“ግብረ ሰዶም ኃይማኖትንና ባህልን በመጻረር ትውልድ እንዳይቀጥል የሚያደርግ ነው”ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ነጋሽ ዘወይንዬ ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ነጋሽ ዘወይንዬ ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ላለፉት 28 ዓመታት የማህበረ ወይንዬ አቡነ ተክለኃይማኖት መሥራችና ሰብሳቢ፤ በባህል ታሪክ እሴት ላይ የሚሠራ ሰገን ዘ ኢትዮጵያ ቦርድ መስራችና ሰብሳቢ ፣ ላለፉት 21 ዓመታትም የገዳማትን ታሪክ በመመራመር የተለያዩ ሥራዎችን የሠሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

በዚህም ከ 100 በላይ የኢትዮጵያ ገዳማትን አጥንተዋል፤ በሌላ በኩልም የግብረሰዶምን አስከፊነት ላይ የተለያዩ 19 ሀገራት በመዞር ምርምርን በማድረግ ሀገራቸውንና ትውልዱን ከችግሩ ለማዳን ለ15 ዓመታት ያህል በብቸኝነት በርካታ ተግባራትን እያከናወኑና እያከናወኑም ያሉ ናቸው፡፡

በአሃዱ ሬዲዮ ላይ የአሃዱ መናገሻ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ከመሆናቸውም በላይ በድምጽ ብልጫ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሚል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በመቀጠል ሶስተኛ ሆነው ሽልማትን የተቀበሉም ናቸው፡፡ ከሰባት ጊዜ በላይ የተለያዩ አዋርዶችንና ወርቆችንም ለመሸለም የቻሉ ስለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡ ከ60 በላይ የምስክር ወረቀቶችም አሏቸው፡፡ እኛም የዛሬ የዘመን እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ ማህበር መቼ ተቋቋመ?

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ፦ ማህበሩ የተመሠረተው ዿጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ሲሆን አራት ዓመት ሆኖታል። ከዛ በፊት ግን ላለፉት 11 ዓመታት በግሌ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ሳደርግ ነበር። በጠቅላላው በዚህ ሥራ ውስጥ 15 ዓመታትን አሳልፌያለሁ፡፡ ማህበሩ መጀመሪያ ወደወይንዬ አቡነ ተክለኃይማኖት ማህበር አምጥቼ ነበር ሥራዎችን የጀመርኩትና ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ደብዳቤ አስገብተን ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም የተሰኘው ማህበር እንዲመሠረት የሆነው። ነገር ግን ማህበረ ወይንዬ አቡነ ተክለኃይማኖ ኃይማኖታዊ በመሆኑና ግብረሰዶም ደግሞ የሁሉም ችግር ስለሆነ ሁሉንም ያሳተፈ ሀገራዊ ማህበር ለማድረግ ከኃይማኖታዊ ተቋሙ ወጥቶ ራሱን ችሎ እንዲቆም በማድረግ በዓለም ላይ ብቸኛ ጸረ ግብረሰዶም ማህበር በመሆን ተቋቁሟል።

በነገራችን ላይ ይህ ማህበር ብቸኛው ነው ስንል አንዳንዶች ግር ይላቸዋል፤ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ሌዝቢያንና ጌ ማህበር (international lesbian and gaye association) ( ILGA) በዓለም ላይ ከተመሠረተ 45 ዓመት አልፎታል። በዓለም ላይ ከ 700 እስከ 1 ሺ ቅርንጫፎችን ዘርግቶም በተለያዩ መንገዶች ግብርሰዶማውያንን የሚያግዝ ሃሳቡንና ተግባሩን የሚያስፋፋ ተጽዕኖ የሚፈጥር ድርጅት ነው።

ይህንን ተግባር የሚቃወም ግን በኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶማውያን እንከላከል የሚለው የእኔ ማህበር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማህበርም እንደ ኒዮርክ ታይምስ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስና ሌሎቹም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በድሃ ሀገር ላይ ይህንን እኩይ ተግባር የሚቃወም ማህበር በማለት ትልቅ ሽፋን የሰጡትና የዘገቡለት ነው፡፡ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ግን ጆሮ የተነፈገው ሥራውም እንዲዘገብ ያልሆነ ስለመሆኑ መናገር እችላለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ማህበሩ ሲቋቋም ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው ምን ነበር?

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ፦ ዋና ዓላማው በዚህ ሕይወት ውስጥ እየኖሩ የተጎዱ ከችግሩ እንዲላቀቁ ማድረግ፤ የተሀድሶ ማዕከላት ማቋቋም፣ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ምክረ ሃሳቦች ማቅረብ ፤ በሌላ በኩልም በቋንቋ በባህል ፖሊሲዎች ላይ ሥራዎች እንዲሰሩ ትምህርት ሚኒስቴር በወጣት ተማሪዎች ግብረገብ ላይ መሥራት እና ምክለ ሃሳብ መስጠት የሚሉት ናቸው፡፡

የሕግ አገልግሎትን መስጠት ሕጉ እንዲሻሻል ማድረግ ብሎም የጤና ባለሙያዎች በግብረ ሰዶም ጦስ የተጎዱ ወጣቶች የአእምሮ ህክምና እንዲያገኙ ማስቻልና ሥልጠናዎችን መስጠት ከሥራዎቹ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ እድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የገንዘብ እገዛን እንዲያገኙ ፤ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ ሙያዊ ሥልጠናን ወስደው ራሳቸውን የሚለውጡበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይገኝበታል፡፡

በጠቅላላው ማህበሩ ሲቋቋም ጀምሮ ዓላማው የሰብዓዊነት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ነው። ትውልዱ በመደፈርና በግብረ ሰዶም ሳቢያ እንዳይጠፋ የማድረግ ሥራ ነው የሚሰራው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ታሪክ ባህል እሴቶች መጠበቅ አለባቸው። በማለትም ሰው ላይ፤ ትውልድ ላይ፤ አገር ላይ እየሠራ ያለ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ አንጻር ማህበሩ ዓላማውን በምን ያህል ደረጃ አሳክቷልስ ማለት ይቻላል?

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ፦ አዎ እኛ በጦርነት ውስጥ ሆነን ነው የምንሠራው፤ የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖም ሌላው ፈተና ነው፤ ነገር ግን የግብረ ሰዶም ጉዳይ የሚያሳስባቸው ብሎም ትውልዱ እንዳይጠፋ የጸና ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች በሚያደርጉት ድጋፍ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

የሚገርምሽ ነገር እኛ ትውልድን ከግብረሰዶም መዘዝ እናድናለን ብለን ስንሠራ ደስ የማይላቸው በተገላቢጦሽ ሃሳቡን ከተዋችሁት በጀት እንመድብላችሁ የሚሉ አካላት ብዙ ናቸው፡፡ እኛ ደግሞ ይህ ድርጊት በኃይማኖት የተጠላ፣ የተወገዘ፣ በባህል አጸያፊ፣ በታሪክ ተቀባይነት የሌለው፣ በኢትዮጵያ ሕግ አንቀጽ 629 ላይ ወንጀል ተብሎ የተቀመጠና የጤና ጠንቅ የሆነን ተግባር ልንቀበል አይገባም ብለን እየታገልን፤ እየተዋጋን እንገኛለን፡፡ ግብረ ሰዶም ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ነው ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ጋር የማይሄድ ስለሆነ እንዋጋዋለን ብለን እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ከኢትዮጵያውያን ባህልና ኃይማኖት አንጻር ግብረ ሰዶም ያለበትን ደረጃ እንዴት ይገልጹታል?

