ከ13 ወራት በኋላ ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን ዳግም የዓለም ቻምፒዮን መሆኗን አረጋግጣለች። የኢትዮጵያ የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት አማኔ በሪሶ በቻምፒዮናው ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ፤ የአምናዋ ቻምፒዮን ጎተይቶም ገብረስላሴ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።
በትናንቱ ማለዳ ውድድር ረጅሙን የ42 ኪሎ ሜትር ፍልሚያ አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአስደናቂ የቡድን ሥራ በመተጋገዝ ለተፎካካሪዎቻቸው ከባድ የነበረውን ሙቀት መቋቋም ችለዋል። የነበራቸው የቁጥር የበላይነትና የቡድን ሥራም ጠንካራ የሥነልቦና የበላይነት አላብሷቸው ነበር። ይህም የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ ለመስራት እድል ፈጥሮላቸው ነበር። ያምሆኖ በነበረው ከፍተኛ ሙቀት ሦስቱንም ሜዳሊያ ማሳካት አልቻሉም።
በማራቶን ከታዩ ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው አማኔ በሪሶ በአስደናቂ ብቃት 2፡24፡23 የሆነ ሰዓት አሸናፊ የሆነችው አማኔ፣ ዘንድሮ በተካሄደው የቦስተን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ብትይዝም በቫሌንሲያ ማራቶን ያስመዘገበችው 2:14:58 ሰዓት ከዓለም የምንጊዜም የማራቶን ፈጣን ሰዓት ሦስተኛ ነው።
የአምናዋ ቻምፒዮን አትሌት ጎተይቶም ገብረስላሴ 2፡24፡34 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያውን የግሏ ማድረግ ችላለች። እአአ በ2021 የበርሊን ማራቶን አሸናፊ እንዲሁም በቶኪዮ ማራቶን ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው። ባለፈው ዓመት የኒውዮርክ ማራቶን በተመሳሳይ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር የፈፀመችው።
እኤአ 2015 ላይ በቤጂንግ ቻምፒዮና በማሬ ዲባባ የተመዘገበው የመጀመሪያው የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ባለፈው በኦሪገን በጎተይቶም ገብረስላሴ መደገሙ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ በአትሌት አማኔ በሪሶ የወርቅ ሜዳሊያው ሰልሷል።
ለሁለት ሰዓታት ቡድኑን ከፊት በመምራት ፀሀይ ገመቹ ለድሉ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። እሷ ትልቁን ሥራ ጨርሳ አቋርጣ ስትወጣም አሸናፊዋ አማኔ በሪሶና የአምናዋ ቻምፒዮን ጎተይቶም እንዲሁም ያለምዘርፍ የኋላው ውድድሩን ተቆጣጥረው ወደፊት ገፍተዋል። ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ግን ያለምዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያ ለማጥለቅ የቻለችውን ሁሉ ጥረት አድርጋ አልተሳካላትም። በዚህም 2፡26፡13 ሰአት 5ኛ ሆና አጠናቃለች።
ይህ በርቀቱ በታሪክ ለኢትዮጵያ ሦስተኛው ወርቅ ሲሆን፤ በሴቶች ወርቅና ብር ሲመዘገብም የመጀመሪያ ነው። የአምና ቻምፒዮኗ ጎተይቶም ዳግም ቻምፒዮን በመሆን የኤድና ኪፕላጋትን ታሪክ የመጋራት እድል ቢኖራትም የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ በራሱ በተከታታይ ቻምፒዮናዎች ወርቅና ብር በማጥለቅ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አድርጓታል። የብር ሜዳሊያው በራሱም በቻምፒዮናው ታሪክ ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን ያስመዘገበችው የመጀመሪያ ነው።
ውድድሩ እጅግ ጥቂት እስኪቀረው ድረስ የታገለችው ያለምዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያውን ብታጠልቅ ኖሮ ኢትዮጵያውያን እኤአ 2011 ዴጉ ላይ ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሦስት በማጠናቀቅ የሠሩትን ታሪክ መጋራት ይችሉ ነበር። ያምሆኖ አሁን ያስመዘገቡት ውጤት ለአትሌቶቹም ለኢትዮጵያም እጅግ የደመቀ ወደፊት በታሪክ ሊረሳ የማይችል ነው። ሞሮኳዊቷ ፋጡማ ጋርዳዲ 3ኛ በመሆን ድሉ በአፍሪካውያን እንዲቀር አድርጋለች።
ምሽት ላይ በተካሄደው የሴቶች 5ሺ ሜትር ፍፃሜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአሸናፊነት የታጩ ቢሆንም ሜዳሊያ ውስጥ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። በታክቲክ ፍልሚያ በታጀበውና እስከመጨረሻዎቹ ሜትሮች ድረስ በርካታ አትሌቶች በአጀብ በተጓዙበት ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ኪፕየጎን በውድድሩ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳሊያዋን ስታሸንፍ፣ ሆላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን ሁለተኛ እንዲሁም ሌላኛዋ ኬንያዊት ቢያትሪስ ቺቤት ሦስተኛ በመሆን የሜዳሊያ ሰገነት ላይ የሚያስወጣቸውን ድል አስመዝግበዋል።
በውድድሩ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች እጅጋየሁ ታዬ አምስተኛ፣ መዲና ኢሳ ስድስተኛ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ ሰባተኛ እንዲሁም ጉዳፍ ጸጋይ 13ኛ ሆነው አጠናቀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም