ኢትዮጵያ ከሁለቱ ኮከቦች የመጀመሪያውን ወርቅ ትጠብቃለች

19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነገ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ይጀመራል። በዕለቱ ከሚደረጉ ውድድሮችም የሴቶች 10ሺ ሜትር ፍጻሜ በጉጉት ይጠበቃል። እጅግ አጓጊውና በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ የሆነው ውድድር ምሽት 3 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ጀምሮ ይከናወናል። በርቀቱ በሚደረገው ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተለመደ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ሲሆን ኢትዮጵያም በቻምፒዮናው የመጀመሪያ ሜዳሊያ ከዚህ ፉክክር ትጠብቃለች።

በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ታሪክ ኢትዮጵያ በሴቶች 10ሺ ሜትር ርቀት 8 የወርቅ፣ 8 የብር እና 4 የነሃስ በድምሩ 20 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሃገር ናት። በዚህ ቻምፒዮናም በተጨማሪ ሜዳሊያዎች የኢትዮጵያ የበላይነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በውድድሩ የወቅቱ ቻምፒዮንና የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይን ጨምሮ በአራት የርቀቱ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶች የምትወከልም ይሆናል።

እአአ በ2021 በአስደናቂ ብቃት የዓለም ክብረወሰንን 29:01.03 በሆነ ሰዓት የሰባበረችው ጀግናዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ፤ አምና ኦሪጎን ላይ በተካሄደው ቻምፒዮና ያሳየችውን አስደናቂ አቋም ዘንድሮ ትደግማለች ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ዓመት በጃንሜዳ እና ባትረስ ሃገር አቋራጭ ተሳትፎ ባለፈ በሌሎች ውድድሮች ያልታየችው ለተሰንበት ድምፃን አጥፍታ ራሷን ለቻምፒዮናው ስታዘጋጅ ቆይታለች።

ዘንድሮ በ10ሺ ሜትር መወዳደር የጀመረችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ኮከብ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ለአሸናፊነት ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዷ ነች። በዓመቱ በተካፈለችባቸው ውድድሮች ሁሉ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ያጠናቀቀችው ጉዳፍ በስፔን በተካሄደው የሰዓት ማሟያ ውድድር 29:29.73 የሆነ አራተኛውን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች። አምና በኦሪጎኑ ዓለም ቻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ1ሺ500 የብር ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችው ጉዳፍ፤ በዚህ ዓመትም ቱሪን ላይ በአንድ ማይል ውድድር ክብረወሰን ለማስመዝገብ ተቃርባ በጥቂት ሰከንዶች ብቻ በመዘግየቷ ነበር ከእጇ የወጣው። በተመሳሳይ በርሚንግሃም የቤት ውስጥ 3ሺ ሜትር ውድድር የሃገሯ ልጅ የሆነችውን ገንዘቤ ዲባባን የዓለም ክብረወሰን ለመስበር በ9ማይክሮ ሰከንዶች ብቻ በመዘግየት የሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት መሆን ችላለች። ፍጥነት የዚህ ዓመት መገለጫዋ የሆነው ጉዳፍ ከወር በፊት በማጣሪያ ካስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት አንፃር በነገው ቻምፒዮናው የ10ሺ ሜትር ርቀት የመጀመሪያ ሜዳሊያዋን ታጠልቃለች ተብላ ትጠበቃለች።

የዘንድሮው ቻምፒዮና እጅግ ከባድ ፉክክር የሚታይበት እንደሚሆን በርካታ ማሳያዎች አሉ። በዚህ ርቀት ቅድመ ግምት ካገኙት የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ባሻገር የካቻምና የርቀቱ አሸናፊ ሆላንዳዊቷ አትሌት ሲፈን ሃሰን ከባድ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት እአአ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በ1ሺ 500 ሜትር የነሃስ እንዲሁም በ 5ሺ እና 10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ አስደናቂ ብቃቷን ማስመስከሯ የሚታወስ ነው። አትሌቷ ከዚያን በኋላ በለንደን ማራቶን መታየቷ ፊቷን ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች ያዞረች ቢመስልም፤ በድጋሚ ወደ መም በመመለስ በርቀቱ ሁለተኛውን የዓለም ቻምፒዮና ሜዳሊያዋን ለማግኘት ቀላል ተፎካካሪ አትሆንም። የ2019 የርቀቱ ቻምፒዮና ዳግም ክብሯን ለመመለስ እንደተዘጋጀችም ገልፃለች።

ብርቱዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በታወቁበትና ውጤታማ በሆኑበት በዚህ ርቀት ድሉን አሳልፈው ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቡድን በመሮጥ እንዲሁም ለአሸናፊነት የሚያደርጉትን ልዩ የአሯሯጥ ስልት ተግባራዊ በማድረግ ድሉ ከእጃቸው እንዳይወጣ ተዘጋጅተዋል። በዚህ ዓመት ርቀቱን ከ30 ደቂቃ በታች በሆነ ሰዓት ከገቡ ስድስት አትሌቶች መካከል አንዷ ሲፈን ሃሰን መሆኗ ቀላል ግምት እንዳይሰጣት ቢያደርግም ዘንድሮ የ10ሺ ሜትር ውድድርን ከተቀላቀለችው ጉዳፍ ጸጋዬ በ12 ሰከንድ የዘገየ ሰዓት ያላት መሆኑ ፉክክሩ ለእሷም ከባድ እንደሚሆንባት ማሳያ ነው።

እአአ በ2021 ሲፋን የርቀቱን ክብረወሰን ከአምስት ዓመት በኋላ በመስበር ደስታዋን አጣጥማ ሳትጨርስ በሁለተኛው ቀን አሻሽላ ከእጇ የነጠቀቻት የምንጊዜም ተፎካካሪዋን አትሌት ለተሰንበት ግደይን ለማቆም ከባድ ትግል ታደርጋለች። በዶሃ ዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተገናኙት ሁለቱ አትሌቶች ውድድራቸውን በሲፈን የበላይነት መደምደማቸው ይታወሳል። በመሆኑም ቻምፒዮናዋ ለተሰንበት ከሃገሯ ልጆች ጋር በመሆን የአትሌቷን የበላይነት ጉዞ ለማስቆም የሚያደርጉት ፍልሚያ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በኢትዮጵያ በኩል ከ30 ደቂቃ በታች በሆነ ሰዓት የሚኒማ ማሟያውን የሮጡትና ከፈጣኗ አትሌት ጉዳፍ በጥቂት ሰከንዶች ብቻ ተከትለው የገቡት አትሌት እጅጋየሁ ታዬ እና ለምለም ኃይሉ በቻምፒዮናው ይሰለፋሉ። ወጣቶቹ አትሌቶች በቡድን ስራ እንዲሁም ለአሸናፊነት በሚደረገው ጥረት ሚናቸው ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 12/2015

Recommended For You