
– በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከስምንት ሺህ በላይ ደረሰ
አዲስ አበባ: – በመዲናዋ ከ40 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ማሽኖች መገጠማቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከውጭ የገቡና በሀገር ውስጥ ተገጣጥመው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከስምንት ሺህ በላይ መድረሳቸውን ተገልጿል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከ40 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርዎች ኃይል መሙያ ማሽኖች በተለያዩ አካባቢዎች ተገጥመዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ከመኖሪያ ቤታቸው በተጨማሪ ልክ እንደማደያዎች ሁሉ ተሽከርካሪያቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚሞሉበት አማራጭ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ማዕከላት ግንባታን ወደ ክልል ከተሞች የማስፋፋት ሥራና ረጅም ርቀት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ገበያ የማስገባት ሥራ ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በሌሎች የሀገሪቷ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ማዕከላት ለማስፋፋት ከሚመለከታቸው ተቋማት፣ ድርጅቶችና ከግሉ ዘርፍ ጋር በማቀናጀት ማዕከላቱ የሚገነቡበት ቦታ እንዲያመቻቹ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሀገሪቱን የነዳጅ ወጪ ለመቀነስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ተቀርጸው እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከውጭ የገቡና በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎችና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ከስምንት ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ በርኦ ገለጻ፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ በኢትዮጵያ የገቡበት ጊዜ በውል ባይታወቅም መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው የቀረጥ ማበረታቻና ከለውጡ ወዲህ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እየገቡ ነው።
ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ከውጭ ሀገራት ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች 15 በመቶ፣ በግማሽ ተገጣጥመው ለሚገቡ አምስት በመቶ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙት ግብዓታቸውን ከቀረጥ ነጻ በማድረግ ማበረታቻ ተሰጥቷል ብለዋል።
መንግሥት ያደረገው የቀረጥ ማበረታቻ የባለሀብቱ ተነሳሽነትና የሀገሪቷን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ እንዲሁም የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ለመደገፍ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
በ10 ዓመታት ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ 148 ሺህ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችንና አራት ሺህ 850 አውቶብሶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ዕቅዱን ለማሳካት ከሀገር ውስጥና ከውጭ አገራት ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ዘርፉን ከነዳጅ ጥገኝነት በማላቀቅ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ ይረዳል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ዘርፉ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለግል ዘርፉ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ከኢኮኖሚ ጠቀሜታና ከአየር ብክለት መከላከል ባለፈ የድምጽ ብክለትን ለማስቀረትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን የሚረዱ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የበላይነህ ክንዴ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮምፕሌክስ የኤሌክትሪክ መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እያመረተ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሀዩንዳይ ኩባንያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ እየገጣጠመ እንደሚገኘ ይታወቃል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2015