በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እጅግ ፈታኝና አጓጊ ከሆኑት ፉክክሮች መካከል አንዱ የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር ነው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንቱ ሰባስቲያን ኮ ሳይቀሩ የውድድሩን ጥንካሬ ‹‹ጥራት›› የሚለውን ቃል ሶስት ጊዜ በመደጋገም ነበር የገለጹት፡፡ ይህ የሆነበት ምክንት ደግሞ ከ10 የምንጊዜ የርቀቱ ፈጣን አትሌቶች 6ቱን ጨምሮ የዓለም ቻምፒዮን እንዲሁም የርቀቱን የክብረወሰን ባለቤት ለአሸናፊነት የሚፋለሙበት መሆኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና የኔዘርላንድስ አትሌቶች በርቀቱ የሚያደርጉት ፉክክር የስፖርት ቤተሰቡ ሊመለከት የሚጓጓለት ውድድር ነው፡፡ በዚሁ ቻምፒዮና ላይ በሌሎች ርቀቶች ሜዳሊያ ያጠለቁ አትሌቶች ለተጨማሪ ክብር መፋለማቸውና በዓመቱ ድንቅ ብቃት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ደግሞ ነገ ምሽት ለሚካሄደው ውድድር ልዩ መልክ ሰጥቶታል፡፡ እአአ ከ2003 አንስቶ የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች በመፈራረቅ ድል የሚያስመዘግቡበት ይህ ውድድር ዘንድሮም የበላይነቱ በእነዚሁ ሀገራት አትሌቶች እንደሚያዝ ይጠበቃል፡፡
የዓምናዋ የርቀቱ ቻምፒዮን እንዲሁም በቡዳፔስት በ10ሺ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ ያስመዘገበችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በዚህ ውድድር አሸናፊ ትሆናለች ተብላ ትልቅ ግምት አግኝታለች፡፡ አስደናቂ ዓመት እያሳለፈች ያለችው ጉዳፍ በቻምፒዮናው ቀጥታ ተሰላፊ ብትሆንም፤ በለንደን ዳይመንድ ሊግ ያስመዘገበችው 14:12.29 የሆነ ሰዓትም ፈጣን ሊባል የሚችል ነው፡፡ ጉዳፍ ካለችበት የብቃት ጥግ አንጻር በጠንካራ ሥነልቦናና ልበ ሙሉነት በውድድሩ እንደምትሳተፍና ለአሸናፊነትም እንደምትሮጥ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል ከአትሌቷ ጋር የሚሰለፉት አትሌቶች ማለትም በቡድን ሥራ የምትታወቀው እጅጋየሁ ታዬ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ እንዲሁም መዲና ኢሳም ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊዎችን ለማስመዝገብ እንደሚተጉ ተገምተዋል፡፡
በቅርቡ የ5ሺ ሜትር ርቀትን 14:05.20 በሆነ ሰዓት በመግባት የዓለም ክብረወሰንን መስበር የቻለችው ኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕየጎን በምትታወቅበት 1 ሺ500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ነው፡፡ አስደናቂ ዓመት እያሳለፈች ያለችው አትሌቷ በዚህ ርቀትም የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ ሀገሯን ወክላ የምትሮጥ ይሆናል፡፡ በሳምንታት ልዩነት በ3 ርቀቶች ክብረወሰኖችን መስበሯ ስለ ጠንካራ ተፎካካሪነቷ ምስክር ሲሆን፤ በቻምፒዮናው አዲስ ታሪክ ለማጻፍ ጥረት ማድረጓ የማይቀር ነው። የሀገሯ ልጅና ኦሪጎን ላይ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያውን ያጠለቀችው ባትሪስ ቼቤትም በውድድሩ ጠንካራ የአሸናፊነት ፍልሚያ ከሚያደርጉት መካከል ትጠቀሳለች፡፡
የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በሶስት ርቀቶች ተካፍላ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ ለስፖርት ቤተሰቡ ተዓምር የሆነችው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሃሰንም በዚህ ውድድር ተሳታፊ ናት። ማራቶንን ከሮጠች በኋላ ዘንድሮ በድጋሚ ወደ መም የተመለሰችው ሲፈን በ10ሺ ሜትር መጨረሻ ላይ ወድቃ ሜዳሊያ ባታጠልቅም፤ በ 1 ሺ500 ሜትር ግን ብርቱ ጥረት በማድረግ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። እንዳሰበችውና ከሁለት ዓመት በፊት ባሳየችው አቋም ላይ አለመሆኗ እየታየ ያለው ሲፈን ሶስተኛውን ውድድር በ5 ሺ ሜትር ለማድረግ በማጣሪያው አረጋግጣለች። ይሁንና የቻምፒዮናውን ብቸኛ የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ እንዲሁም በ10 ሺ ሜትር በተካሄደው ትንቅንቅ የትከሻ ለትከሻ ትግል በማድረግ የወርቅ ሜዳሊያውን ከነጠቀቻት አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ጋር ብርቱ ፉክክር ማድረጓ እንደማይቀር ተገምቷል፡፡
በወንዶች 5ሺ ሜትርም የአሸናፊነት ግምቱ ለኢትዮጵያ ያደላ ሆኗል፤ የአምናው ቻምፒዮን ኖርዌያዊው ጃኮብ ኢንብሪትሰን በዚህ ውድድር አለመካፈሉ ደግሞ ለዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ በርቀቱ እንደሚካፈል የተገለጸው አትሌት በሪሁ አረጋዊ በተለይ የአሸናፊነት ግምቱን ያገኘ አትሌት ነው፡፡ በአንጻሩ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሽዋ ቼፕቴጊ ተሳታፊ መሆኑ ውድድሩን ማክበዱ አልቀረም፡፡ ይሁንና ሁለቱ አትሌቶች በዚህ ርቀት በሉዛን ዳይመንድ ሊግ ተገናኝተው በበሪሁ ከአንድ ሰከንድ በበለጠ የበላይነት መጠናቀቁ የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱ ወደ እሱ እንዲያደላ አድርጓል፡፡ እጅግ ስኬታማ ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው በሪሁ በ10ሺ ሜትር ሜዳሊያው ባይሳካለትም በዚህ ርቀት ባንዲራውን ለማውለብለብ የሞት ሽረት ትግል የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015