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ፦ አሁናዊ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አደገኛና ጨካኝ ግብረሰዶማዊነት እየተስፋፋ ነው፡፡ ሆስፒታል ውስጥ  ጾታ አንሞላም እስከማለት የተደረሰበት ሁኔታ እያጋጠመ ነው፤ ልጁ ከትምህርት ቤት እቤቱ ተመልሶ እማዬ ” እኔ ወንድ ነኝ ሴት? ወደፊትስ ሴት መሆን አልችልም ?” ብሎ እስከመጠየቅ ተደርሷል፡፡ ወንዶች የሴቶች ቀሚስ ለብሰው ቦርሳ ይዘው ፋሽን እያሳዩ ነው፡፡ አንተ አንቺ አትበሉ ተብሎ በተለያዩ ቦታዎች ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሲጠቃለል እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳችንን ያመላክታል፡፡ እኛም በግልም በማህበርም ያለፉትን 15 ዓመታት ስንጮህ የነበረው ይህ እንዳይሆን ነበር፡፡

እኛ ትውልድን ከግብረ ሰዶም እንታደግ ብለን ስንነሳ ዝም ብለን አልነበረም፡፡ የተለያዩ ማሳያዎችን ጭምር ይዘን ወደ ኃይማኖት አባቶችና ወደ መንግሥት ተጉዘናል። ለምሳሌ በ 2003 ዓ.ም እጁን ሲመታ 666 የሚያወጣ ሰው እንዴት አድርጎ ግብረ ሰዶምን እያስፋፋ እንደሆነ በአንደበቱ ተናግሮ እኔም በቪዲዮ ቀርጬ የኃይማኖት አባቶችም መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት ስጡት ብዬ ነበር፡፡ ከዛም በኋላ 2005 ዓ.ም በመሠረቱት ቡድን ውስጥ በመግባት ወንዶች ቀሚስ ለብሰው ጡት መያዣ አድርገው እንዴት እንደሚሆኑ አሳይተናል። ከ 8 እስከ 32 ዓመት በዛ ሕይወት ውስጥ የቆዩት ወጣቶች ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ በማለት ግብረ ሰዶማዊነት ምን ያህል አስከፊ ሕይወት እንደሆነ እንዲናገሩ ሰርተናል። በወቅቱ የሰማም የሆነ ትኩረት የሰጠ አካል ባለመኖሩ ዛሬ ላይ ብሶ ተባብሶ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊከተን ተዘጋጅቷል፡፡

ይህ ሁሉ ነገር ሲጠቃለል የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን ከባህል ከኃይማኖታችን አፈንግጠን መውጣታችንን ነው። ሁላችንም እንደምንገነዘበው አሁን በየቦታው ሺሻ፣ ጭፈራ ቤት ፤ የራቁት ጭፈራ ድርጊት፤ ስካር ፤ ገንዘብ መውደድ በጣም በዝቶ ተንሰራፍቷል ፡፡ ግብረሰዶም ደግሞ እነዚህ ሁኔታዎች በጣም ይመቹታል፡፡ በመሆኑም እግር በእግር እየተከተለ ልጆቻችንን ብሎም ትውልዱን ሊያጠፋ እየተስፋፋ ነው፡፡

ግብረ ሰዶም የእግዚአብሔርን ሃሳብ በመጻረር ትውልድ እንዳይቀጥል የሚያደርግ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም አዳም ቢያስፈልገው ኖሮ ያደርገው ነበር፤ ነገር ግን ሄዋን ስለሆነች የምታስፈልገው ያደረገውም እንደዛ ነው፡፡ ኖህም ወደመርከቡ ሲያስጋባ እንስሳትን ወንድና ሴት አድርጎ ነው። እጽዋትን ብናይ ሴቴና ወንዴ ናቸው። ኤሌክትሪክም ኔጋቲቭና ፖዘቲዝ ነው። ከተፈጥሮ ጋር የተቃረነ ሥራ እየተሰራ እያየን ግን መሪዎች፤ የኃይማኖት አባቶች ፤ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተቃውሞን ካላሰሙ ትውልድ ማለቁ ነው፡፡

በመሆኑም 98 በመቶ በላይ ኃይማኖተኛ የሆኑ ሕዝቦች የሚኖሩባት ባህልና ወግ ያላት አገር እስልምናውም ክርስትናውም በእግዚአብሔር ተፈጥረናል ከሞትን በኋላ ደግሞ ገነት ወይም ጀነት እንገባለን ብሎ በሚያምንበት ሀገር ላይ እንደዚህ አይነት ሥራ ነግሶና ተንሰራፍቶ ማየት የማንም ችግር ሳይሆን የራሳችን እንዝላልነት ያመጣው በመሆኑ ሁላችንም ወደምንጫችን፤ ወደቀደመው ማንነታችን መመለስ ይገባናል፡፡

