በቀኝ በኩል ደርቦ የሚመጣ ተሽከርካሪ አደጋ ሲያደርሰባቸው ስንመለከት እኛው እለፉ ብለን ቆመን እግረኞችን ለአደጋ የምናጋልጥ በመሆኑ የአደጋው ተካፋዮች ነን። ስለዚህ እንዲዚህ ዓይነት መሣሪያ መሰራቱ አደጋውን ከመቀነሱም በላይ ለእኛ እፎይታን የሚሰጥ ነው›› ሲሉ አስተያየት መስጠታቸውን ያብራራል።
በተመሳሳይ አደጋውን ያደረሱ ተሽከርካሪዎች አደጋውን በማድረሳቸው ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እንደሚደርሱባቸው ጠቅሶ፣ አሁን መፍትሔው በመገኘቱ እፍይታ እንደተሰማቸው ከተሰበሰበው አስተያየት መረዳቱን ይጠቅሳል። አደጋው አፍጣኝ መፍትሔ ስለሚያስፈልገው መሣሪያ በጥራት ተመርቶ በመኪናቸው ላይ በፍጥነት ተገጥሞ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚጠይቁ አሽከርካሪዎችም በርካታ እንደሆኑ ይናገራል።
በሀገራችን ያሉ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም የሚያደርሱት አደጋ ግን የከፋ ነው የሚለው ጎይቶም፤ ችግሩ የጋራ በመሆኑ ይህንን አደጋ ለመከላከል ሁሉም ሰው ርብርብ ማድረግ ያለበት ስለመሆኑ በርካታ ሰዎች ከሰጡት አስተያየት መረዳቱንም ይገልጻል።
‹‹እስካሁን መሣሪያው መሠራቱን በማበረታታት በፍጥነት ተግባር ላይ እንዲውል የሚፈልጉ ሰዎች እንጂ በመሣሪያው ላይ ቅሬታ ያቀረበ አካል አልገጠመኝም። ለአሽከርካሪውም ቢሆን መኪናው ማሟላት ያለበትን ሁሉ ነገር ሲያሟላ ወይም አንድ ነገር ሲጎድል ያለው በራስ መተማመን እኩል አይደለም። ይህን መሣሪያ በማከናወን ላይ የገጠመ አሽከርካሪ ግን እግረኛን ለማሳለፍ ሙሉ የራስ መተማመን ይኖረዋል›› ይላል ።
እሱ እንዳለው፤ መኪና የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አንድ መኪና ሲያመርቱ ዳሽ ቦርዱ ላይ መጠባበቂያ ቦታዎች አዘጋጅተው ክፍት ያደርጋሉ። ይህንን የሚያደርጉትም አዲስ ሃሳብ ቢመጣ፣ ለተሽከርካሪ የሚያግዝ ፈጠራ ቢኖር በሚል ነው። ዳሽ ቦርዱ እንዳይነካ እስከ አምስት የሚደርሱ ክፍት ቦታዎች ለየተው ይተውለታል። ይህም መኪና የማምረቱ ሂደት አልቆ እንደማይመጣ እና ብዙ ግብዓቶች እንደሚፈልጉ ያሳያል። ይህ ደግሞ የፈጠራ ሥራ የማይቋረጥ እንደሆነም ያረጋግጣል።
በዚህ የተነሳም የፈጠራ ሥራው ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ትራንስፖርት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ እና ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ማበረታቻና እውቅና ማግኘቱንም ጎይቶም ይናገራል።
ሥራውን ለመሥራት መሥሪያ ቦታቸውን(ወርክሾፕ) እስከ መስጠት ድረስ እገዛ እያደረጉ ያሉ ‹‹ዘዊቶ›› የሚባል ዓለም አቀፍ ተቋም እና ‹‹ቢጄአይ›› የመሳሰሉ ተቋማት እገዛ እያደረጉለት እንደሆነ የጠቀሰው ጎይቶም፤ በቀጣይ ይህንን ሥራ በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ሥራውን ለማገዝ ቃል መግባታቸውን ይገልጻል፤ ሌሎች አካላት ቢተባበሩ የበለጠ ሥራው ውጤታማ ይሆናል ሲል ያስረዳል።
ሁለተኛውን የፈጠራ ሥራውን በሚመለከት ደግሞ እንዲህ ብሏል። እሱ እንደተናገረው፤ ሁለተኛው የፈጠራ ሥራው የጫማ ሶልን በኬሚካል የሚያጸዳ ማሽን ነው፤ ማሽኑ የራሱ የጽዳት ግብዓት ለመጠቀም የሚያስችለው ኮንቴነር የተገጠመለት ነው። ማሽኑ ራሱ ቆሻሻዎችን ስቦ የሚያስቀምጥበት ማከማቻ አለው። ለእጅ የሚሆን ሳኒታይዘር የተዘጋጀለትም ነው።
