ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት ምሽት ባደረጓቸው ሁለት የዓለም ቻምፒዮና የፍፃሜ ውድድሮች ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል። በሴቶች 1500 ሜትር ወጣቷ አትሌት ድሪቤ ወልተጂ ቻምፒዮኗንና ባለክብረወሰኗን ኬንያዊት ፌይዝ ኪፕዬጎ ተከትላ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል የርቀቱ ባለክብረወሰን ለሜቻ ግርማም ሞሮኳዊውን የዓምና ቻምፒዮን ሶፊያን ኤልባካሊ ተከትሎ ለ3ኛ ጊዜ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። ለሜቻ ለወርቅ ሜዳሊያ ቢጠበቅም አልተሳካለትም፣ ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ካደረገው ጥረትና ከተጓዘበት መንገድ አኳያ ብዙዎችን ያስቆጨ ሆኗል።
በዶሃው ቻምፒዮና የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ትኩረት ያልተሰጠው ወጣት አትሌት የኬንያውያን የባህል ስፖርት ተደርጎ በሚቆጠረው ርቀት በእልህ አስጨራሽ ፉክክር አንገት ላንገት ተናንቆ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። ያ የብር ሜዳሊያ ግን ከወርቅም የላቀ ደማቅ ነው። ለሜቻ በወቅቱ የርቀቱ ኮከብ የነበረውን ኬንያዊ ኮንሲስለስ ኪፕሩቶ እስከ መጨረሻ ፈትኖ በ0.01 ማይክሮ ሰከንድ ተቀድሞ ነው የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው። በወቅቱ ኬንያዊውም አትሌት ማሸነፉን እርግጠኛ አልነበረም። የመቶ ሜትር ውድድር አሸናፊ እንኳን በቅፅበት በሚለይበት ዘመን ከሁለቱ አትሌቶች አሸናፊውን ለመለየት ደቂቃዎች ማስፈለጋቸው ፉክክሩ ምን ያህል እንደነበር ማሳያ ነው።
ለሜቻ ባልተለመደው ርቀት ታሪክ ማኖሩን ቀጥሎ ከአንድ በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ከገጠመው ጉዳት ሌላ ታሪክ ለመስራት ያደረገው ጥረትም ዳግም ሳይሳካ ቀረ። በውድድሩ እስከ መጨረሻ ታግሎ በወቅቱ በድንቅ አቋሙ ላይ በነበረው ሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤልባካሊ በመቀደሙ የብር ሜዳሊያ አጠለቀ። ይህም የብር ሜዳሊያ በኦሊምፒክ መድረክ ለኢትዮጵያ በርቀቱ በታሪክ የመጀመሪያ ነው። ከእሱ በፊት በርቀቱ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ትልቁ ውጤት በሞስኮ ኦሊምፒክ ፈር ቀዳጁ አትሌት እሸቱ ቱራ ያስመዘገበው የነሐስ ሜዳሊያ ነበረ።
ለሜቻ በሁለቱ ታላላቅ መድረኮች ለጥቂት ያጣቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች ቁጭት ፈጠሩበት እንጂ ተስፋ አላስቆረጡትም። በዚያም ቁጭት ወደ ዩጂን 2022 የዓለም ቻምፒዮና አቅንቶ ለሶስተኛ ጊዜ ወርቅ አልተሳካለትም። ሞሮኳዊው ኤልባካሊ በፉክክሩ በቀላሉ የሚረታ አልነበረም። ያም ሆኖ ለሜቻ የተለመደውን የብር ሜዳሊያ ማጥለቁ አልቀረም። ከብር ሜዳሊያው በላይ ግን በውድድሩ ብቃቱን እያሳደገ መምጣቱ ትልቅ ተስፋና ትርጉም ነበረው።
ይህም በሶስት ታላላቅ መድረኮች ማሳካት ያልቻለውን ወርቅ ከአሠልጣኙ ተሾመ ከበደ ጋር ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናከረለት። የ2023 የውድድር ዓመት አዲስና የተሻሉ አዳዲስ ስኬታማ ቀናቶችን ያየበት ሆነ። ለሜቻ ዘንድሮ የተለየ አትሌት ነው፣ ካለፉት ዓመታት በብቃትም በራስ መተማመንም አድጎ ብቅ ማለት ችሏል። ከወትሮው በተለየ በፈታኙ መሰናክል ፊት ሲቆም ግርማ ሞገሱ ለተፎካካሪዎቹም አስፈሪ አደረገው። ይህም ባስመዘገባቸው ስኬቶች እንጂ በከንቱ ሙገሳ ያገኘው አይደለም።
የዓመቱን የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በብቃት ማሸነፍ ዘንድሮ ለለሜቻ ቀላሉ ሥራ ሆኖ ታይቷል። ለሜቻ ፉክክሩ ከሰአት ጋር ሆኖ በርቀቱ አዲስ ታሪክና የዓለም ክብረወሰን በመሰባበር ተጠምዶ ያለፉትን ወራት አሳልፏል። ባለፈው የካቲት በፈረንሳይ ሌቪን የቤት ውስጥ የ3ሺ ሜትር ውድድር እኤአ 1996 ላይ በኬንያዊው ዳንኤል ኮመን ለሁለት አስርተ ዓመታት ገደማ ተይዞ የቆየውን የዓለም ክብረወሰን 7:23.81 በሆነ ሰአት በእጁ አስገብቷል።
የካቲት ላይ በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን የጀመረው ስኬት አድጎም ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማይታሰበው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ሰኔ ላይ ደግሞታል። ባለፉት በርካታ ዓመታት በርቀቱ ዓለምን ያስደመሙ ኬንያውያን አትሌቶች እኤአ 2004 ላይ የተመዘገበውን ክብረወሰን መስበር አልቻሉም። የኦሊምፒክና የዓለም የርቀቱ ቻምፒዮን ኤልባካሊም ይህን ክብረወሰን አልደፈረም። ለሜቻ ግን ዘንድሮ ያውም ከሁለት ወራት በፊት በ7:52.11 አንክቶታል።
ይህ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለና ብቃቱን እያሳደገ የመጣ ኮከብ በርቀቱ ሶስት ነገር ብቻ እንዲያልም አድርጎታል። ይህም ደጋግሞ ያጠለቀውን የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በወርቅ መቀየር ነው፣ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን መሆንና ሁለቴ ያሸነፈውን ኤልባካሊን ማሸነፍ ነበር። ያም ሆኖ ይህ ጥያቄ ትናንት ምሽትም አልተሳካም፣ ለወጣቱ አትሌት ግን ነገም ሌላ ቀን ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015