በእኛ ባህልና ወግ ባልና ሚስት እንኳን በሰው ፊት አትሳምም፡፡ ነገር ግን ድህነታችንን ተጠቅመው የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች እየመጡ ቆሻሻ ተግባራቸውን ሲፈጽሙብን ዝም ልንል አይገባም። አካታች የሥነወሲብ ትምህርት(comprehensive sexual education)፣ በሚል በትምህርት ደረጃ ሲሰጥ እንዴት ዝም እንላለን። ዩኒስኮ የራሱን ህልም ለማሳካት ነው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያፈሰሰው። ይህንንም የዛሬ 4 ዓመት አጋልጫለሁ። በ7ኛ ክፍል መጻህፍት ላይ የሚወጡት ነገሮች ይህንን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡

አሁን እኮ በአገራችን ወይዘሮም፤ ወይዘሪትም መባል አንፈልግም የሚሉ ሴቶች እየተስተዋሉ ነው፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው? ማዕረግ የለኝም የሚል ሰው ሌላ ችግር አለበት ማለት ነውና ትኩረት ያሻል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ግብረሰዶማውያን ተግባራቸውን ለማስፋፋት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ምን ምን ናቸው? ለምሳሌ ከአለባበስ፣ ከቀለም፣ እንዲሁም ከሌሎች ተያያዥ ነገሮች ተግባራቸውን ለማስፋፋት የሚጠቀሟቸው መልዕክት ማስተላለፊያዎች ምን ይመስላሉ?

ሊቀ ትጉኃን መምህር ደረጀ፦ ይህንን ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ጀምሮ ተናግሬያለሁ፤ ለምሳሌ ነጭ ቀበቶን አዘውትሮ ማድረግ፣ ጫማ ያለካልሲ ማድረግ፣ ባላቶሊ(የጸጉር ቁርጥ) መቆረጥ፣ አፍንጫና ጆሮ ላይ በዛ ያሉ ጌጣጌጦችን ማድረግ፣ እምብርት ላይ ሎቲዎችን ማድረግ ፣ ጥብቅ ያለ ሱሪ ማድረግ፣ ሱሪን ዝቅ አድርጎ መታጠቅ መገለጫዎቻቸው ሲሆኑ ስማቸውም “ዜጋ ” ነው፡፡

በነገራችን ላይ ሀብታሞቹ “ላባ” ደሃዎቹ ደግሞ “ቻይና” ይባላሉ ፤” ቶፕና ቦተም” በማለትም አድራጊና ተደራጊውን ይለዩበታል፡፡” ባይ ሴክሽዋል” አሉ፤ እነሱ ደግሞ ወንድም ሴትም ጋር የሚሄዱ ናቸው፡፡

በጠቅላላው ግን መንግሥት ግብረ ሰዶምን የማጥፋት ቁርጠኛ አቋም ላይ ከደረሰ ሳምንት አይፈጅበትም። የት ቦታ እንደሚጨፈር፤ የት ምን እንደሚደረግ ሁሉም ይታወቃል፡፡ እንደ ዩጋንዳና ሩሲያ መሪዎች ጠንካራ አቋም መያዝ ከተቻለ ችግሩን በቀላሉ ማስወገድ ይቻላል። ለእኔ ቸልተኝነት ነው ትውልዱ በዚህን ያህል ደረጃ ግብረሰዶም ውስጥ እንዲገባ ያደረገው፡፡

ከላይ እንዳልኩት እኛ የራሳችን አኩሪ ባህል ያለን፤ ነውር የሚባለውን የምንፈራ ነበርን፡፡ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ግን አሳፋሪም ፤አንገት አስደፊም ፤ከፍ ሲል ደግሞ ነገ ትውልዱን እስከወዲያኛው የሚያሳጣ ነው፡፡

