19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሀንጋሪ ቡዳፔስት ለ9 ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ነገ ይጠናቀቃል። ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን በያዘው ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚካፈሉባቸውና በእጅጉ የሚጠበቁባቸው የሴቶች፣ ነገ ደግሞ የወንዶች የማራቶን ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ዛሬ ማለዳው ከ2 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፤ የወንዶቹ ውድድርም ነገ ጠዋት በተመሳሳይ ሰዓት ይደረጋል፡፡ በርቀቱ ኢትዮጵያዊያን የአትሌቲክሱ ዓለም ከዋክብት የማሸነፍ ቅድመ ግምትን ሲያገኙ፤ ኢትዮጵያም በቻምፒዮናው ተጨማሪ ወርቆችን በሁለቱም ጾታ ከውድድሩ ትጠብቃለች፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ታሪክ ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታ 5 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሃስ በጥቅሉ 15ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ከነዚህም ውስጥ 12ቱ ሜዳለያዎች በወንዶች ሲመዘገቡ 3ቱ በሴቶች የተገኙ ናቸው። በዚህ ውድድር በሚመዘገቡት ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው የተሻለ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ይረዳታል፡፡ በሁለቱም ጾታዎች የወቅቱ ቻምፒዮናዎች ጎተይቶም ገብረሥላሴ እና ታምራት ቶላን ጨምሮ 8 የርቀቱን ፈጣን ሰዓት ባስመዘገቡ አትሌቶች ትወከላለች፡፡ በኦሪገኑ ቻምፒዮና በሶስት ሜዳሊያዎች መመለስ የቻለው የማራቶን ቡድኑ ዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ተስፋ ተደርጎበታል፡፡
በቶኪዮ ማራቶን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችው ብርቅዬዋ አትሌት ጎተይቶም ዘንድሮም ለአሸናፊነት ትጠበቃለች፡፡ አትሌቷ በመድረኩ ያላት ፈጣን ሰዓት አምና በኦሪገኑ ቻምፒዮና ያስመዘገበችው 2፡18፡11 ሲሆን፤ ይህም ለአሸናፊነት ተጠባቂ አድርጓታል፡፡ በዝግጅት ወቅት ከአየር ንብረትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም በቂና ጠንካራ ዝግጅትን አድርጋለች፡፡ ይሁንና በዛሬው ውድድር በርካታ ተፎካካሪዎች በመኖራቸው ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቃታል፡፡ ከእነዚህም ግንባር ቀደሟ ኬንያዊቷ አትሌት ሮዝመሪ ዋንጂሩ ናት፡፡ አትሌቷ ፈጣን ሰዓትን ካስመዘገቡ አትሌቶች አንዷ ብትሆንም ኢትዮጵያዊን አትሌቶች በቀላሉ እጅ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
የቫሌንሲያ ማራቶን ፈጣን ሰዓት ባለቤት አማኔ በሪሶ ሌላኛዋ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያ ታስመዘግባለች ተብላ የምትጠበቅ ጠንካራ አትሌት ነች፡፡ አትሌቷ ባስመዘገበቻቸው የማራቶን እና የግማሽ ማራቶን ፈጣን ሰዓቶች ምክንያት በዛሬው ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኗ የሚጠበቅ ነው። ኢትዮጵያን የሜዳለያ ቅድመ ግምት እንድታገኝ ያደረገቸው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላውም በዛሬው ፉክክር ተካታለች። ምንም እንኳን በመድረኩ ሀገሯን ወክላ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትሳተፍ ቢሆንም በዓመቱ በተካፈለችባቸው ውድድሮች የፈጣን ሰዓት ባለቤት በመሆኗ ኢትዮጵያ የመድረኩን የበላይነት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚናን እንደምትጫወት ይጠበቃል። ፀሐይ ገመቹም ሌላኛዋ የመድረኩ አድማቂና የቡድኑን ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ እንደምትጨምር ይጠበቃል፡፡ አትሌቷ በውድድር ዓመቱ በቶኪዮ ማራቶን 2፡16፡56 የሆነ ፈጣን የግል ሰዓት ባለቤት በመሆኗ ኢትዮጵያ ለአሸናፊነት እንድትጠበቅ ማድረግ ከቻሉት አትሌቶች ውስጥ አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡
በወንዶች በኩል እአአ በ2022 በኦሪገን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 2:05:36 የሆነ የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ያሸነፈው አትሌት ታምራት ቶላ በዓመቱ ያስመዘገባቸው ፈጣን ሰዓቶች ከግምት ውስጥ ሲገቡ በዘንድሮ ውድድርም ድሉን ይደግማል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ አትሌቱ ዘንድሮ በተካፈለባቸው የውድድር መድረኮች በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ እአአ 2021 በአምስተርዳም ማራቶን 2፡03፡39 የሆነ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ነው፡፡ ይኸውም በቡዳፔስት ድሉን በመድገም በዓለም ቻምፒዮና መድረክ ሶስት ሜዳሊያዎችን በርቀቱ ያገኘ ብቸኛው አትሌት የመሆን እድሉን ያሰፋዋል በሚል ይጠበቃል፡፡
ታምራት በለንደን ማራቶን ውድድሩን በሶስተኛነት ቢጨርስም ያስመዘገበው ሰዓት ፈጣን በመሆኑ አትሌቱን ከተፎካካሪዎቹ በላይ ለድል እንዲጠበቅ አድርጎታል። ዘንድሮ ከእሱ በላይ ፈጣን ሰዓትን ማስመዝገብ የቻሉት የኬንያና ሌሎች ሀገራት አትሌቶችን የሚፎካከር ቢሆንም በመድረኩ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለወርቅ ሜዳሊያ እንደሚያበቃ ተስፋ ተደርጎበታል፡፡
እአአ የ2018 የዱባይ ማራቶን አሸናፊና የፈጣን ሰዓት ባለቤቱን ልዑል ገብረሥላሴን ጨምሮ ጸጋዬ ጌታቸው እና ሚልኬሳ መንገሻ ከ2 ሰዓት ከ 05 ደቂቃ በታች ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ በመሆናቸው በቡድን ሥራ የኬንያዊያን አትሌቶችንና ሌሎች የርቀቱ ተፎካካሪዎችን ለማሸነፍ የሚያደርጉት እገዛ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2015