ወጣት ሳሚያ አብዱልቃድር ትባላለች። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአፕላይድ ኬሚስትሪ ሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ በቢዝነስ አስተዳደር ይዛለች፤ ከዚህ በተጨማሪ በሕይወት ክህሎት እና በሥራ ፈጠራ ላይ የሚያተኩሩ የተለያዩ አጫጭር ኮርሶችን ተከታትላለች።
ጠንካራ፣ ብርቱ እና ባለራዕይ፣ ወጣት ኢትዮጵያዊት ሥራ ፈጣሪ ናት። ወጣት ሳሚያ ለወጣት ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን በዲፕሎማትነት እሴትን ለመጨመር ብሎም የሥራ ፈጠራን ሥነ-ምህዳሩን ለማስፋት እና ወጣቶችን ለማበረታታት በተለያዩ መንገዶች ልምዷን ታካፍላለች፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ነው ያለው የምትለው ወጣት ሳሚያ፤ ይህም ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች መልካም እድል እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የካፒታል እጦት፤ የተገደበ የንግድ መረብ እና የንግድ ትምህርት እጦትና መሰል እንቅፋቶች ስለሚያጋጥሟቸው እነዚህን ተግዳሮቶች አለፈው ውጤታማ ለመሆን እንደሚቸገሩ ትገልጻለች።
ወጣት ሳሚያ እንደምትናገረው፤ በዋናነት ትኩረት ሰጥታ የምትሰራው በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በቢዝነስ ልማትና በፈጠራ ሥራዎች ላይ በማተኮር ነው። ለዚህም አጋዥ እንዲሆን እ.ኤ.አ. በ2019 እያንዳንዱ ተማሪ ለስኬት መብቃት እንዲችል የት/ቤት ሥርዓቶችን በማሻሻል አቅማቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ አካባቢ ለመፍጠር የAim View General Educational Consultancy አቋቁማለች።
በተጨማሪም በትምህርት ዘርፍ Minimum Learning Competency Ethiopia (MLCE) የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅትም መስርታለች። ድርጅቱ ራዕያቸውን እውን ማድረግ የሚችሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በSTEM ማለትም (በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሂሳብ እና ኢንጂነሪንግ) ትምህርት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ለመደገፍ ከሚመለከታቸው አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ ተማሪዎችን የመደገፍ ሥራ የምትሰራ እንደሆነ ትናግራለች። በተጨማሪም ወጣት ሳሚያ የአርክ-አፍሪካ የኢንቨስትመንት አማካሪ እና የንግድ ልማት ኩባንያ ተባባሪ መሥራች እና የማኔጅመንት አጋር ስለመሆኗ ታስረዳለች።
”እራሴን ሥራ ፈጣሪ ነኝ ብዬ ነው የሚወስደው” የምትለው ወጣት ሳሚያ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የራሷን ድርጅት ለመቋቋም ጥረት በምታደርግበት ወቅት አራት የሚሆኑ ጉዳዮች አስቸጋሪ ሆነውባት እንደነበር ትናገራለች። እነዚህ የክህሎት ክፍተት፣ መረጃ የማግኘት ችግር፣ ከሰዎች ጋር ኔትዎርክ መፍጠር አለመቻሏ እና ራዕዩን እውን ለማድረግ የፋይናንስ አቅርቦት እጦት ነበሩ።
እነዚህን ተግዳሮቶች ወደ መፍትሔ ለመለወጥ በማሰብ እና ሥራ ፈጣሪ ደግሞ በባህርዩ ፈተናዎችን ወደ ዕድል የመለወጥ አቅም ያለው በመሆኑ፤ ችግሮችን ወደ መፍትሔ ቀይሮ ለራሱም ለሀገሩም የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንዳለባት ታስባለች፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግም በግሏ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት ባለመቻሏ ለሥራዋ አጋዥ የሚሆን ምቹ የሆነ ሥነ ምህዳር ባለመኖሩ እርሷ ከተገፈጠችው ፈተና በመነሳትና ተነሳሽነቱን በመውሰድ ለእንደ እሷ አይነት ይህንን ተግዳሮት እየተጋፈጡ ላሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለመድረስ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር መቋቋም ችላለች። ማህበሩም የወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ፍላጎቶች ለመረዳት፣ ለማብቃት፣ ለመደገፍ እና ለማስተዋወቅ የሚሰራ ማህበር ነው።
ስለማህበሩ አመሰራረት ወጣት ሳሚያ ስትናገር፤ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማህበራት እንዳሉት ወጣቶችን ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲያመሩ የሚያበረታታ ማህበር ለማቋቋም ፍላጎት ያድርባታል፡፡ ይህንኑ ወደ ተግባር ለመለወጥም ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመሄድ ማህበሩን ለመመስረት እንደበቃች ትናገራለች።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት የሆነችው ወጣት ሳሚያ፤ እንደ ማህበር አምስት የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ነው ወደ መፍትሔነት የቀያርነው ትላለች፤ የመጀመሪያ በኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ትምህርት ኮርስ አንድ ብቻ ነው ያለው እርሱም በዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የሚሰጥ ነው። ከዛ ውጭ የሥራ ፈጠራን ለመበረታታት የሚሆን ምቹ ሁኔታ የለም፤ ይህ ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር የሚያያዝ ነው። በዚህ መነሻ ወጣቶች ያላቸውን ክህሎት መውጣት እንዲችሉ በማሰብ ሀሳብ ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ቀጥታ ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ የመደገፍ ሥራ እንደምትሰራ ትገልፃለች።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የቢዝነስ ሥራ በተለይም አዲስ የፈጠራ ሥራ ያለ መረጃ መሥራት ከባድ በመሆኑ ለወጣቶች ጠቃሚ፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ታግዛለች፡፡ ሌላው ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እራሳቸውን ወይም የያዙትን ሃሳብ ወደ ገበያው ለማውጣት ስለሚቸገሩ በእነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ትንቀሳቀሳለች፡፡ በሌላ በኩል ለሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ ወይም ታደርጋለች፤ የማማከር ሥራዎችንም ታከናውናለች፡፡
የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ሥራ ፈጣሪዎች፤ ለውጥ ፈላጊዎች፣ የፈጠራ እና መሠረታዊ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ እና የንግድ ድርጅቶችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመር፣ ለማስተዳደር እና ለማሳደግ ፍላጎት ያላቸው ዕድሜያቸውም ከ18-35 ዓመት ላይ ያሉ ወጣቶች የተካተቱበት መሆኑን ወጣት ሳሚያ ታስረዳለች፡፡ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበርም አጽንኦት የሚሰጠው በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ላይ እና በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉት ነው ትላለች።
ከዚህ ሌላ የተቸገሩ ወይም የተገለሉ ወጣቶች ሕይወት ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ቆርጠን ተነስተናል የምትለው ወጣቷ፣ ስለዚህ የሙያ ማጎልበቻ ሴሚናር፣ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን፣ የመማክርት ዕድሎችን እና ወርክሾፖችን በማደራጀት የንግድ ሥራ ክህሎት እና እውቀትን ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ለማቅረብ እየሠሩ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በአካባቢያቸው ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ለውጥ ለማምጣት እና ዘላቂ የንግድ ሥራዎችን ለመገንባት ያላቸውን ኃይል አስተባብረው ለውጤት እንዲበቁ ማህበሩ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ከሁሉም አስተዳደርና አካባቢ የተውጣጡ ወጣቶችን በኢትዮጵያ ውስጥ ውጤታማ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማበረ ታታት፣ ለማብቃት እና ለማሳደግ በሙሉ አቅሙ እየሠራ እንደሆነ ተናግራለች።
ሥራ ፈጠራ በትምህርት ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም የምትለው ወጣት ሳሚያ፤ በቀለም ትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን የራስ ሥራ ለመጀመር አያበቃም። ጥንካሬና ራዕይ፣ በራስ መተማመንና ለፈተናዎች ሁሉ የተዘጋጁ መሆን የግድ ነው ትላለች። ሥራ መፍጠር ለየት ያለ አተያይ ይፈልጋል። በትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን ሥራ ፈጣሪ ለመሆን መስፈርት አይደለም የማኅበረሰቡን ችግር በአንክሮ መረዳት እና ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከሌላው ሰው በተለየ መንገድ ነገሮችን ማጤን እንደሚጠይቅ ትናገራለች።
ታዳጊ ሀገር ላይ እንደመኖራችን ስለሥራ ፈጠራ ሲታሰብ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ የምትለው ወጣት ሳሚያ፤ ትላልቅ ነገሮች ሆነው ዛሬ ሁሉም የሚጠቅማቸው የስልክ፣ የቴሌቪዥን የፈጠራ ሥራዎች የሚሰሩት ከትንሽ ነገር በመነሳት ነው እያደጉ የሚመጡት፣ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበርም ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ቴክኖሎጂን መሥራት አድርገው በሚመጡ የፈጠራ ሥራዎች ነው ትላለች።
ወጣት ሳሚያ እንደምትለው አንድ ግለሰብ አዲስ ነገር ይዞ ሲመጣ ከቤተሰቡ ጀምሮ ‹‹አይሳካም›› በሚል ሀሳቡ ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ኢኖቬሽን ደግሞ የሚጨበጥ ነገር ለማሳየት በባህርዩ በጣም ረዥም ሂደትና ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ በቀላሉ አምርቶ በመሸጥ ገንዘብ የሚገኝበት አይደለም፡፡ ልክ እንደ ልጅ ተረግዞ የሚወለድ ብዙ ውጣውረድ ያለው ነገር ነው፤ ብዙ ሰው በቶሎ ገንዘብ ለማግኘት ነው የሚጣደፈው፡፡ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበርም በዚህ ረዥም ሂደት ባለው የሥራ መስክ ለወጣቶች አጋዥ ለመሆን ነው እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው ብላለች።
ከስድስት መቶ በላይ የተመዘገቡ አባላት ያሉትን ማህበር መመስረት የፈለጉበትን ሌላ ምክንያት ስታስረዳም አስፈላጊው ክትትል እና እገዛ ቢደረግላቸው ፋይዳው ለብዙዎች የሚተርፉ የሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ትላለች። “ዓለም አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የበቃቸው በሥራ ፈጣሪዎቿ ነው” የምትለው ወጣት ሳሚያ ሕይወትን የሚያቀሉና የሚያቀላጥፉ ፈጠራዎች ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ተገቢው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ተሞክሮን በመጥቀስ ትናገራለች።
በትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎች የኢትዮጵያን ዕድገት በሚያሳልጡ ዘርፎች ሁሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች በሥራ ፈጠራ እና በሥራ ፈጠራ ሃሳብ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የምትናገረው ወጣቷ፤ ነገር ግን ያላቸውን ርዕይ ወደ ተግባር ለመለወጥ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ታስረዳለች። የሥራ ፈጣሪዎች ወደ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሆነ ወደ ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተበታተነ መልኩ በመሄድ ድጋፍና እገዛ እንደሚጠይቁና ይህ ግን ለተቋማቱም ሆነ ለሥራ ፈጣሪዎቹ አስቸጋሪ በመሆኑ ማህበራቸው መመስረቱ በጋራ በመሆን የሚያስፈልጓቸውን ጉዳዮች ለመጠየቅ እንዲሁም የሥራ ፈጣሪዎችን በተገቢው መልኩ ለማገዝ ይረዳል ትላለች።
ይህ ማኅበር መቋቋሙ የሥራ ፈጣሪዎችን ውጣ ውረድ በግማሽ እንደሚቀንሰው በመግለጽ፣ ከተለያየ የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት እንደሚፈልጉ ትናግራለች። እነዚህ ወጣቶች እንቅፋት በገጠማቸው ቁጥር እነርሱም ሆነ ሀገር ተገቢውን ጥቅምና ግልጋሎት ከማግኘት እንደሚሰናከሉ የምታስረዳው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት ሳሚያ፣ ይህ ማኅበር ሥራ ፈጣሪዎች እርስ በእርሳቸው መደጋገፍ እንዲችሉ በማሰብ የተመሰረተ ነው ብላለች።
ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ትክክለኛ፤ ቀጥተኛ እና ጠቃሚ የሆነ መረጃ በማግኘት ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቅሳ፣ ማህበራቸው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያለውን ክፍተት ለመድፈን እንደሚሰራም ገልጻለች። በተጨማሪም ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች፣ ስለ አዳዲስ ሕጎች፣ የሥራ ፈጠራቸውን የት ይዘው መሄድ እንዳለባቸው፣ ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶችን በሚመለከት ማኅበራቸው እገዛ በማድረግ እና መረጃ በማቅረብ እንደሚሰራ ትናገራለች።
የሥራ ፈጣሪዎችን ከባለሀብቶች፣ ከመንግሥት እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ማስተሳሰር ሌላው ዓላማቸው መሆኑን የምትገልጸው ወጣት ሳሚያ፣ ወጣቶች ያላቸውን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ዋነኛ እንቅፋት ከሆኑት መካከል የፋይናንስ ችግር አንዱ በመሆኑ፤ ለእነዚህ ወጣቶች የገንዘብ ምንጮችን ማፈላለግ እና ማገናኘት ከተመሰረቱባቸው እና ከሚሰሩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነም ገልፃለች።
ማህበሩ በቀጣይ ማሳካት የሚፈልገው ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ነው የምትለው ወጣት ሳሚያ ከሀገሪቱ ሕዝብ 60 ከመቶ የሚሆነው ወጣት እንደመሆኑ ያንን ባማከለ መልኩ ማህበሩ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርታቸውን አቅርበው መሸጥ እንዲችሉ ማድረግ እንደሆነ ትናግራለች።
ይህንኑ የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ለማበረታታትና ለመደገፍ ማህበሩ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ የምትናገረው ወጣት ሳሚያ፤ ለአብነት በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት እንደተፈራረሙ ገልጻ፤ ስምምነቱ ከባንኩ ጋር ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር ለሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነ ተናግራለች።
“ስምምነቱ ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ንግድ በመለወጥ ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል’’ የምትለው ወጣት ሳሚያ፣ በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፈጠራ ባለቤቶች አስፈላጊውን ብድርና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን እንደሚያመቻች ጨምራ ገልጻለች። ሁለቱ ተቋማት በጋራ መሥራታቸው ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ያለባቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመቅረፍና ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ በማድረግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ወጣት ሳሚያ ትናገራለች።
በመጨረሻም ወጣት ሳሚያ ለወጣቱ የሚከተለውን መልዕክት ታስተላልፋለች፡፡ ድሃ ሀገር ላይ ነው ያለነው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይደክሙ፣ ባለመሰልቸት እራሳቸውን አልፎም ሀገራቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከወጣቶቿ ብዙ ስለምትጠብቅ ወጣቶች ተስፋ ባለመቁረጥ ላስቀመጡት ግብ መሳካት ደከመኝ፤ ሰለቸኝ ሳይሉ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015