እኛ እኮ የራሳችንን ባህላዊም ሆነ በዓላዊ ኩነቶቻችንን ከማክበርና ከመዘከር ይልቅ የውጪዎቹ በራሳቸው ምክንያት ስለሚያከብሯቸው ቫላንታይን ዴይና ሌሎች ቀኖች የምንጨነቅ ሆነናል፡፡ 37 ዓመት አገር የመራች ንግስተ ሳባ እያለችን ማርች 8 ብለን በጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ አመጽ ያስነሱትን ሴቶች የምንዘክር ነን። የራሳችን አኩሪ ባህሎቻችንንና ታሪካችን እነሱ ላይ መጫን አቅቶን ልጆቻችን የቀለም ቀን እያሉ ቀለም ሲራጩ እንዲውሉ የፈረድን ዓድዋና ሌሎች የድል ቀኖቻችንን የዘነጋን ሆነናል፡፡ ስለዚህ የውጪውን እያመጣን የራሳችንን ልብስ እያወለቅን መሆኑን ተረድተን ወደቀድሞ ማንነታችን በሚመልሱን ተግባራት ላይ አተኩረን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ መምህር እርስዎ ወደቀደመ ማንነታችን መመለስ ከችግሩ ሁሉ መውጫ ቁልፍ ነው እያሉኝ ነውና፤ ወደ ቀድሞ ማንነታችን እንዴት እንመለስ?

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ ፦ “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን መለወጥ አይቻለውም”፤ ከእኛ የሚጠበቀው ወደ እግዚአብሔር መመለስ ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሀገሪቱ የምትገዛባቸው ሕጎች ሁሉ ሲወጡ ከኃይማኖት፤ ከእሴት ፤ ከትውፊት አንጻር ታይተውና ተገምግመው ሲሆን ሀገራችን ደግሞ ኃይማኖት፣ ወግና ባህል ያላት ኪነ ስዕልና ጥበብ የተገለጸላት ከሁሉም በላይ ደግሞ ቀደምት የሆነች ናት። ከዚህ አንጻር ወደማንነቷ መመለስ ይገባታል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ሰው ላይ መሥራት ሲቻል ብቻ ነው። ምክንያቱም የተሰራ አእምሮ የፈረሰን ይገነባል፤ የፈረሰ አእምሮ ደግሞ የተሰራን ያፈርሳልና፡፡

አዲስ ዘመን፦ ግብረ ሰዶም ስር ሰዶ የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ሊወሰድ የሚገባው ጥንቃቄና ርምጃ እንዴት ይገለጻል?

ሊቀ ትጉሃን መመህር ደረጀ፦ ሁላችንም እንደ አንድ ሆነን መጮህ ነው አማራጩ፡፡ እኔ የዛሬ 15 ዓመት የጀመርኩት ጩኸት ወደማህበረ ወይንዬ መጣ፤ ከዛም ወደተቋም አደገ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ብቻዬን ለ 15 ዓመታት ስጮህ ዝም ብሎ የነበረ ሁሉ ችግሩ አጠገቡ ሲደርስና ቤቱን ሲያንኳኳ ድምጽ ማሰማት ጀመረ ፡፡ ይህ ጥሩና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡

አንድ ሰው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ብዙዎችን የመለወጥ ሃይል አለው፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው ፤እሱ “ህልም አለኝ ብሎ” ተነሳ የእሱ ህልም ኦባማን 44ኛ ጥቁር የአሜሪካን ፕሬዚዳንት አደረገው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በአንድ ድምጽ መጮህ ትኩረት አስክናገኝ ድረስ መታገል አለብን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ችግሩን ፍርጥርጥ አድርጎ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለ ግብረሰዶም ማውራት ተግባሩን ማስፋፋት ነው የሚል ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡ እንግሊዝ አገር ግብረሰዶማውያን ይገደሉ ነበር፤ ይህንን ለመሸሽ ሚዲያው እንዳይናገር አደረጉት። እነሱ ግን ውስጥ ወስጡን እየሄዱ ባለሥልጣናቱን ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችንም መያዝ ጀመሩ፡፡ በዚህም ሕጋዊ ለማድረግ ቻሉ፤ ኢትዮጵያ ላይም የገበያ ቦታውን ፣ ባለሀብቱን፣ ታዋቂ ሰዎችን ፣ ባለሥልጣናቱን ከያዙ በኋላ ምን ታመጣላችሁ ሊሉን ነው፡፡ ግብረ ሰዶም በኢትዮጵያ በ 2003 ዓ.ም 13 ሺ የነበረ ሲሆን ፣ ቀጥሎ 30 ሺ ደረሰ የዛሬ 4 ዓመት መቶ ሺ ደርሷል፤ ለዚህ አሃዝ መጨመር ዋናው ምክንያት ዝም ማለታችን እነሱ ደግሞ ሥራቸውን በአግባቡ መሥራታቸው ነው፡፡

ይህ ሆኖም የግብረሰዶምን አስከፊነት ተገንዝበን ወጥተናል ያሉትንም የምንደግፍበት ሁኔታ የለም። ስምንት ጊዜ የወንድ ሚስት ሆኖ ያገባው “አጠለል” ትውልድ ይዳን በእኔ ይብቃ ብሎ አደባባይ ሲወጣ ማንም ድጋፍ ያደረገለት አልነበረም ፤ ብዙ ስቃይና እንግልት ደርሶበት እሱም ሲብስበት ሰው ደብድቦ እስር ቤት ገብቶ ነው የሞተው፡፡ በመሆኑም ሰዎች ከዚህ ጉዳይ ወጥተው ዋጋ ከፍለው አርዓያ ሲሆኑ መርዳት ብንችል፤ ከግብረሰዶም እሳት ወጥቶ ፤ ትዳር መሰርቶ ፤መውለድ እንደሚቻል ብናሳያቸው ይበረታታሉ ሌሎችም እንዲወጡ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

አዲስ ዘመን ፦ እነዚህ ወገኖች ተግባራቸውን ለማስፋፋት ድጋፍ የሚያገኙት ከየት ነው?

ሊቀ ትጉሃን መምህር ደረጀ፦ ትልቁ ድጋፍ የሚገኘው” ከዓለም አቀፉ ሌዝቢያንና ጌዎች ማህበር” (international lesbians and gay association) ሲሆን ሌሎች ዓለምአቀፍ የርዳታ ድርጅቶችና ተቋማት ድጋፍ አድራጊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ በድህነታችን ምክንያት የተለያዩ ርዳታዎችን እንሰጣችኋለን ብለው በሀገራችንም ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸው ያሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ልናውቅና ልንገነዘብ የሚገባን ድርጅቶቹ ርዳታ የሚሰጡን የእውነት የእኛ ችግር ጉስቁልና አሳስቧቸው ሳይሆን ጥቅማቸውን ፈልገው ነው፡፡ ገሚሶቹ ወርቃችንን፤ ነዳጃችንን፤ መሬታችንን ፈልገው ሌሎቹ ደግሞ ግብረሰዶምን ሊያስፋፉ መሆኑን ማወቅ ግዴታ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ግብረሰዶማውያኑ ትኩረት የሚያደርጉባቸው የትኞቹን የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው?

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ደናግላን ወንዶች አሉ በማለት የወሲብ ቱሪዝምን ማስፋፋት ዓላማቸው ነበር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ከሰባት እስከ 14 ዓመት ያሉ ታዳጊዎችን ወደ ድርጊቱ ማስገባት ጀመሩ፤ አሁን ግን ከአንድ ዓመት ሕጻን ጀምሮ ወርደዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገራችን ላይ እየተከናወነ ያለው ግብረሰዶማዊነት ጨካኝና ዘግናኝ ያደርገዋል፡፡

ሌላው ግብረሰዶምን ያስፋፋው ነገር ወላጆች ታዳጊ ልጆቻችው ግብርሰዶማዊ ሲሆኑባቸው ወጥቶ ከማናገርና በጋራ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ልጁን የመደበቅ አካባቢ የመቀየር ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ በግብረሰዶም ጥቃት ውስጥ የወደቁ ታዳጊዎችን እንዴት መለየት ይቻላል?

ሊቀትጉሃን መመህር ደረጀ፦እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የተፈጸመባቸው ታዳጊዎች ትምህርት ይጠላሉ፣ ምግብ አይመገቡም፣ እንቅልፍ አይተኙም፣ ጭንቀትና ድብርት ራስን የማጥፋት ሙከራ ውስጥ ይገባሉ። ይህን ካለፉ ደግሞ በቀለኛ በመሆን እነሱም ሲያድጉ የተፈጸመባቸውን ሌሎች ላይ ለመፈጸም ይሄዳሉ፡፡

አዲስ ዘመን፦ በግብረሰዶማውያኑ ተመራጭ የሆኑ አካባቢዎችስ የትኞቹ ናቸው?

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ፦ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣ አርባምንጭ፣ ጎንደር ሲሆኑ በከተማ ውስጥ ፒያሳ (አራዳ ህንጻ )፣ ቦሌ ፍል ውሃ ፣ ወሰን በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ገስት ሀውሶችና በትልልቅ ሆቴሎች ላይ መገኘት ጀምረዋል። በተለይም በአንድ የጋራ መኖሪያ ቤት እስከ 20 የሚደርሱ ግብረሰዶማውያን ተይዘዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች አከራይና ተከራይ አይተዋወቁም፤ ገንዘብ ብቻ ነው የሚለዋወጡት ፤ ነዋሪውም ጎረቤቱ ማን እንደሆነ አያውቅም ፤ ይህ ደግሞ ለእነሱ መስፋፋት ትልቅ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኮሚቴዎች በግቢያቸው ውስጥ ስላለው ሰው መጨነቅና ማን ምን እንደሆነ ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ትምህርት ቤት መምህራንና ወላጆች የጋራ ግንኙነት በማድረግ ስለ ልጆቻቸው በግልጽነት መወያየትም አለባቸው። በሌላ በኩልም ሁሉም ቤተ እምነቶች ግብረሰዶም በጣም አጸያፊ መሆኑን ሊያስተምሩ ተከታዮቻቸውን ሊያነቁ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያ ሕግ ተግባሩን ምን ያህል ይኮንነዋል?

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ፦ አንቀጽ 629 ከአንድ ዓመት እስከ 32 ዓመት ወይም እድሜ ልክ አስራት ይላል ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ግብረሰዶም ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ነው ይላል፤ ነገር ግን ሰው ብቻውን ሆኖ ግብረሰዶም መሆን ይችላል። በኢትዮጵያ ሕግ ጾታ ቅየራ ወንጀል ነው ብሎ አይልም። ስለዚህ ውጪ አገር ጾታቸውን ቀይሮ የመጣ ሰው ግብረሰዶምን ፈጸመ ብለን ልንከሰው የምንችልበት የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡

በመሆኑም ሕጉ በራሱ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ሕጉ ነባራዊ ሁኔታን ተንተርሶ የሚሻሻልበትን ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡፡ እስከሚሻሻል ደግሞ ባለው ሕግ የመቅጣቱ ሁኔታ መጀመር ይገባዋል። በጠቅላላው ግን ትውልዱን እየጨረሰ ያለውን ግብረሰዶም እዚህ እንዲደርስ ያደረገው ሕጉ ጠበቅ ያለ አለመሆኑ ሳይሆን ያለውም በአግባቡ ተግባራዊ አለመደረጉ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ አሁን አንዳንድ ርምጃዎችም እየተወሰዱ እንዳሉ እንሰማለንና እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ፦ ንግድ ባንክ ህንጻ ላይ ይከፈታል የተባለው ሬስቶራንት በሕዝቡ መካከል ጥያቄ ስለፈጠረና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች መንቀሳቀስ ስለጀመሩ፣ ጾታ አንሞላም የተባለበት ሆስፒታል ፣ ፋሽን ለማሳየት ወንዶች ቀሚስ ለበሱ የሚለው ጩኸት ስለበዛ ያንን ለማረጋጋት ሥራው ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ሥራ በዚሁ ቀጥሎ በተከታታይ ቢሠራ ችግሩን በቁጥጥር ሥር ለማዋል አንድ ሳምንት በቂ ነው፡፡ በትክክልም ሥራው እንዲሰራ ከተፈለገ ማህበራችን በሩ ክፍት ነው፡፡

እንደ ማህበር እኛ የምንለው ትውልድን ከግብረሰዶማውያን እንታደግ እንጂ የችግሩ ሰለባዎች ይገደሉ ፤ ይዋረዱ የሚል አቋም የለንም፡፡ በመሆኑም ትውልዱን ከማዳን አንጻር መንግሥታዊ ተቋማት አብረውን ቢሰሩ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ለእነሱም ቢሆን ተደጋጋሚ ጥሪዎችን እያቀረብን ነው፡፡ ‹‹ከሞት መንገድ አምልጡ፤ ሰው ሁኑ፤ ሰው መሆንም ትችላላችሁ›› ብለን ጥሪ አቅርበናል ፡፡ ከመጡም ደግሞ በፍቅር ተቀብለን አስተምረን ትክክለኛውን ጎዳና አሳይተን መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ እናደርጋቸዋለን።

በነገራችን ላይ 35 ዓመት በግብረሰዶማዊነት የቆየ ሰው በማህበሩ አማካይነት ከችግሩ እንዲወጣ ሆኗል። ትምህርት ቤቶች የኃይማኖት ተቋማት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በቅንጀት መሥራት ከቻሉ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ እንደ ሀገር ችግሩን ለመከላከል ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ፦ አንዱ የቤተሰብ ትምህርት ቤት ማለትም እናት አባት ልጆች በጋራ የሚበሉበት፣ የሚጸልዩበት ልጆች ለወላጆቻቸው ታዛዥ የሚሆኑበት ፤ አዋቂ ሲመጣ ብድግ ብለው የሚቀበሉበት፤ ሁለተኛው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት ሲሆን በዚህ ውስጥ ደግሞ የቀድሞው የእርስ በእርስ ግንኙነታችንና አብሮነታችን እኔ ለጎረቤቴ፤ ጎረቤቴ ለእኔ ልጆች ያለው ጥበቃና ሃላፊነት በጠቅላላው የእሱ የእኔ የሚለው ነገር የሌለውና እኛነት የሚዳብርበት መንገድ፡፡ ሶስተኛው የኃይማኖት ትምህርት ሲሆን ልጆች በዚህ ውስጥ አልፈው ሥነምግባር ግብረገብ ተምረው እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ አራተኛውና የመጨረሻው መደበኛው (የቀለም )ትምህርት ቤት ሲሆን በዚህም የሚያግባቡንን ታሪኮች በማስተማር መምህራን ለሚያፈሩት ትውልድ አርዓያ ሆኖ ለመገኘት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህ ያጣናቸው አራት መፍትሄዎች የቸግሮቻችን መውጫ ቁልፍ መንገዶችም ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን ፦ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ግፊት ያለበት ከመሆኑ አንጻር አንዳንድ የውጭ ተቋማት ጫናን እንዴት መመከት ይቻላል ብለው ያስባሉ?

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ ፦ መጀመሪያ በርዳታ አይደለም መኖርን ማሰብ ያለብን፡፡ በቀደመው ጊዜ እኮ እነሱ ረጂዎቹ ሳይኖሩም መኖር የቻልን ሰዎች ነን። በመሆኑም በርዳታ እንኖራለን የሚለውን አስተሳሰብ ማጥፋት ያስፈልጋል፤ ዩጋንዳ እኮ ደሃ ሀገር ናት ግን ደግሞ ግብረሰዶምን ከመቃወም አልፋ ሕግም አውጥታለች፤ እነ ፑቲን የኃያላኑ ጫና ስለሌለባቸው አይደለም በገሃድ እየተቃወሙ ያሉት በመሆኑም ርዳታ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ሊቀትጉሃን መምህር ደረጀ፦ እኔም አመሰግ ናለሁ፡፡

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 20/2015

Recommended For You