በሀንጋሪ ቡዳፔስት ባለፉት አስር ቀናት ተካሂዶ ትናንት በተጠናቀቀው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ሲጠበቅ በነበረው የወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል። ባለፉት ሁለት ቻምፒዮናዎች በእያንዳንዱ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን ማሳካት የቻሉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፤ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ መሆን አልቻሉም።
በከፍተኛ ሙቀትና ወበቅ በታጀበው የትናንት ማለዳ የወንዶች ማራቶን ውድድር እስከ መጨረሻው እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገው አትሌት ልዑል ገብረስላሴ በ2:09:19 በቻምፒዮናው ለኢትዮጵያ ሦስተኛውን የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግቧል።
ሚልኬሳ መንገሻ በ 2:10:43 6ኛ እና ፀጋዬ ጌታቸው በ2:11:56 ሰዓት 17ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። አምና በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌት ታምራት ቶላ ከብዙ ትግል በኋላ በጨጓራ ሕመም ምክንያት ከ35 ኪሎ ሜትር በኋላ ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ተገዷል። በውድድሩ 85 አትሌቶች ተሳትፈው 25ቱ በነበረው ሙቀት የተነሳ ለማቋረጥ ተገደዋል።
የዩጋንዳው ቪክቶር ኪፕላንጋት 2:08:53 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። ትውልደ ኢትዮጵያዊው የእስራኤል አትሌት ማሩ ተፈሪ በውድድሩ መጨረሻ ሜትሮች ልኡል ገብረስላሴ መድከሙን ተከትሎ 2:09:12 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያን ሊያጠልቅ ችሏል።
አትሌት ልዑል ገብረስላሴ በውድድሩ ወቅት የነበረው ከፍተኛ ሙቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደ ቡድን ያሰቡትን እንዳያሳኩ ማድረጉን ገልጿል። “ውድድሩ ጥሩ ነበር ነገር ግን ሙቀቱ እየጨመረ መጥቶ ፈታኝ ሆኖብን ያሰብነውን ማሳካት አልቻልንም የነሐስ ሜዳሊያ ነው ያመጣነው ወርቅ ባለማምጣታችን ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲልም አስተያየት ሰጥቷል።
በማራቶን ከወሰደው የነሐስ ሜዳሊያ በኋላ የኢትዮጵያ ሜዳሊያ ብዛት 9 (2 የወርቅ ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ) ሜዳሊያዎች ደርሷል። እስከ ወንዶች ማራቶን ማጠናቀቂያ ድረስ ከ200 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ2,000 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል። 42 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 18 የዓለም ሻምፒዮናዎች በማራቶን የወሰደቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት 12 ናቸው። በወንዶች 3 የወርቅ፤ 6 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያዎች ናቸው፡፡ ሦስቱን የወርቅ ሜዳሊያዎች ታምራት ቶላ በ2022፣ ገዛኸኝ አበራ በ2001 እንዲሁም ሌሊሳ ዴሲሳ በ2019 አግኝተዋል፡፡ 6 የብር ሜዳሊያዎችን የወሰዱት ከበደ ባልቻ በ1983፤ ሌሊሳ ዴሲሳ በ2013፤ የማነ ፀጋየ በ2015፤ ታምራት ቶላ በ2017 እንዲሁም ሞስነት ገረመው በ2019ና በ2022 እኤአ ነው፡፡ 3 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ደግሞ ፀጋዬ ከበደ በ2009፤ ፈይሳ ሌለሳ በ2011 እንዲሁም ታደሰ ቶላ በ2013 እኤአ ላይ አግኝተዋል።
ምሽት በተካሄደው የወንዶች 5ሺ ሜትር ፍፃሜም ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አምናው ሜዳሊያ ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል። የ5ሺ ሜትር ክብር ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመካከለኛ ርቀት በተለይም የ1500 ሜትር አትሌቶች ድል እየሆነ መጥቷል። ከትናንት በስቲያ በሴቶቹም ተመሳሳይ ርቀት ይህ የተስተዋለ ሲሆን፤ በትናንት ምሽት የወንዶች ውድድርም ሜዳሊያ ያስመዘግባሉ ተብለው የተጠበቁት ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሀጎስ ገብረህይወትና በሪሁ አረጋዊ የታክቲክ ፍልሚያውን በድል መለወጥ ሳይችሉ 5ኛ፣6ኛና 8ኛ ሆነው አጠናቀዋል።
ኖርዋዊው ጃኮብ ኢንገብሪግሴን በርቀቱ ዳግም ቻምፒዮን ሲሆን፤ ስፔናዊው ሞሐመድ ካቲር የብር፣ ኬንያዊው ጃኮብ ክሮፕ የነሐስ ሜዳሊያ ወስደዋል። በምሽቱ የ3ሺ ሜትር መሠናክል የሴቶች ፍጻሜም ሲምቦ አለማየሁ፣ ዘርፌ ወድማገኝ፣ ሎሜ ሙለታ ሜዳሊያ ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል። ዘርፌ ወንድማገኝ 4ኛ ሆና ባጠናቀቀችበት ውድድር ትውልደ ኬንያዊቷ የባህሬን አትሌት ያቪ ዊንፍሬድ የወርቅ፣ ኬንያውያኑ ቢትሪስ ኪፕኮይችና ፌዝ ቺሮቲች የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ወስደዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም