ኢትዮጵያ የምትጠብቃቸው ተጨማሪ ሜዳሊያዎች

 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ሜዳሊያ ማጥለቅ በስፖርቱ ዓለም ከታላላቅ ስኬቶች መካከል ይጠቀሳል። ለወከሉት ሀገር ኩራት ከመሆን ባለፈም ለአትሌቱ እንደሚወዳደርበት የስፖርት ዓይነት ደረጃውን ለማሻሻልም ወሳኝ ነው። በርካቶች ለረጅም ጊዜ በጠንካራ ዝግጅት መትጋታቸው እንዲሁም ለዝግጅቱ ሲሉ ከሌሎች ውድድሮች ራሳቸውን የማቀርባቸው ምክንያትም ይኸው ነው።

ዛሬ 6ኛ ቀኑን ባስቆጠረው የቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 147 ሜዳሊያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ግማሽ የሚሆኑት ባለቤቶቻቸው ታውቀዋል። በቻምፒዮናው የሜዳሊያዎች ብዛት ቀዳሚ የሆነችው አሜሪካ ዘንድሮም በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሆና እየመራች ትገኛለች። አምና በተካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ላይ አሜሪካን ተከትላ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ ዘንድሮም ከቀዳሚዎቹ መካከል ትገኛለች።

ባለፉት ቀናት በተካሄዱ ውድድሮች አስደሳች፣ አስገራሚ እንዲሁም የሚያስቆጩ ሁኔታዎች መስተዋላቸው አልቀረም። በተለይ በሴቶች 10 ሺ ሜትር ርቀት የኢትዮጵያውያን አትሌቶች አይበገሬነት የተመሰከረበት ውጤት ከወርቅ እስከ ነሐስ ያለውን ሜዳሊያ ማስገኘቱ ውድድሩን በመልካም ስሜት እንዲጀመር አድርጎታል። አስፈሪና ጠንካራ በተባሉ ርቀቶች ደግሞ ሳይጠበቅ የተገኙ ሜዳሊያዎች ከወርቅ ያልተናነሰ ዋጋ የሚያሰጣቸው ነበሩ። በሌላ በኩል ያለ በቂ ዝግጅት የተኬደባቸው በሚመስሉ ርቀቶች ከማጣሪያ አለማለፍ፣ የቡድን ስራን በአግባቡ ባለመስራት ያልተመዘገቡ ውጤቶች እንዲሁም በአትሌቶች መዘናጋት የተነጠቁ ሜዳሊያዎች የሚያስቆጩና ለቀሪ ውድድሮችም ትምህርት የሚሆኑ ነበሩ።

ኢትዮጵያ ከምትካፈልባቸው ርቀቶች መካከል የመጨረሻው ሜዳሊያ የተገኘው ከትናንትና በስቲያ ምሽት እስከተካሄደው የ3ሺ ሜትር የወንዶች መሰናክል የፍጻሜ ውድድር መሆኑ ይታወቃል። በዚህም በደረጃ ሰንጠረዡ በ6 ሜዳሊያዎች ከዓለም ሀገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች (ትላንት፣ ዛሬ እና ነገ ለኢትዮጵያውያን የፍጻሜ ውድድሮች አልነበሩም)። አንድ የወርቅ፣ ሶስት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ያላት ኢትዮጵያ በሜዳሊያዎቹ ብዛት አሜሪካንን የምትከተል ቢሆንም በወርቅ ሜዳሊያ መበለጧ ነው ሶስተኛ ላይ እንድትቀመጥ ያደረጋት። በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች ብቻ አትሌቶቿን ይዛ በቻምፒዮናው የቀረበው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በቀዳሚነት ተቀምጣለች። በቀጣይ በሚኖሩ የተለያዩ ርቀቶች ላይም ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ መሪነቱን አጠናክራ እንደምትቀጥል ይጠበቃል።

በተለይ ሜዳሊያ ይመዘገብባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ ርቀቶች መካከል የሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል፣ የ5ሺ ሜትር እና የማራቶን ውድድሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ እምብዛም የማትታወቅባቸው ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሳትፎ አልፎ ሜዳሊያ ከተገኘባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ የሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል ነው። በርቀቱ በፈርቀዳጅ ውጤታማ አትሌት ሶፊያ አሰፋ እግር የተተኩት አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው እና መቅደስ አበበ ዓምና በተካሄደው የኦሪጎን ዓለም ቻምፒዮና የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ማስገኘታቸው የሚታወስ ነው። በመሆኑም ዘንድሮም እንደ ወንዶቹ ሁሉ በሴቶች በዚህ ርቀት በደረጃ ሰንጠረዡ ለውጥ ያመጣል በሚል ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች በውጤታማነት ከምትጠቀስባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ በሆነው 5ሺ ሜትርም የወርቅን ጨምሮ ሌሎች ሜዳሊያዎች ይገኛሉ በሚል ይጠበቃል። በርቀቱ ተደጋሚ ድል እንደመመዝገቡ ጠንካራ እና ልምድ ያላቸው አትሌቶች ዝግጅታቸውን አጠናቀው ውድድራቸውን ለማድረግ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተዋል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃም የተሻሉ አትሌቶች እንዲሁም ፈጣን ሰዓት ያላቸው በመሆናቸው የአሸናፊነት ግምቱን እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን፤ የ10ሺ ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ደግሞ ቅድመ ግምቱን ካገኙት ቀዳሚዋ ናት። በውድድሩ ላይ የታየውን የቡድን ስራ በዚህ ላይም በመድገም ለሀገራቸው ተጨማሪ ሜዳሊያ እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡን የሚያስደስት ውጤት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው የኢትዮጵያውያን የሜዳሊያ ኢላማ የሚያነጣጥረው በማራቶን ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታዎች እንደ አምናው ሁሉ አኩሪ ውጤት ይገኛል በሚል ይጠበቃል። በሁለቱም ጾታዎች የዓለም ቻምፒዮን የሆኑ አትሌቶችን ጨምሮ በርቀቱ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች ተካፋዮች ናቸው። ይኸውም ውድድሩን ከወዲሁ አስፈሪ ያደረገው ሲሆን፤ አትሌቶቹም በታላላቅ የማራቶን ጎዳናዎች ላይ በመሮጥ ከዚህ ቀደም የተጎናጸፏቸውን ስኬቶች በድጋሚ የግላቸው እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You