መኖሪያ ቤት ወይም ቢሮ ለማጽዳት የምንጠቀመው ኬሚካል በጤናና በአየር ንብረት ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅእኖ የሚከላከል መሆኑን ገልጾ፣ ማሽኑ ለቢሮዎች፣ ለሆቴሎች፣ ለእምነት ተቋማት፣ ለገበያ ማዕከላት፣ ለጤና ተቋማት እና ለመሳሳሉ ቦታዎች አገልግሎት መስጠት ይችላል ይላል። ወደ እነዚህ ቦታዎች የሚገባ ሰው የጫማውን ሶል በማሽኑ ካጸዳ በኋላ ስለሚገባ የቤቱን ወለል ለማጸዳት ጥቅም ላይ የሚውሉትን ኬሚካሎች በማስቀረት ወለሉን ካለ ኬሚካል ለማጽዳት እንደሚያስችል ያብራራል።
ስለዚህም ይህ ጥቅሙና መሰል ሥራዎቹ ታይቶ ማሽኑ በጤና ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን እና በሚመለከታቸው አካላት እውቅና ማግኘቱን ተናግሯል። ማሽኑ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ሲውልም የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ባሉት መዋቅሮች ሁሉ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል የተገባለት መሆኑን ይገልጻል።
በጫማችን ታችኛው ሶል ይዘናቸው ከቦታ ቦታ የምንቀሳቀሰው ተላላፊ በሽታዎች በርካታ ናቸው የሚለው ጎይቶም፤ ኮቪድ የተከሰተ አካባቢ ላይ የቅድመ ጥንቃቄ ርምጃዎች ጠንከር ያሉ እንደነበሩ አስታውሶ፣ ከኮቪድ በኋላ ግን ብዙ ነገሮች ተትተዋል፤ ኮቪድንም ሆነ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል አቅማችንም ተዳክሟል ሲል ያመለክታል። ወደፊትም ከአኗኗር ዘይቤያችንና ከግሎባላይዜሽን ጋር የሚመጡ ተያያዥ ብዙ ነገሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ ያለው ጎይቶም፣ ቅድመ ጥንቃቄዎች የግድ ባህልና ልምድ ልናደርጋቸው ይገባል ሲል ይመክራል።
እሱ እንዳብራራው፤ ማሽኑ ተላላፊ በሽታዎችን በመቀነስ ጤናን ለመጠበቅ በእጅጉ ያግዛል። ሌላው ቀርቶ አሁን ላይ እንደሚታየው በሆቴሎች አካባቢ ከላይ ጫማ ማጽጃ የተገጠመላቸው አሉ። የተለያዩ ምግብ የሚሠራባቸው፣ የሚቀርብባቸውና ምንጣፎች ያሉባቸው ቦታዎች ላይ ግን ይህ እንብዛም አይታይም። ከላይ ጫማቸው ጽዱ ቢሆንም ታችኛው ግን ተቃራኒ ነው። ይህ ደግሞ በርካታ በዓይን የማይታዩ በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን ወደ ውስጥ እንዲገቡ እድል ይፈጥራል። በዚህም ለበሽታ ተጋላጭ መሆን እንደሚከሰት ጠቁሞ፣ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋልም ይላል።
ጎይቶም የፈጠረውን ማሽን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አሁን ላይ ባለው ዋጋ ከ25ሺህ እስከ 30ሺህ ብር ይፈጃል። ‹‹እነዚህን ሥራዎች ተግባር ላይ ለማዋል የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋል። ሃሳብ ያለው ሰው የፋይናንስ ድጋፍ ካላገኘ የትም መድረስ አይችልም። ስለዚህም ሥራዎቼን እውን ለማድረግ ሃሳቡን ይዤ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ። ›› ይላል።
ጎይቶም እንዳብራራው፤ አሁን ላይ ለፈጠራ ውጤቶች ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጣቸው ነው። በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ክትትል አድርጎ መወዳደርም የሚቻልበት እድል አለ።
ይሁንና የራስን ክፍተት መሙላት ይገባል የሚለው ጎይቶም፤ አሁን እርሱ በዚህ መልኩ እየተጓዘ እንደሆነም ያነሳል። በቀጣይም በውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ያምናል። እነዚህ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች ተሠርተው ያሉ ቢሆኑም አደጋዎችን ማስቀረት ያልቻሉ በመሆኑ አደጋዎቹ እየተባባሱ ናቸው ሲል ይጠቁማል። የፈጠራ ውጤቶቹ በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግን እንደሚጠይቁ ጠቅሶ፣ ወደ ተግባር ለመተርጎም አጋሮች በማፈላለግ ላይ መሆኑንም ይናገራል።
‹‹በተለይ አሁን ላይ የመኪና አደጋ በየዓመቱ በርካታ አምራች የሆኑ ዜጎችን እያሳጠና በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር የንብረት ውድመት እያስከተለ ነው። ይህ ችግር ደግሞ እንደሚፈጠረው አደጋ አይነት እየታየ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል›› የሚለው ጎይቶም፤ በቀጣይም በአፋጣኝ ተግባር ላይ ለማዋል ቃል የገቡትን በማስታወስ እንደሚሰራም ያስረዳል።
‹‹አካባቢያችን ላይ ልብ ብለን ካየናቸው ብዙ መፍትሔ የሚሹ ችግሮች አሉ፤ በንድፍ ሃሳብ ከሦስት በላይ የሚሆኑ ችግር ፈቺ ሃሳቦች አሉኝ። ቅድሚያ የሰጠኋቸው አንገብጋቢ ለሆኑት ነው። ሃሳብ ሁሉም ሰው ዘንድ አለ። ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ከማውጣት አንጻር ካልሆነ በስተቀር ብዙ ችግሮች በአካባቢያችን ላይ ያሉ ናቸው፤ መፍትሔዎቹም እንዲሁ›› ይላል።
ችግር ፈቺ ተብለው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሃሳቦች ወደ ተግባር ሳይቀየሩ መደርደሪያ ላይ ሆነዋል። ሌላ ሃሳብ ማመንጨት ችግሩ መፍትሔ ስለማይሆን የሚመለከታቸው አጋር አካላት እነዚህ ሃሳቦች ከመደርደሪያ ላይ የሚወርዱበትን አሰራር በመዘርጋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ለዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ሀገርን በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመደገፍ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። የውጭ ምንዛሪን ለማግኘትም ሁነኛ መፍትሄ ነው። የሀገርን ገጽታ ከመለወጥ አንጻርም የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም ይህንን ሁሉ ጥቅም ተመልክቶ መሥራት የግድ መሆኑን ያመለክታል። የፈጠራ ሥራዎች ተግባር ላይ እንዲውሉ ለማድረግም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝቦ፣ እሱም ‹‹ ኑ አብረን እንስራ›› ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2015